ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጥቃትና ዘረፋ እየደረሰባቸው ነው

0
699

የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ማኅበራት በመዳረሻ ቦታዎች ላይ ጥቃትና ዘረፋ እየደረሰባቸው እንደሆነ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መጋቢት 24 ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ አስታወቁ። በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ የማኅበራቱ ተወካዮች በአንዳንድ ክልል ውስጥ ያሉ የጎበዝ አለቆች አላሠራ እንዳሏቸው፣ ያለአግባብ ገንዘብ እንዲከፍሉ እንደሚደረጉ፣ ሹፌሮች እንደሚደበደቡ እና ትራፊኮችም ያለአግባብ እንደሚያስቆሟቸው ተናግረዋል።

እንደማሳያም አፋር ላይ ሥጋት ፈጥሮብናል ያሉት የማኅበራቱ ተወካዮች ሰው ገጭታችኋል በሚል ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ ሺሕ ብር እንዲከፍሉ መደረጋቸውን በሚመለከት ለፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሎጀስቲክስ አሠራር 90 በመቶ የአገሪቱ ወጪ እና ገቢ የሚንቀሳቀሰው በጭነት ተሽከርካሪ እንደሆነ በመድረኩ ላይ የገለጹት የመድህን ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ማኅበር ተወካይ ወርቅነህ ዳኘው፥ የጉዞ ደህንነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታና በቅንጅት ባለመሰራቱ 30 በመቶ የሚሆነው ሥራ በተፈለገው መጠንና ፍጥነት እየተሠራ እንዳልሆነም አክለዋል።

በመድረኩ ላይ እንደ ተግዳሮት ከተጠቀሱት መካከል የደላላ ጣልቃ ገብነት፣ የአውራጅና ጫኚዎች የሚፈጠሩ አተካሮዎች/ችግሮችና መዘግየቶች ፣ የኢትዮ ጅቡቲ መንገድ ብልሽትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ችግር ይገኙበታል።
በተጨማሪም የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ ከማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ጋር በመሆን ረቂቁን ለሚንስቴሩ ማቅረቡን ያስታወቀው ተቋሙ፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ ኬላዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በጅምር ደረጃ እንዳለ አሳውቋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር በክልሎች ለተፈጠሩት ችግሮች የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ሥራዎቻቸውን በአግባቡ እና በፍጥነት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበው፥ በክልል መዳረሻ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ሸራ አትፈቱም፣ ብር ክፈሉ እያሉ የሚያስቸግሩ አካላት እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባም አስታውቀዋል።

የደኅንነት ሥጋቱንም በተመለከተም ሚኒስተር ዴኤታዋ ከክልሎች ጋር ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው፥ ችግሮቹን ለመቅረፍ ጊዜ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here