“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ሕይወት ጣፋጭ፣ አስደሳችና አጓጊ ብትሆንም የሕይወት ጉዞ ግን ሁል ጊዜ አልጋ በአልጋ አይደለም። በሕይወት ጉዞ ላይ ጋሬጣ የሚሆኑ ነገሮችም ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆኑ ሰው ሰራሽም ጭምር ናቸው። ለምሳሌ ለእኩል ሥራ በወንድና በሴት ሠራተኞች መካከል ያለው የደሞዝ ልዩነት፣ የሴትን የሥራ ድርሻ በቤት ውስጥ ሥራና ልጅ በማሳደግ መወሰን አለበት የሚለው አመለካከት፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሳቢያ የሚደርሰው ጉዳት፣ ከለከፋ እስከ ተገዶ መደፈር ከድብደባ እስከ ግድያ ከዘለፋ እስከ የአሲድ ጥቃት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ሁሉ ሰው ሰራሽ ነገሮች ናቸው። እናም አመለካከትን በመለወጥ ብቻ ልንቀርፋቸው እንችላለን።
ይህንኑ ተስፋ አድርገንና የአስተዋጾ ትንሽ የለውም በሚል እምነት ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከጓደኛ፣ ከወዳጅና ዘመድ ጋር ስናወራ ችግሩን በማሳየት፣ በሴቶች ጥቃት እንዲሁም እኩልነትን ባለመቀበል ምክንያት የምትጎዳው ሴትዋ ብቻ ሳትሆን ማኅበረሰቡም ጭምር እንደሆነ ለማስረዳት የምንሞክር ሴቶች አለን። ታዲያ በዚህ መንገድ የሚያውቁን ሰዎች ሌሎች ማኅበራዊም ሆነ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አንድ ዜጋ አመለካከታችንን ስናንጸባርቅና አስተያየታችንን ስንሰጥ ሐሳባችንን እንደ ሐሳብ ከመሞገት ይልቅ “የሚያምርብሽ ሴቶች ሴቶች እያልሽ ስታወሪ ነው” የሚል ነገር ሲሰነዝሩ አስተውያለሁ።
ስለሴቶች እኩልነት በተደጋጋሚ የምንናገረው ይህን መሰል ያንቺ ድርሻ ይሔ፥ የእኔ ደግሞ ይሔ የሚለውን አመለካከት ለመቀየር ቢሆንም የፆተኝነት አስተሳሰቡ መልኩን ቀይሮ ስለሴቶች እኩልነት የሚናገሩ ሴቶች ድርሻ ሁል ጊዜ ስለጾታ እኩልነት መሟገት ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ መምጣቱ ምን ያህል የፆተኝነት አስተሳሰብ ሥር የሰደደ፣ በአንዱ ጋር ልናፈርሰው ስንሞክር በሌላው ጋር የሚበቅል እንደሆነ ያሳያል።
ታዲያ ይህንን ባየሁ ጊዜ ከመገረም ባለፈ “መፍትሔው ምንድነው?” ብዬ መጠየቄ አልቀረም። እናም በእኔ እምነት መፍትሔ ብዬ የማስበው አንደኛ ሴቶች የእኩልነት ጥያቄን ከመጠየቅ ጎን ለጎን በማኅበራዊም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አንድ ዜጋ ገንቢና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው። ጠቃሚ ሐሳብ፣ ገንቢ ትችትና አብሮነትን የሚያጎሉ አስተያየቶችን እንደ ዜጋ መሰንዘር አለባቸው። ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ “ዝም ብለሽ ስለሴቶች ብቻ ተናገሪ” የሚል ትችቶች ቢደጋገምም በሒደት ግን ይህ አመለካከት እየተሸረሸረና እየጠፋ ይሔዳል። እንዲሁም መሬት ላይ ባሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፖለቲካውም፣ በማኅበራዊውም፣ በʻሲቪክ ሶሳይቲʼዎች እንዲሁም በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ በወደድነው መንገድ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሕይወታችንን በአንድም ሆነ በሌላው መንገድ የሚነኩን ኹነቶች ላይ የእጃችን አሻራ ያረፈባቸው መሆናቸውን ማሳየትና የእኩልነት እንቅስቃሴውን ሰዎች፥ እኩል መሆናችንን እንዲያውቁ ከመወትወት ባለፈ በተግባርም እኩል መሆናችንንና ምን ላይ መሳተፍ፣ ስለምን ማውራት እንዳለብን የምንወስነውም እኛው እራሳችን መሆናችንን ማሳየት መቻል አለብን።
ኪያ አሊ
kiyaali18@gmail.com
ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011