የገንዘብ እጥረትያጋጠመው ዳሽን ቢራ 400 ሚልዮን ብር ከንግድ ባንክ ተበደረ

0
701

ዳሽን ቢራ አክስዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም ለወሰዳቸው ቆርኪ ፋብሪካና ብቅል ግብዓቶች ክፍያ ለመፈፀም 400 ሚሊየን ብር ከንግድ ባንክ እንደተበደረ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።

በኢትዮጵያ የቢራ ኢንዱስትሪ በአቅም ደረጃ ከሔኒከንና ቢጂአይ ቀጥሎ ሦስተኛን ደረጃ የያዘው ዳሽን ቢራ በአገሪቷ ባለፉት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ተከትሎ በተከፈተበት ዘመቻ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የገበያ ድርሻ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፈጠሩ አይዘነጋም። በዚህም የተነሳ ድርጅቱ የፋይናንስ እጥረት ችግር እንዳጋጠመው ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ይህንን ለጊዜው ለመፍታት ከንግድ ባንክ የአጭር ጊዜ ብድር መውሰዱን ምንጮች አክለዋል።

ምንም ዓይነት የፋይናንስ እጥረት የለብንም ያሉት የዳሽን ቢራ አክስዮን ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብርሃም ዘሪሁን ይህንን አስተባበለዋል። ከአቅም በላይ በማምረት የድርጅታቸው ምርቶች ተፈላጊነቱ እንደጨመረ እንዲሁም ምርታችን በጥቁር ገበያ እየተሸጠብን ነው ያሉት ኃላፊው የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማርካት በባሕር ዳር ማስፋፊያ መሰራቱንና የደብረ ብርሃን ማስፋፊያ ሊሠራ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ለድርጅቱ ያቀረበችው ጥያቄ ተከትሎ የዳሽን ቢራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንድሬስ ሄንደሪከ በሰጡት ምላሽ፡- ከንግድ ባንክ ብድር መውሰዳቸውን ባያስተባብሉም የገንዘብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግልፅ ማድረግ እንደማይቻል በላኩልን ደብዳቤ ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጭ እንዳገኘችው የዳሽን ቢራ ምርት ባለፉት ወራት አገሪቷ ገብታበት ከነበረው የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ በተለያዩ ቡድኖች ምርቱን የማጥላላት ዘመቻ ይደረግ እንደነበር ታውቋል። በዚህም የተነሳ ድርጅቱ የትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ የድርጅቱ የፋይናንስ አቅም ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ይታወሳል።

ይሁን እንጂ፤ በዚህ ዓመት የምርት ፈላጊው ጨምሯል የሚሉት አብርሃም ድርጅቱ በጎንደር የሚያመርተው 950 ሺሕ ሄክቶ ሊትር ስላልበቃ፤ ደብረ ብርሃን ላይ ኹለት ሚሊየን ሄክቶ ሊትር እያመረተ ነው ብለዋል። ከዚህም በላይ እንዲያመርት ማስፋፊያ እናደርጋለን ብለዋል። ደብረ ብርሃን ማስፋፊያ ለማድረግ ከኢንቨስትመንት ቢሮ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም አክለዋል።

በእንግሊዙ ቫሳሪ ግሎባል እና በጥረት ግሩፕ በባለቤትነት የተያዘው ዳሽን ቢራ በዓመት ሦስት ሚሊየን ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከዳሽን ቢራ በተጨማሪ ባላገሩ፣ ጃኖና ሮያል ድራፍትን እያመረተ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here