“ለውጡ” ሴቶችን ከጥቃት ለማስጣል እንዲበቃ የመዓዛ ካሣ ጉዳይ እንደማሳያ

0
651

ባሳለፍነው ሳምንት ከሰማናቸው አሳዛኝ ዜናዎች አንዱ መዓዛ ካሣ የተባለች ግለሰብ በሥራ ባልደረባዋ በደረሰባት ጥቃት ሕክምና ስታገኝ ቆይታ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ጥቃት የፈፀመባት ሰው ከእስር ቤት ማምለጡ ደግሞ ሌላው አሳዛኝ ገጽታ ነው። ቤተልሔም ነጋሽ ይህንን ክስተት እንደማሳያ በመጥቀስ ዛሬም የሴቶች ጥቃት መከላከል ጉዳይ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ይላሉ።

ባለፈው አንድ ዓመት አገራችን በብዙ ለውጥና ነውጥ ውስጥ አልፋለች። ርዕሰ ጉዳዬን ከአንደኛ ዓመት በዓልና ሰሞኑን እያነበብን እና እየሰማን ካለው ያለፈው አንድ ዓመት ግምገማ ጋር ለማያያዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሥልጣን የመጡበትን ዕለት ምክንያት አድርጎ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ካደረጉት ንግግር በመጥቀስ ልጀምር።

“አገራዊ ማንነታችን ያለ እናንተ፣ ያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምንም ነው። አገሪቷን የገነቡ፣ ያገለገሉ፣ ያቆሙ ሴቶችን ዕውቅና በመንፈግ አገራዊ ትንሣኤን ማረጋገጥ አይቻልም። መንግሥታችን ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚቆመው፣ ለሴቶቻችን ውለታ ለመዋል ሳይሆን ለሁላችንም ብለን ነው። ግማሽ አካሉን የረሳን አገር ሙሉ የአገር ስዕል ይኖረው ዘንድ ከቶ እንደማይችልና ወደፊትም እንደማይራመድ መንግሥት በውል ይገነዘባል። በመሆኑም መንግሥታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀ መልኩ ለሴቶች ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሠራል።”

በሁሉም መስክ በእነኝህ 365 ቀናት የተመዘገበው እመርታ በመመዘን ላይ ነውና ከላይ በንግግራቸው ቅንጭብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገኙበት አሳዛኝና ትክክለኛ ያልሆነ ደረጃና አኗኗር ከነበረበት ምን ያህል ፈቀቅ አለ? በተለይም ደግሞ የሴቶች ጥቃት ጉዳይ እንዴት ነው? ለሚለው የሆነው ብዙ አይደለምና ቢያንስ በጥቅሉ መልካም ክስተቶችን መጥቀስ ይሻላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ዐሥር ሴት ሚኒስትሮችን ወደ ሥልጣን አመጡና በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፆታ ተዋፅዖ ምጣኔ 50፡50 ሆነ። ድርጊቱ የበለጠ አስደናቂ እንዲሆን ያደረገው ከተለመዱትና “ለስላሳ” ተብለው ለሴቶች ከሚሰጡ (ሠራተኛና ማኅበራዊ፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ ባሕልና ቱሪዝም) ውጪ መከላከያ፣ ትራንስፖርት፣ ሠላም፣ ሳይንስና ኢኖቬሽን ወዘተ. ያሉ ወትሮ በሴት ሚኒስትሮች ተመርተው የማያውቁ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችም በሹመቱ በሴቶች እንዲያዙ ማድረጉ ነው። ቀጠለና ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን አገኘን። ይህም በአፍሪካና በዓለምም ጭምር ሴት ፕሬዚዳንቶች ካላቸው አገራት ተርታ አሰለፈን። ከዚያ የመጀመሪዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው መዓዛ አሸናፊ ተጨመሩ፣ የምርጫ ቦርድም ብርቱካን ሚደቅሳን አገኘ።

እነዚህ ሹመቶች በብዙ መልኩ እጅግ አስደሳችና ታሪካዊም ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳንቆይ ነበር ድርጊቱ ካለው እምርታዊ ትርጉም ባሻገር ለሠፊው የኢትዮጵያ ሴት ምን ይጨምራል? የሚለው ላይ መወያየትና መከራከር የጀመርነው። አለፍ ሲልም ይህን ለውጥ በሴቶች የፖለቲካ ሥልጣን ውክልና ረገድ በግለሰብ (በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ) በጎ ፈቃድ የተሰጠ በመሆኑ እንዳይቀለበስ፣ወደኋላም እንዳንመለስ እንዴት ተቋማዊ እናድርገው፣ ተተኪ ሴት መሪዎችንስ እንዴት እናፍራ የሚለው ከመወያያነት አልፎ ፕሮግራም ተቀርፆ በመንግሥት ሳይቀር (ምሳሌ ጀግኒት ፕሮጀክት) ወደ መሠራቱ ተገብቷል።

የሹመቱ ፋይዳ ይቆየንና ከላይ በጠቀስኩት የጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር አንፃር በብዙ መልኩ ትርጉም ባለው መልኩ ጉዳያቸው ተካቶ ከችግር እንዲወጡ ከመሥራት አንፃር “የተረሱት” ሴቶች የሚያስብለንን እውነታ፣ ማለትም በሴቶች ላይ የሚፈፀም የኃይል ጥቃትን በሚመለከት ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን እንይ። በነገራችን ላይ ለዚህ መነሻ የሆነኝ በቀደመው ሳምንት በቢሮዋ በተፈፀመባት ጥቃት ሕይወቷ ያለፈውን አንዲት ሴት ሞት መነሻ በማድረግ የሰማሁት መረጃ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ብቻ በአብዛኛው “ወደድናችሁ” ባሉ ወንዶች የሰባት ሴቶች ሕይወት ማለፉ በማኅበራዊ ሚዲያ ተገልጿል። መረጃው የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር የቀረበለትና ፖሊስም የሚያውቀው ነው። እናስ “ለውጡ” ለሴቶች እንዴት ነው ብትሉ ዛሬም በመንገድ፣ በሥራ ቦታዎች በየካፌው “እምቢ ካልሽ አትኖሪም”፣ “ሻይ እንጠጣ ስልሽ እምቢ አልሽ” ተብለው በፖሊስ አባላት ሳይቀር ይደፈራሉ፣ ይገደላሉ። ወንጀለኞችን ለመያዝ ፖሊስ ያመነታል፣ ማኅበረሰቡ በሞቷ ሳያዝን “ምን አድርጋው ነው”፣ “ምን ለብሳ ነው” “ማን ፊት ስጪው አላት” ይላል።

እስቲ ባለፈው ሳምንት ሕይወቷ ያለፈውን መዓዛ ካሣ ታሪክ እንመልከት።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሻለ ሕክምናና ድጋፍ እንድታገኝ ጥረት ሲያደርጉ በነበሩ የሴት መብት ተሟጋቾች እንደተጋራው፦
“መዓዛ ካሳ የፋይናንስ ባለሞያና ዕድሜያቸው ሰባት እና አራት የሆኑ ልጆች እናት ነበረች:: ከኹለት ወር ተኩል ገደማ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በሥራ ቦታዋ ላይ እንዳለች የጥበቃ ካሜራ ባለበት፣ ቢሮዋ ውስጥ የሥራ ባልደረባዋ በነበረና ጌታቸው ዓለምፀሐይ በሚባል ግለሰብ በተደጋጋሚ በጩቤ ተወግታ በአለርት ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላት ቆይታለች። የሕክምና ወጪዋ እየጠነከረ ሲመጣ ከተጠርጣሪው ቤተሰቦች ማስፈራሪያ ይደርሳት ነበር። “ሕይወትሽ እንዲተርፍ ከፈለግሽ ክሱን አቋርጪና እንደግፍሻለን” የሚል። ጉዳዩን በሰማንበት ጊዜ ከተለያዩ የንቅናቄ አጋሮቻችን ጋር በመሆን ለመዓዛ ሕክምናና ከሷ ውጪ ደጋፊ ለሌላቸው ልጆቿ የምንችለውን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል”።

በደረሰባት ጥቃት የተነሳ የአንጀት ፌስቱላ እንዲሁም የጨጓራ መጎዳት አጋጥሟት የነበረ ሲሆን ‘ኦ’ የደም ዓይነት በቶሎ ባለመገኘቱ የፈሰሳትን ደም ለመተካት ከባድም ነበር። የመዓዛ የጤና ጉዳይ እጅግ አሳሳቢና ብዙ ክትትልና ዕርዳታ የሚሻ ነበር። መዓዛ በደረሰባት ጥቃት ምክንያት ስትሰቃይ ቆይታ ባለፈው እሁድ ሕይወቷ አልፏል።

መዓዛ የሞት አፋፍ ላይ ሳለች አዲስ ፀባይ ማሳየት ጀምራ “ቢታሰር ለኔ ምን ይጠቅመኛል?” ስትል የነበረውን ሰው ደጋግማ ፍርሐት በተመላበት ሁኔታ “እባካችሁ ይታሰር፣ እሱን አሳስሩት ሌላው ይቅር” ስትል እንደነበር ቤተሰቦቿና ለጥየቃ የሔዱት ጓደኞቻችን ነግረውናል።

የመዓዛ ቤተሰቦች “የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲኖር እኔ እደውላለሁ” ያላቸውን የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ፖሊስ መርማሪ ዮናስ ሳህሌን አምነው ሲጠባበቁ የቆዩ ቢሆንም ዝምታው ሲበዛባቸው ደውለው “ምን አደረጋችሁ?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ከብዙ ማድበስበስና ነገ ዛሬ በኋላ ተጠርጣሪው ለሕክምና በወጣ ጊዜ ከሌሎች ተጠርጣሪ ታሳሪዎች ጋር እንዳመለጠ እና ይህም ከሆነ መቆየቱ ተነግሯቸዋል። ማምለጡን በሚገባ እያወቁ ለመዓዛና ቤተሰቦችዋም ምንም ጥበቃ ሳይደረግ ቀናት ማለፋቸውን ሰምተናል። ተጠርጣሪው ጌታቸው ዓለምፀሃይ የሕግ ትምህርት ያለውና የተለያዩ ሰበቦችን በመጠየቀም ከፍትሕ ተጠያቂነት ሊያመልጥ የሞከረ ሲሆን ፖሊስም እነሆ “ጠፋብኝ” ብሎ መልስ በመስጠት ላይ ይገኛል። ትናንት ባገኘነው መልስ ፖሊስ እንዳረጋገጠው ተጠርጣሪው የጠፋው የካቲት 19 ነው።”

የተለያዩ ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይህ ታሪክ ሲወጣ ከገለጹት ቁጣና “ሴቶች በዚህ አገር ምን ዋስትና አለን?” ከሚለው ሥጋትና ፍርሐት ውጪ መንግሥትም ይሁን የአዲስ አበባ ፖሊስ በይፋ ያወጡት መግለጫ የለም። የመዓዛ አጥቂ ሲያመልጥ ለአንድ ወር አካባቢ ከታሠረ በኋላ ቢሆንም ክስ እንዳልተመሠረተበት ቤተሰቦቿ ከፖሊስ ተረድተው ነበር። ለምን ሲባል “በምን እንደምንከሰው ግራ ገባን፣ ቆይ የእስዋ ሁኔታ እስኪለይ እንጠብቅ” የሚል መልስ ነበር የተሰጠው። ሐኪም ሲያመልጥ ሊጠብቀው ይገባ የነበረው ፖሊስም ተይዞ በኋላ በዋስ ተለቋል። እንግዲህ ስለ ሴቶች ሕይወት የመንግሥት ምላሽ ይህን የሚመስል ነው። ሌላው ቀርቶ ሰባት ሴቶች በስድስት ወራት በጥቃት ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ የሴቶችን ጉዳይ ቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ መግለጫ ለማውጣት ዝም ያለው ለምን ይሆን የሚለው ግራ የሚገባ ነው።

ሴቶችን ከጥቃት የመጠበቅ ነገር ለመንግሥት አሁንም ቀዳሚ አጀንዳ አይመስልም። በተለይ የቅርባቸው በሚባሉ ሰዎች ጥቃት በሚደርስ ወቅት ተጎጂዋን ጥፋተኛ ለማድረግ የመሞከር በዚህም የማሸማቀቅ ነገር ይታያል። ይህም ብዙዎቹ የቤት ውስጥ ጥቃቶች ሪፖርት እንዳይደረጉ ምክንያት ይሆናል። አጥቂዎች ሳይቀሩ ሚዲያና መድረክ ተሰጥቷቸው የተለመደውን ሴቶችን በአሉታዊ መልኩ የመሳልና የፈጠራ ታሪክ የማባዛት ተግባር እንዲከውኑ ይፈቀድላቸዋል። ይህም በሕይወት ላሉ ለተጎጂዎቹ ካልሆነም ለቤተሰብና ለልጆቻቸው ትልቅ የሥነ ልቦና ጠባሳ ትቶ ያልፋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንዳሉት ሴቶችን ያልያዘ ወይም ያላሳተፈ ዕድገት ሁለንተናዊ ሊሆን አይችልም። ጥናቶች እንዳረጋገጡት ደግሞ ለሴቶች ተሳትፎና ሙሉ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ከሚሆኑ ምክንያቶች አንዱ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው። በሞት የሚደመደመው ጥቃት እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ጥቃቶች ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊና አዕምሮአዊ ጤናን የሚጎዱ ናቸው። በ2016 የወጣው የሕዝብና ጤና ጥናት ግምት እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሴቶች 23 በመቶው ቢያንስ በሕይወታቸው አንድ ጊዜ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ዐሥር በመቶው ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፥ ካገቡ ሴቶች 34 በመቶው በባሎቻቸው ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። ይኸው ጥናት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ሪፖርት የመደረግ ዕድሉ 66 በመቶ መሆኑን አስቀምጧል።

ጽሑፌን በወቀሳ ከመደምደሜ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ ክፍል ኢትዮጵያ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቀጥል ምክንያት የሆኑትና ከመፍትሔውም ሊሠራባቸው የሚገባውን ጉዳዮች ልጠቁም። የመጀመሪያው ምክንያት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋማት ደረጃ ሳይቀር በሴቶች ላይ ያለው አግላይ አመለካከት ሲሆን፥ ኹለተኛው በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ክፍተት ነው። ያሉት የሕግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚፈፀምባቸውን ሁኔታዎች በሙሉና በአግባቡ የማያካትቱ ናቸው።

ሕግ ባለባቸው እንደ አስገድዶ መድፈር ያሉ ጥቃቶች ላይ አፈፃፀሙ የተለያየና በአስፈፃሚው ላይ የተንጠለጠለ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ ጥቃትን በአግባቡ የሚዳስስ ሕግም የላትም። ማንኛዋም ሴት ከጥቃት የተጠበቀ ሕይወት እንዲኖራት፣ ለአገር ዕድገትም የበኩሏን አስተዋፅዖ ማበርከት እንድትችል እነኝህ ጉዳዮች መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል። ከሁሉም በላይ ከስታትስቲክስና ከፖለቲካ ማኒፌስቶ ማሣመሪያ በዘለለ መንግሥት የሴቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሊሠራ ይገባል። ከላይ እንደተጠቀሰው ታሪክ ፖሊስ ጉዳዩን ሲፈፅም በካሜራና በሰው ምስክር የተያዘ ወንጀለኛ ክስ ሳይመሠርት ከወር በላይ ሲያስቀምጥ ከዚያም በንዝህላልነት ሲያስመልጥ፣ ማምለጡንም በወቅቱ ሳያሳውቅ ሲቀር ፍትሕ እንዳስተጓጎለ ታውቆ ሊጠየቅ ይገባል። ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ሲመጡም በአግባቡ እንዲያስተናግድ ምንሽ ነው የሚለውን ጥያቄና ፍርድ ትቶ ከተጠቂና ከፍትሕ ጎን እንዲቆም መሠራት ያለበት ሁሉ ሊሠራ ይገባል። ሴቶችን የሚመለከት ሥራ ሊሠሩ የተቋቋሙ ተቋማትም ምን ሠሩ የሚለው ሊፈተሽ አደረጃጀታቸውም ሥራውን የማያሳልጥ ከሆነ እንደገና ሊዋቀሩ የግድ ይላል። በአጠቃላይ የሴቶች ጥቃት በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here