የመገናኛ ብዙኀን አረዳድን ማሳደግ የጥላቻ ንግግርን ለመግራት ዓይነተኛው መፍትሔ ነው

0
741

ከወራት በፊት መንግሥት የጥላቻ ንግግር ሕግ ለማውጣት እየሠራ እንደሆነ ባስታወቀበት ወቅት የብዙዎችን ቀልብ ስቦ የመወያያ ርዕስ መሆን ችሎ ነበር። በተመሳሳይ ከቀናት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ˝መርፌ ዐይናማ ናት – ባለስለት˝ በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ትሥሥር መድረክ ያስተላለፈው መልዕክት ተከትሎ እንዲሁ በድጋሚ ዐቢይ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ወጥቷል፤ በማወያየትም ላይ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ላይም ጎልቶ የወጣው መልዕክት አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪዎች ልክ እንደመርፌ በሚወጋ መልዕክታቸው አገርና ሕዝብ ላይ እየተከሉ ያሉትን አደጋና እየረጩት ያለውን መርዝ ሊያዩት አይችሉም የሚል ጠንከር ያለ ሐሳብም ተንፀባርቋል። በርግጥ እንደመርፌ በሚወጋው መልዕክታቸው እንደመርፌዋ የተቀደደውን ለመሥፋት፣ የተበተነውን ለመጠገን እንደሚሞክሩም ይታወቃል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽሕፈት ቤት መልዕክት ተከትሎ በማኅበራዊ ትሥሥር መድረኮች ጎራ ለይተው የተለያዩ ወገኖች ውይይቶችን ሲያካሒዱ ከርመዋል፤ አሁንም በማካሔድ ላይ ናቸው።

የጥላቻ ንግግርን በሕግ ማውጣት አለመውጣትን በተመለከተ የክርክር ሐሳብ መሆኑ በተለይ ዴሞክራሲ ባልዳበረባት ኢትዮጵያ ቀርቶ፥ ዴሞክራሲ ባደገባቸው ምዕራባውያን መካከል አንኳን ሥምምነት የሚደረስበት ጉዳይ አይሆንም። ምክንያቱም የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግ ተፈጥሯዊውን ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ይገድባል፡፡

ለዓለም ዐቀፍ ክርክሮቹ ማሣያ የሚሆነው አውሮፓ የጥላቻ ንግግርን በሕግ ስታግድ አሜሪካ ደግሞ አላግድም ማለቷ ነው፡፡ ኹለቱንም ለኢትዮጵያ እንደ አርአያ የመውሰድ ልምድ አለ፡፡ አንዱ ወገን እንኳን ኢትዮጵያ አውሮፓም አግዳለች ሲል፣ ሌላኛው አውሮፓማ የፍትሕ ስርዓታቸው ጠንካራ ነው፡፡ ሕጉን አላግባብ አይጠቀሙበትም ይላል፡፡ አሜሪካን ለሚያነሱት ደግሞ፣ የአሜሪካ ሕዝብ ተዓማኒነት ያላቸው ጠንካራ የመገናኛ ብዙኀን እና ሲቪል ማኅበራት ያሉበት አገር ስለሆነ የጥላቻ ንግግሮች እዚያ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጋር አይወዳደርም ይባላል።

የፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ ለማውጣት አስቸጋሪ የሚሆነው፣ አንድ ንግግር ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን አልፎ አስጊ የጥላቻ ንግግር መሆኑን መለየት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ፣ የጥላቻ ንግግርን ብቻ ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ በሚደረግበት ሰዓት ፍርድ ቤቱ በምሉዕነት ነጻ እና ገለልተኛ መሆን ካልቻለ ለመዳኘት ስለሚቸግር እና በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ተናጋሪ ማንነት እና የትነት ማወቅ ስለሚቸግር ነው፡፡

ስለሆነም ሕግ አንድ አማራጭ ቢሆንም በጣም ተመራጩ ግን አይደለም፡፡ ብዙ ባለሙያዎችም የሚመክሩት ሌሎች የንግግር ነጻነትን ሳይገድቡ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሔዎችን መፈለግ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተደራሲዎችን የመገናኛ ብዙኀን አረዳድ ማሳደግ ከመፍትሔዎች ሁሉ የተሻለውና አዋጪ መንገድ ነው፡፡

የተደራሲዎች የመገናኛ ብዙኀን አረዳድ ዕውቀት (‹ሚዲያ ሊትሬሲ›) የምንለው አንባቢያን ወይም አድማጭ/ተመልካቾች አንድ በመደበኛም ይሁን ማኅበራዊ ሚዲያ የቀረበን መልዕክት ሲያነቡ ወይም ሲያደምጡ ሒሳዊ (‹ክሪቲካል›) በሆነ መንገድ እንዲሆን ክኅሎታቸውን ማዳበር ነው፡፡

በዚህ እምነት አዲስ ማለዳ የጥላቻ ንግግርን ለመግታት፣ የሐሰት መረጃዎችን እና አሳሳች መልዕክቶችን ጉዳት ለመቀነስ በመንግሥት እና ሲቪል ማኅበራት እንዲሁም ኀላፊነት የሚሰማቸው ብዙኀን መገናኛዎች የሚከተሉት ተግባራት እንዲከናወኑ ጥሪ ታቀርባለች፡-

  • የብዙኃን መገናኛዎችን ሒሳዊ አረዳድ ክኅሎት ማሳደግ፣
  • የሐሰት ዜናዎችን በፍጥነት ማስተባበል እና እውነታውን ይፋ ማድረግ፣
  • የመንግሥትን ዕቅዶች፣ ሥራዎች እና እርምጃዎች ለሕዝብ ሁሌም ግልጽ ማድረግ፣
  • የሐሰት መረጃ እና የጥላቻ መልዕክት የሚያስተላልፉ ዜጎችን ማንነት ለሕዝብ ማሳወቅ

መንግሥት እና ዜጎች ይህንን ማድረግ ከቻሉ በሐሰት መረጃዎች እና በጥላቻ ንግግሮች መሬት ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት እና አገራዊ አለመረጋጋት አስቀድሞ መከላከል እና መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here