በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ የ‘አክቲቪስቶች’ ሚና ከፍተኛ ነው። ይኹንና አክቲቪስቶቹ ብዙኀኑን ያውቁ ይሆን የሚለው እንደሚያጠራጥራቸው የገለጹት ገመቹ መረራ፣ በአክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች የመርሕ መደበላለቅ ጉዳይ ላይ የሰላ ትችታቸውን በምሣሌ እያዋዙ ሰንዝረዋል።
‘ጌም ኦቭ ትሮንስ’ የተሰኘ አንድ ዝነኛ ተከታታይ ፊልም አለ። ፊልም የመመልከት ልማዱ ያላቸው በርካቶች በሰፊው የሚያውቁት ፊልም ስለሆነ፥ አንድ “ዌስተሮስ” የተባለ ጥንታዊ ግዛትን ጠቅላይ ዙፋን ለመቆናጠጥ በግዛቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ “ክልሎችን” የሚያስተዳድሩ የመሳፍንት ቤተሰቦች በሚያደርጉት የሥልጣን ሽኩቻ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ከሚለው ባለፈ ስለ ፊልሙ ከማስተዋወቅ ልቆጠብ። (ፊልሙን ለማየት ዕቅድ ያለው ሰው ይህ ጽሑፍ የፊልሙን ታሪክ በከፊል የሚናገር ስለሆነ ታሪኩን አስቀድሞ ላለማወቅ ቀጣዮቹን ጥቂት አንቀፆች ቢያልፋቸው ይመከራል።) በኔ ዕይታ ፊልሙ በአጠቃላይ በበርካታ አስተማሪና ዛሬ ላይ ካለንበት ኹኔታ ጋር አያይዘን እያሰብን እንድናሰላስል በሚያስገድዱ ትዕይንቶች የተሞላ ነው። ከነዚህ ጥያቄ ከሚያጭሩ ትዕይንቶች አንዱ ደግሞ በፊልሙ ኹለተኛ ምዕራፍ፣ አራተኛ ክፍል ላይ ያለው አንድ ትዕይንት ነው።
በግዛቲቱ በስተሰሜን ያለው ክልል ገዢ የነበረው አባቱ በግዛቲቷ ንጉሥ መገደል እና በእህቶቹ በዚያ መያዝ የተበሳጨው ሮብ ስታርክ የተባለው የመጀመሪያ ልጅ ጦር አዝምቶ ወደ ግዛቲቱ መናገሻ ጉዞ ይጀምራል። በመንገዱ ላይ ያሉትን የንጉሡን አጋሮች በጦር ሜዳ እያሸነፈ ይሔዳል። ታዲያ ከአንዱ ውጊያ ማብቃት በኋላ ከአንዲት በጦርነቱ ለተጎዱት ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ የምትሰጥ ልበ ሙሉ ሴት ላይ ይመሰጣል፤ ቀርቦም አንዱን ተዋጊ ስታክም ያግዛታል፤ ይተዋወቃትናም ያዋራታል። እኔን የሳበኝ የውይይታቸው ክፍል ከሞላ ጎደል ይህ ነው፦
ሮብ፦ ሥምሽ ማነው?
ታሊሳ፦ ታሊሳ
ሮብ፦ የቤተሰብሽ ሥም?
ታሊሳ፦ ቤተሰቦቼ ለየትኛው ወገን እንደሚዋጉ ለማወቅ ነው?
ሮብ፦ የኔን የቤተሰብ ሥም ታውቂዋለሽ፤ እኩል እንሁን።
ታሊሳ፦ ይኼ ልጅ እግሩን ያጣው ባንተ ትዕዛዝ ነው። (ቀደም ብላ ስታክመው ወደ ነበረውና አንድ እግሩ ወደተቆረጠ ወጣት እያሳየች።)
ሮብ፦ አባቴን ገድለውታል!
ታሊሳ፦ ታዲያ ይኼ ልጅ ነው የገደለው?
ሮብ፦ እሱ የሚዋጋላቸው ቤተሰቦች ናቸው የገደሉት!
ታሊሳ፦ ይህ ልጅ የንጉሡ ጓደኛ ይመስልሃል? ወንዝ ዳር ያደገ ምስኪን የአሳ አስጋሪ ልጅ ነው። ምናልባት ለዚህ ጦርነት ከወራት በፊት በእጁ እስኪያኖሩለት ድረስ ጦር ጨብጦ አያውቅም!
ሮብ፦ ለልጁ ምንም ጥላቻ የለኝም!
ታሊሳ፦ እሱ እግሩን መልሶ ያበቅልለታል¡
ሮብ፦ እጃችንን ብንሰጥ፣ ይኼንን ደም መፋሰስ ማስቆም ይቻል ነበር፤ ይገባኛል¡ ከዚያ አገሪቱ ሰላም ትሆን ነበር፣ ሕይወትም በፃድቁ ንጉሥ አገዛዝ ፍትሐዊ ትሆናለች¡
ታሊሳ፦ ንጉሡን ልትገለው ነው?
ሮብ፦ አማልክቱ ከረዱኝ፣ አዎ።
ታሊሳ፦ ከዚያስ ምን?
ሮብ፦ አላውቅም!…
ታሊሳ፦ ንጉሡን ለመጣል እየታገልክ ነው። ግን ከጣልከው በኋላ ምን እንደምታደርግ ግን ዕቅድ የለህም?!!
በቅርቡ በማኅበራዊው ሚዲያ ጥቂት አክቲቪስቶች ያስጀመሩትን እና በሺዎች የሚቆጠሩት ተከታዮቻቸው ተቀብለው በሰፊው ያስተጋቡትን አንድ ዘመቻ ስመለከት ነው ከላይ ያለው ምልልስ ትዝ ያለኝ። ዘመቻው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት አልቻሉም፣ ይልቀቁ የሚል ይዘት ያለው ነው። እሺ፣ የጥያቄው መነሻና ዓላማ ምንም ይሁን ምን ጥያቄያቸው ተሰማና ሥልጣናቸውን ለቀቁ እንበል። “ከዚያስ ምን ይፈጠራል?” ብሎ የሚጠይቅና የጠየቀ ሰው አላጋጠመኝም። አብዛኞቹ የአገራችን አክቲቪስቶችም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አይደሉም። ምላሽ ከማጣታቸው ባለፈ የአክቲቪዝም ትኩረታቸው ምን ዘርፍ/ዘውግ ላይ ነው? ብሎ የጠየቀ ሰው ምላሽ አያገኝም። ሁሉም ጥያቄ፣ ሁሉም ችግር፣ ሁሉም ሐሳብ ይመለከተናል ብለው ያምናሉና።
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጡበት ዕለት ዋዜማ ከወዳጆቼ ጋር ቁጭ ብለን እየተወያየን ነበር። ውይይታችን “ኢሳያስን ሕዝቡ ወጥቶ ይቀበላቸዋል አይቀበላቸውም?”ን የጨመረ ነበር። ለውይይታችን ማጣቀሻነት ማኅበራዊ ሚዲያውን ተመለከትን። ልኂቃኑ በአብዛኛው የፕሬዝደንት ኢሳያስን መጥፎ ገጽታ በመተንተን አንድም ኢትዮጵያዊ ወጥቶ አቀባበል እንደማያደርግላቸው፣ ዐቢይ ኤርትራ ሔደው ሕዝቡ ወጥቶ የተቀበላቸው አሁን የተሾሙና ምንም ቁርሾ የሌላቸው በመሆናቸው መሆኑን ወዘተ. እየተነተኑ ነበር። አንደኛው ወዳጃችን የተናገረውን ነገር ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አለማሰብ አልቻልኩም። “ልኂቃኑ ሕዝቡን አያውቁትም! ነገ የሚሆነውን ታያለህ!” ነበር ያለው። በማግሥቱ ሕዝቡ ወጥቶ “ኢሱ፣ ኢሱ፣ ኢሱ” እያለ ተቀበላቸው። እውነትም ሕዝቡን አያውቁትም!
የታሪክ ምሁሩ ጢሞቲ ስናይደር መልካምነትን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዱን እነርሱ በመሆናቸውና የእያንዳንዳችንን እገዛ የሚሹ በመሆናቸው ተቋማትን ተከላከሉ ሲል ይመክራል። ተቋማት ራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ ከመነሻው ካልጠበቅናቸው ተራ በተራ ይወድቃሉ ይላል። አንድ “የኔ” የምትለውን ተቋም ምረጥና ከጎኑ ቁም፤ የምትመርጠው ተቋም ፍርድ ቤት፣ ጋዜጣ፣ ሕግ፣ የሠራተኛ ማኅበር፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል በማለት ይመክራል። ይህ ምክር ትልቅና የሕዝቦችን ሕልውና ሊወስን የሚችል ቁምነገር ያዘለ ነው። መሪዎች ይሔዳሉ፣ ይመጣሉ። አንዳንድ መሪዎች ደግሞ ላሰቡት አገዛዝ እንቅፋት ይሆናሉ ያሏቸውን ተቋማት ያስወግዳሉ፣ አሊያም ምንም እንዳይሠሩ አድርገው ሽባ ያደርጓቸዋል። ከዚያ ወደ ሕዝቡ ይዞራሉ። ሕዝቡም ከገዢዎቹ በትር ያስጥሉት ዘንድ ከዚህ ቀደም ከሚደርስባቸው ጥቃት ራሳቸውን መከላከል ይችላሉ በሚል ዕሳቤ ችላ ወዳላቸው ተቋማት ይዞራል። ቀድሞውኑ አልጠበቋቸውም፣ አልደገፏቸውም፣ አልተከላከሉላቸውም ነበርና ተቋማቱ የሉም። ሕዝብ የማይከላከላቸውን፣ በተለይ መንግሥት ያዳከማቸውን ተቋማት መተቸት ደግሞ ሌላ ጥፋት መፈፀም ነው። ለዚህ ነው በሌሎች ዓለማት ያሉ አክቲቪስቶች አንድ መብት፣ ችግር ወይም ሐሳብ መርጠው በአትኩሮት ለለውጥ ጩኸታቸውን የሚያሰሙት።
የታሪክ ምሁሩ ጢሞቲ ስናይደር መልካምነትን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዱን እነርሱ በመሆናቸውና የእያንዳንዳችንን እገዛ የሚሹ በመሆናቸው ተቋማትን ተከላከሉ ሲል ይመክራል። ተቋማት ራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ ከመነሻው ካልጠበቅናቸው ተራ በተራ ይወድቃሉ ይላል።
ፖለቲከኛ እና ‘አክቲቪስት’
እአአ በ2014 የወጣውና የጥቁሮችን የመብት ትግል የሚያሳየው ‘ሰልማ’ የተባለው ታሪካዊ ፊልም ላይ አንድ ትዕይንት አለ። ፊልሙ ውስጥ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሊንደን ጆንሰን ከትግሉ ግንባር ቀደም መሪ ከማርቲን ሉተር ኪንግ (ዶ/ር) ጋር በቢሯቸው ውስጥ ውይይት ያደርጋሉ። በውይይታቸው መሐል ታዲያ መጠነኛ መካረር ይፈጠርና ፕሬዝዳንቱ ኪንግን እንዲህ ይሉታል፦
“አሁን እኔን ትሰማኛለህ! ስማኝ! አንተ አክቲቪስት ነህ። እኔ ፖለቲከኛ ነኝ። አንተ አንድ ትልቅ ጉዳይ አለህ። እኔ አንድ መቶ አንድ ጉዳዮች አሉኝ። አሁን በዚህ ጉብኝትህ የበለጠ ገፍተህ እየጠየቅክና እኔ ላይ ጫና እያደረግክ ነው። ይሁን፣ ሥራህ ነው። ያንተ ተግባርህ እሱ ነው። ነገር ግን ባንተ ምን ማድረግ እንደምችል እና እንደማልችል መጠየቅ እና መስማት ትክት እና ስልችት ብሎኛል!”
እርግጥ ነው፤ በኛ አገር የፖለቲካና የአክቲቪዝም ድንበር በጣም ቀጭን፣ ምናልባትም የሚተላለፍና የተቀላቀለ ነው። በአመዛኙ እከሌ ፖለቲከኛ ነው፣ እከሌ አክቲቪስት ነው የምንለው ሰዎቹ ከሚያነሱት ጥያቄ ባሕሪ፣ ዓይነት እንዲሁም ከሚሹት ምላሽ ወይም መፍትሔ በመነሳት ሳይሆን ከጠያቂው የፖለቲካ ፓርቲ አባል/መሪ መሆን ያለመሆን በመነሳት ነው። ይህ ደግሞ ስህተት ነው። አክቲቪስት በሥልጣን ላይ የተቀመጠው አካል ማንም ይሁን ማን ትኩረቱ በችግሩ መቀረፍ እና በጥያቄው መመለስ ላይ ነው። ፖለቲከኛ በአንፃሩ ከመነሻው ጥያቄውን የሚያቀርበው እርሱ የሥልጣን መንበሩን ከያዘ ብቻ መፍትሔ የሚያገኝ እንደሆነ አድርጎ ነው። ግቡ የጥያቄው መመለስ ሳይሆን የጥያቄው በርሱ መመለስ መቻልን ማሳመን እና ወደ ሥልጣን መምጣት ነው። ለዚህ ዓላማ ሲባል ራሱን ችግሩንም ራሳቸው መፍጠር ድረስ ሊሔዱ ይችላሉ። የኹለቱ ሚና መቀላቀል አሊያም የአንዱ በአንዱ ተከልሎ ዓላማውን ለማሳካት መሞከር ውጤቱ እርስ በርስ መተማመንን የሚያሳጣና ሕዝብ በአንድነት ሊቆምለት የሚገባው ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ሳይቀር እንዲከፋፈል የሚያደርግ ነው።
ከዚህ አንፃር አንዳንድ የአገራችን (በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ያሉ) አክቲቪስቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እና የሚሹትን መፍትሔ ስመለከት አንዳንዴ “ምን እያደረጉና እያሉ እንደሆነ ይረዱታል ወይ?” ብዬ እጠይቃለሁ። “ከራሳቸው ድምፅ ውጪ መስማት የሚወዱት ነገርስ አለ ወይ?” እላለሁ። ምናልባት አካኼዳቸውን በአገራችን ፖለቲካ በስላቅ ደረጃ የተለመደችው “መርሕ አልባ” የምትለው ሐረግ ልትገልጸው ትችላለች። ጥያቄያቸውን፣ ዛቻቸውን፣ ፉከራቸውን፣ ወዘተ. የሚቀበልና የሚያስተጋባ ተከታይ እስካገኙ ጊዜ ድረስ ቀድሞ ያነሱት ጥያቄ መመለስ ትዝ ሳይላቸው ከአጀንዳ አጀንዳ ይዘላሉ። ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እስካሳየላቸው ጊዜ ድረስ ማንኛውንም ነገር ወይም ሰው በማጋነንና በማንኳሰስ፣ በማጥላላትና በማወደስ፣ በመካብና በማዋረድ፣ በማጋጋልና በማብረድ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። የሚያነሱት ጥያቄ ለሕዝቡ የሚጠቅምም ይሁን እነሱ ከሌሎች አቻ አክቲቪስቶች ጋር ለገቡበት እልህ እና የግል ፉክክር ምላሽ መሆኑን መለየት ያዳግታል። ይህ አስፈሪ አካሔድ፣ በተለይ ሕዝቦች እነዚህን አክቲቪስቶች ተከትሎ በብሔርና በቋንቋ እየተለያየ የጎሪጥ መተያየቱን ወደሌላ ደረጃ ባደረሱባት አገራችን ውስጥ የት ነው የሚያደርሰን?
መንግሥት በአክቲቪስቶች የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩር እና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ መደገፍና ማበረታታት ያለባቸው ራሳቸው አክቲቪስቶቹ ናቸው። ይህ የድጋፍና ክትትል ተግባራቸውም ነው የሐሳባቸውን ልዕልና፣ የተቆርቋሪነታቸውን እውነተኝነት እንዲሁም የዓላማቸውን ቀናነት የሚያሳየን። በአገራት ታሪክ እና በሕዝቦች ኑሮ ላይ አዎንታዊና በገንዘብ የማይተመን ለውጥ ያመጡትን የበጎ ፈቃደኝነትን እና የማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ የሚወልደውም የዚህ ዓይነት ጤነኛ አክቲቪዝም ነው። አሁን እየታዘብኩ ባለሁት አካሔድ ግን፣ ድንገት አገራችን የሕዝቡን ጥያቄ እና ችግር ለመቅረፍ የሚተጋ መንግሥት/መሪዎች ብታገኝ እንኳን ይኼንን መልካም አጋጣሚ እና ዕድል ልናባክን እንደምንችል አስባለሁ። ምክንያቱም በቀናነት የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚፈልግ መሪ እንኳን ቢሆን፣ ካልተደገፈና በአመፅ፣ በረብሻና ከፋፋይ የተንኮል ጥያቄዎች ከተከበበና ከተጣደፈ፣ ከላይ እንዳየነው እንደ ፕሬዝደንት ጆንሰን ትክት እና ስልችት ሊለው፤ ተነሳሽነቱንም ሊያጣ ይችላልና።
አክቲቪስቶቻችንንስ ማን ይቀስቅሳቸው?
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ በጠቀስኩት የ‘ጌም ኦቭ ትሮንስ’ ትዕይንት ላይ ያለው የሮብ ስታርክ እና የታሊሳ ውይይት በዚህ ነበር የሚያበቃው፦
ሮብ፦ ያከምሺው ልጅ አንቺ እዚህ በመምጣትሽ ዕድለኛ ነው።
ታሊሳ፦ አንተ እዚህ በመምጣትህ ዕድለ ቢስ ነው!
ምናልባት የአክቲቪስቶቹ መኖርና ውትወታ በርካታ የሕዝቡ ማኅበራዊ ችግሮች እንዲታዩና እንዲሰሙ፣ ብሎም መፍትሔ እንዲያገኙ አስችሎ ይሆናል። ያኔ ሕዝቡም በነርሱ መኖር ዕድለኛ ሆኗል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው፣ በኅብረተሰቡ ኑሮና መስተጋብር ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖና ውጤት በአግባቡ ያልታሰበባቸው እና ያልተገመገሙ ጥያቄዎችና ቅስቀሳዎች፣ ፉከራዎች እና ዛቻዎች በተመለከትኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ሕዝቡ ምን ያህል ዕድለ ቢስ እንደሆነ ነው የማስበው።
“ከአፍ የወጣ አፋፍ” ይላል የአገራችን ሰው። ከአፋችን የወጡ ቃላት ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለንም። ልንቆጣጠራቸው፣ ልናስቀራቸው፣ አሊያም ከወሰንን አቆይተን ልናወጣቸው የምንችለው ከአፋችን ከመውጣታቸው በፊት ብቻ ነው። አንድ አክቲቪስት በስሜት፣ በፉክክር አሊያም በጥላቻ ተነሳስቶ የሚያደርገው ቅስቀሳ በርካቶች ተከታዮቹ ዘንድ ይደርሳል። ተከታዮቹም የሰሙትን የርሱን ቅስቀሳ ለመተግበር የሐሳብና የተግባር ዝግጅት ሊያደርጉ አሊያም ምቹ አጋጣሚ እየጠበቁ ይሆናል። በዚህ መሐል ግን እርሱ ወደ ሕሊናው ቢመለስ እና ባደረገው ቅስቀሳ ጥሪው ተፀፅቶ “ተሳስቼ” ነበር ቢል ተከታዮቹ አይሰሙትም፤ የቅስቀሳውን ሐሳብ የራሳቸው አድርገውታልና። ከዚያም ባለፈ በተቃራኒው ወገን ያለውና በርሱ ቅስቀሳ ያዘነው፣ አፀፋዊ ጥላቻና ፉክክር ውስጥ የገባን የኅብረተሰብ ክፍል እንደመረዘው ይቀራል። አክቲቪዝም በመርሕ እና በኀላፊነት ስሜት ካልተተገበረ መዘዝና ዳፋው፣ ችግርና መከራው ለሚታገሉለት እና እቆረቆርለታለሁ ለሚሉት ሕዝብም ነው የሚተርፈው።
ሳይረፍድና ምንም ማድረግ የማይቻልበት ኹኔታ ሳይፈጠር በፊት ታዲያ ራሳቸውን ብቻ የሚሰሙትን እነዚህን አክቲቪስቶቻችንን ማን ይቀስቅሳቸው? ምናልባት በደኅና ጊዜ የቀሰቀሱት ሕዝብ ራሱ ሊቀሰቅሳቸው ይችል ይሆን? አክቲቪስቶቹ በየደረጃው ያሉ የአገር መሪዎችን “ይውረዱ፣ ይሰቀሉ፣ ወዘተ.” ሲሉን ሕዝቡ በጽሑፉ መግቢያ ላይ እንዳለችው ሴት “እሺ ወረዱ፣ ከዚያስ ምን?” ብሎ ጠይቆ ዓላማና ዕቅዳቸውን ተረድቶ መጠንቀቅ ይችል ይሆን? የእሳት አደጋ ሲፈጠር እሳቱን ለማጥፋት ከሚውሉት ስልቶች አንዱ “ማስራብ” ይሰኛል። እሳቱ ሊያቃጥላቸው የሚችላቸውን በዙሪያው ያሉ ዕቃዎች ማንሳት ነው ማስራብ። እሳቱ በዙሪያው የሚበላው ነገር ሲያጣ ራሱ ይከስማል። አገር አልባ ዕድለቢሶች ከመባላችን ወይም ከመሆናችን በፊት አንዳንድ አክቲቪስቶችን በዚሁ መልኩ “ማስራብ” ይቻል ይሆን?
ገመቹ መረራ የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
fana@ethiopianlawgroup.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011