በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ያስተላለፈውን መልዕክት በመንተራስ፥ ቤተልሔም ነጋሽ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ግልጽ ካለመሆኑም ባሻገር ሐሰተኛ መረጃ የበዛው ፖለቲከኞችና የመገናኛ ብዙኀን ኃላፊነታቸውን ስላልተወጡ ነው በማለት የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርበዋል።
ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጽ ያጋራው “የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ስለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ያስተላለፉት መልዕክት” በሚል ርዕስየማኅበራዊ ሚዲያን አደገኝነትና ለሐሰተኛ ዜና፣ ለጽንፈኞች መሣሪያ መሆን አስመልክቶ የተሰጠ በኃይለ ቃላት የታጀበ መግለጫ ነው።መግለጫው ከተለጠፈበት ጊዜ አንስቶ በዛው በማኅበራዊ ሚዲያ ማለትም በፌስ ቡክ መግለጫው የተለያዩ ምላሾችን አግኝቷል። መግለጫው ጽሕፈት ቤቱ ሰርክ ሲያጋራቸው ከነበሩት ተስፋን ያዘሉና አዎንታዊ መልዕክት ያላቸው የፌስ ቡክ/ትዊተር መልዕክቶች የተለየ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና ጠንካራ ቃላት የያዘ በመሆኑ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል። የተለያዩ መገናኛ ብዙኀንም በመግለጫው ላይ ዜጎች በተለይ በአክቲቪዝም ይሁን በሌሎች ሁኔታዎችና መድረኮች ያገባኛል ብለው በግል ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ግለሰቦችን አስተያየት እየጠየቁ ዘገባ ሠርተዋል። ይህም ጉዳዩ ያገኘውን ትኩረትና የነበረውን ጠንካራ ምላሽ ያሳየ ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያ ለማትከታተሉ አንባብያን የመግለጫውን ይዘት በተመለከተ ሐሳብ ለመስጠት አንድ ኹለት አንቀጾችን ካጋራሁ በኋላ በመግለጫው ላይ ያለኝን ሐሳብ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
“መርፌ አይናማ ናት ባለ -ስለት። እግሩ የፊቷን እንጂ የሚከተላትን አታይም። እናም ጨርቅ ላይ እሷ አለፍኩ ብላ የክርና የገመድ መዓት ታስገባበታለች። የእኛ ሀገር አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ጦማሪዎችም ልክ እንደመርፌዋ ናቸው። እነሱ ሃገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል። ድረ- ገፃቸውን የሚያነብላቸው ተከታታይና ደጋፊ ማብዛታቸውን እንጂ ሃገርና ሕዝብ ላይ እየተከሉ ያሉትን አደጋ፣ እየረጩት ያለውን መርዝ ሊያዩት አልቻሉም።
ባለፉትጥቂትወራትሀገራችንያስመዘገበቻቸውንየድልስኬቶችበመዘርዘርናከእርሱምትይዩየገባችበትንየፖለቲካቀውስለእናንተበማስታወስጊዜአችሁንማባከንአይገባም።አሁንያለውትልቁቁምነገርከዚህከገባንበትአሳሳቢቀውስራሳችንንም፣ሀገራችንንምእንዴትእናውጣትየሚለውነው።
ሁለትየገመድጽንፎችንይዘውየቆሙኃያላንበሚያደርጉትጉተታኢትዮጵያናኢትዮጵያውያንአደገኛውጥረትውስጥየከተቱበትወቅትላይእንገኛለን።
ልበሥውርሆኖግራናቀኝንበጥሞናማስተዋልበተሳነውጽንፈኛቡድንየሀገራችንአየርምድሯሰላምናተስፋንከመተንፈስይልቅየስጋትናየውድመትደመናንአርግዞየመከራዶፉንሊጥልከአናታችንበላይመጣሁመጣሁይላል።
መካረርእዚህምእዚያምበርትቷል።ተፈጥሮነውናየተወጠረናየተካረረጉዳይቆይቶመበጠሱአይቀርም።
“የማንቤትጠፍቶ፣የማንሊበጅ፣ያውሬመፈንጫይሆናልእንጂ” የሚለውየሽፍቶችፈሊጥእንጂየሰላማዊዜጎችመመሪያአይደለም።
በእውነትኢትዮጵያዊነትየሚፈተንበትወቅትእየመጣነው፤ማንምጣፋጭዘርናፍሬነኝብሎሊኮራናሊመጻደቅየሚችለውየግንዱሥርእስካለብቻነው።የግንዱንሥርቆርጦናነቅሎበቅርንጫፉናበዘሩመኩራትየሞኝጨዋታይሆናል።
… በማህበራዊ ሚዲያ በጣም የበዙ የሐሰት መረጃዎች ይተላለፋሉ። ሐሰት ጮሆ ስለተነገረ፤ ጎልቶ ስለተፃፈ፤ በብዙ ሰዎች ስለተደገፈ ወይም በታዋቂ ሰዎች ስለተወራ እውነት አይሆንም። ኢትዮጵያ ግን የዘላለም እውነት ነች። በሐሰት ዜናም ሆነ አሉባልታ የማትፈርስ ፅኑ መሠረት ያላት እውነት ናት”
ሊተላለፍ የፈለገው መልዕክት ግልጽ አይደለም
ማኅበራዊ ሚዲያን ለመጥፎ ተግባር የሚጠቀሙበት አካላትና ግለሰቦች መኖራቸው ግልጽ ነው። እዚሁ ሚዲያ ላይ መጥቶ እነኝህን አካላት ለማስጠንቀቅ ይህንኑ መድረክ መጠቀሙም ጥሩ ነው። ነገር ግን ከቃላቱ ጠንካራነትና በጉዳዩ በከፍተኛ ሁኔታ መማረርን ከማሳየት ውጪ መልዕክቱ በእርግጥ ስለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ወይስ በአገሪቱ ላይ በአጠቃላይ እዚህም እዛም ባለው መፈናቀልና ነውጥ ላይ የተሰነዘረ ነው የሚለው ግር ይላል። ይኸውም በጥቅሉ ኢትዮጵያን ለመበታተን ተነስተዋል ስለተባሉ አክራሪ ኃይሎች ከመናገር አጥፊዎቹን መጥቀስና ቢቻል መውቀስ ለምን አልተቻለም። የሐሰት መረጃዎቹ የትኞቹ ናቸው ለሚለው ቢያንስ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ ወይም አምጥተዋል የተባሉትን ለይቶ በዚሁ ላይ መገናኛ ብዙኃንን ጠርቶ መግለጫ መስጠትስ ለምን አልተቻለም።
ሌላው ደግሞ ሐሰተኛ የተባሉት ዜናዎችስ ʻሐሰተኛ ያስባላቸው ምንድነው?ʼ የሚለው ነው። ይህን ያልኩት የሐሰተኛ ዜናዎችን ብያኔ በሚመለከት ክርክር በመኖሩ ምክንያት ነው። ለምሳሌ በየል ዩኒቨርሲቲ ሐሰተኛ ዜናዎችን በሚመለከት የወጣ ጽሁፍ የሐሰተኛ ዜና ትርጉም ስያሜው ሐሰት የሚለውን ቃል ስለያዘ በዚህ ሥር የሚካተቱት ጨርሶ ያልተደረጉ በሬ ወለደ ዓይነት ወሬዎች ብቻ ናቸው ተብሎ ሊደመደም እንደሚችል ጠቅሶ ያልተደረገ ድርጊትን ብቻ ሳይሆን የተፈፀመ ድርጊትንም ጨማምሮ ወይም የተወሰነ መረጃ አስቀርቶ ሰዎች እንዲረዱት በተፈለገው መልኩ እንዲረዱት ለማድረግ መሞከርም እዚህ ትርጓሜ ውስጥ ሊገባ ይገባል ይላል።ለምሳሌ ያህል ዜናው እውነት ሆኖ ምስሉ ከሌላ ቦታ የተወሰደ ከሆነ ድርጊቱን ባልተገባ መልኩ የሚያሳይ ነው።
እዚህ ላይ በተለምዶ “የመንግሥት” የምንላቸው የአገራችን መገናኛ ብዙኀን እንደምሳሌ ሊጠቀሱ ይገባል። በማኅህበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መረጃዎችን ተከታትሎ ሐሰት ከሆኑ ሐሰት መሆናቸውን በመናገር የሐሰት ዜናን በማጋለጥ የነበራቸው ሚና ምንም ነው ለማለት ይቻላል። ጭራሽ ባለሥልጣናት ያልፈለጉት መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ በቀረበ ቁጥር መልስ መስጫና ትክክለኛ ላልሆነ መረጃ ማቅረቢያ እየሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ምሳሌዎችን ባለመሰጠቱ እየተቸ ያለው ምናልባትም የማይፈልገው መረጃ በመውጣቱ ነው ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በሌላ ጎን በማኅበራዊ ሚዲያ ወጥተው መንግሥት በባለሥልጣናቱ በኩል ያስተባበላቸው መረጃዎች የማይስተባበሉበት ደረጃ ሲመጣ ወይም በውጪ ሚዲያ ሲዘገቡ ተመልሶ ትኩረት ለመስጠት መሞከሩ የሚያሳየው ሐሰት ተብለው የተሸፋፈኑ መረጃዎች ሁሉ ምናልባት የቀረቡበት መንገድ ተለይቶ ይሆናል እንጂ ሐሰት እንዳልነበሩ ነው፡፤
ማኅበራዊ ሚዲያ በጎ ጎን እንደሌለው አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም
ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጥፎ የሚጠቀሙበት እንዳሉ ሆነው ለበርካታ በጎ ምግባራት መዋሉን መርሳት አይገባም። የጌዲኦ ቀውስ ዘግይቶም ቢሆን የመንግሥትንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ያገኘው ማኅበራዊ ሚዲያው ከአካባቢው ባሉ ሰዎች ጭምር ታግዞ እውነቱን ስላወጣ ነው። በዚሁ ላይ መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን ሳይጀምር በግለሰቦችና ይህንን ብለው በተሰባሰቡ ደጋግ ኢትዮጲያውያን አማካኝነት ድጋፍ ማሰባሰብ የተቻለው በማኅበራዊ ሚዲያው ነው። ሌላው ቢቀር በዳያስፖራ ያሉ አክቲቪስቶች ሳይቀር ከፍተኛ ድጋፍ ያሰባሰቡት በማኅበራዊ ሚዲያ የተደረጉ ዘመቻዎችን ተከትሎ ነው፡፤
በእርግጥ በመግለጫው መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ተብሎ የመጥፎ ድርጊቱ ፈፃሚዎች በቁጥር ከአጠቃላዩ ተጠቃሚ ጋር እንደማይመጣጠን መገለፁ አግባብ ነው። ነገር ግን ሙሉ መግለጫው ማኅበራዊ ሚዲያን ከሐሰተኛ ዜናና ከሽብር ጋር አቆራኝቶ በጎ ጎን እንደሌለው አድርጎ የሚያቀርብ መምሰሉ ትክክል አይደለም። ጥፋቱን የሚፈፅሙትንም እንዲሁ ትክክለኛ ምክንያታቸውንና ከጀርባቸው ያለ አካል ይኑር አይኑር በትክክል ማወቅም ይሁን መገመት በሚከብድበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱ ጽንፈኞች አድርጎ መሳሉም በበኩሌ አግባብ ነው ብዬ አላምንም።ሐሳብን በነፃነት መግለጽ በተከበረበት አገር እውነትን በመረጃ በማውጣትና እነሱንም በማጋለጥ ሐሳባቸውን መሞገትና ተቀባይነት አጥተው አፍራሽ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ በተለይ ከመንግሥት የሚጠበቅ ይመስለኛል።
ሐሰተኛ መረጃ የበዛው ፖለቲከኞችና የመገናኛ ብዙኀን ኃላፊነታቸውን ስላልተወጡ ነው
ባለፈው ሳምንት የተሳተፍኩበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከናወነ ሐሰተኛ ዜና በኢትዮጵያ ሥጋት ስለመሆኑ እና እንዴትስ ጉዳት እንዳያመጣ ማድረግ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ለመምከር ያለመ አንድ ኹነት ላይ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር የሆኑት መኩሪያ መካሻ እንዳሉትና በግሌም እንደምስማማው ለሐሰተኛ ዜና እየጨመረ መምጣት አንዱ ምክንያት መገናኛ ብዙኀን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር በሚጣጣም መልኩ ወቅታዊ መረጃዎች በተከታታይ መስጠት አለመቻላቸው ነው።አንድ ኹነትን ወይም ድርጊትን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምጭምታ ሲሰማ ወይም መጋራት ሲጀምር መገናኛ ብዙኀኑ በመረጃው የተመለከተው አካል ዘንድ በመሔድ የተባሉትን ተቀብለው ማውጣት ሳይሆን መረጃው ሐሰት መሆን አለመሆኑን የማጣራት ግዴታም አለባቸው። እዚህ ላይ ሚዲያዎች በተለይ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ድሮ ከለመዱት አሠራር ብዙም ፈቀቅ አላሉም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፥ ምክንያቱም በርካታ ሰዎችን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ሽፋን ለመስጠት እስኪታዘዙ ወይም ጉዳዩ ከቁጥጥር እስኪወጣ ድረስ ሲጠብቁ ታይተዋልና (ጊዲኦ፣ ለገጣፎ፣ሱሉልታ መጥቀስ ይቻላል)።
ከዚህ ሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ዓይነተኛ ወይም የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ መሆኑ እንዲቀር መገናኛ ብዙኀን ከተቋቋሙበት ዓላማም አንፃር የሚዲያ አጠቃቀምን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኀንም ይሁን ባለፈው ሳምንት በቢቢሲ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ እንደተደረገው ከዩኒቨርሰቲዎች ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምንና የሐሰት ዜናዎችን መለየት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ተከታታይ ትምህርት መስጠትና የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት አለባቸው።
ፖለቲከኞችም ʻወሬው በራሱ ይሞታልʼ በሚል ተስፋም ይሁን በሌላ ምክንያት ከሚዲያ መሸሽም ሆነ ሚዲያ ላይ መውጣት እንጂ ሌላ አማራጭ የሚጠፋበት ወቅት ላይ ሲደርሱ ነገሩን መሸፋፈን፣ መካድ፣ ሌላ አካል ላይ ማላከክ ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ሊረዱት ይገባል። ሌላው ቀርቶ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸውን ከአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመማር ተከታታይ መረጃ የሚሰጥባቸው ሐሰተኛ ዜናም ሲወጣ ማስተባበያውና እውነቱ የሚወጣባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ይችላሉ። ሰዎችም የሚያጠራጥር መረጃ ሲወጣ መሥሪያ ቤቱ ገጽ ላይ በመሔድ ማጣራት ይችላል። እነሱም ይህን በማድረግ ከሕዝቡ ጋር ቀጥታ መገናኘትና ተዓማኒነትን ማትረፍ ይችላሉ። ስለሆነም መገናኛ ብዙኀንም ይሁኑ መንግሥት ሌላውን አካል ከመውቀስ በፊት መረጃ በመስጠት ረገድ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን ምንያህል ተውጥተዋል የሚለውን መፈተሸ ይገባል።
ከሁሉም በላይ ደግመ ማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠራቸው የመሰሉ ቀውሶችንና አደገኛ አዝማሚያዎችን ከምንጫቸው ለማስወገድመሥራት ይገባል። ይህን ያልኩበት ምክንያትም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መግለጫው ከይዘቱና አቀራረቡ ጋር ሲታይ ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ብቻ ጋር የተያያዘ ነው ለማለት ስላላስቻለኝ ነው።
ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011