ብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ቦረናን ጨምሮ በኦሮሚያና ሶማሌ ብሔራዊ ክልሎች አዋሳኝ ከተሞች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥማቸውና ለድርቅ ሊጋለጡ ይችላሉ ሲል ሥጋቱን ገለፀ።
በእነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ከመጠን ያለፈ ዝናብ የነበረና ሰብል አበላሽቶ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት የዝናብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ፍንጭ መገኘቱ በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን አስደንግጧል።
በአገሪቷ ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በሚገኙት ተጋላጭ የሆኑት አካባቢዎች በሚያዝያ ወር ዝናባማ መሆን የነበረባቸው ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እርጥበት አለመታየቱንና የሙቀት መጠን መጨመር ሥጋት ማሳደሩን ተቋሙ ገልጿል።
በተለይም በአገሪቷ አፋጣኝ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ወደ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ባሉበት ወቅት ይህ ዓይነቱ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ፍንጭ መገኘቱ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ማወቅ ተችሏል። በአገሪቷ አፋጣኝ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተረጅዎች ምግብ ለማቅረብ አገሪቷ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ በቅርብ በመንግሥት መገለፁ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አህመዲን አብዱልከሪም ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የአየር ሁኔታው ተለዋዋጭ በመሆኑ በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ኦሮሚያና ሶማሌ የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። ይህም እንደ ጎዴ፣ ቀብሪደሃርና ቦረና ያሉ ከተሞችን ያካትታል።
በተጨማሪም አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ወቅቱ የእርሻ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት በመሆኑ በዝናብ እጥረት ምክንያት ምንም ዓይነት ዝግጅት አልተደረገም። ዝናብ የሚመጣ ከሆነ በቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን እንደተዘጋጁ ማወቅ ተችሏል።
ተቋሙ የትንበያ መረጃ እንደሚያመለክተው በእነዚህ አካባቢዎች በሚኖረው የዝናብ እጥረት የተነሳ አርብቶ አደሮች ለእንስሳት የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማግኘት አንጻር ከፍተኛ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በተጨማሪም በአንዳንድ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ ኦሮሚያ እንዲሁም በአርሲና ባሌ ዝቅተኛ ቦታዎች አነስተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ኤጀንሲው አስጠንቅቋል። እነዚህ እርጥበት አጠርና ከፍተኛ የውኃ ትነት ያለባቸው አካባቢዎች የውኃን ብክነትን ለመከላከል የሚያሰችሉ ዘዴዎችን ሊተገብሩ ያስፈልጋል ሲል ኤጀንሲ መክሯል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011



