የሴቶች ሰቆቃ በማረሚያ ቤቶች

0
961

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የሴት ታራሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያሳያሉ። በመላው አገሪቱ ከሚገኙት 200 ሺሕ ታራሚዎች ውስጥም 3 ነጥብ 7 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ በትዳር አጋሮቻቸው፣ በፍቅር ጓደኞቻቸው፣ ወይም በጥቃት አድራሾቻው ላይ ራስን በመከላከል ወቅት ጉዳት ያደረሱ ናቸው። የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በአሰላ፣ አምቦ፣ አዳማ እና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶች ላይ ባካሔደው ጥናት 40 በመቶ የሚሆኑት ሴት ጥፋተኞች ድርጊቱን የፈጸሙት ራሳቸውን ለመከላከል መሆኑን ያትታል።

ሴት ታራሚዎች በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ወንድ ታራሚዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች በተጨማሪ የጤና እና የንፅሕና ጥበቃ ችግሮች፣ በተጣበበ ቦታ ተጨናንቆ የመታሰር እና የተለያዩ ችግሮች የሚያጋጥሟቸው ሲሆን ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ ልጆቻቸውን ይዘው መታሰራቸው ችግራቸውን ያባብሰዋል።

ባልተለመዱ ድምፆች እና አብዝተው በሚሰሙት የማረሚያ ፖሊሶች ኮቴዎች በታጀበው ጊቢ ውስጥ ብርቱካናማ ዩኒፎርም የለበሱት የቃሊቲ ማረሚያ ሴት ታራሚዎች ከክፍላቸው ፊት ለፊት ወዳለው ሜዳ ላይ በዝምታ እየተመለከቱ ይተክዛሉ። ደብረዘይት መንገድ ላይ የሚገኘው ይህ ማረሚያ ቤት በ2002 ላይ ነበር የሴቶች ግቢውን 1 ሺሕ ታራሚዎችን እንዲያቆይ ታስቦ የተቋቋመው።

በማረሚያው በአሁኑ ወቅት 345 ሴት ታራሚዎች የሚገኙ ሲሆን 424 የሚሆኑት ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ በተሰጡ የተለያዩ ምህረቶች እና ይቅርታ ተለቀዋል። ታዲያ በሴቶች ማረሚያ ግቢ ውስጥ ወንድ ታራሚዎችም የሚቆዩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ጠባቂዎቻቸውም ወንዶች ናቸው።

በማረሚያው ውስጥ ልጆቻቸውን ከማሳደግ ጀምሮ እስከ ፈታኙ የፍትሕ ጥያቄ ድረስ ያለው ውጣ ውረድ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ሕይወት ለሴት ታራሚዎች አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል። እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሳይፈረድባቸው መቆየት እንዳለ ሆኖ፥ ፀጋ ኃይሌን ጨምሮ አብዛኞቹ ታራሚዎች ከእስር ሲፈቱ የሚገቡበት ቤት እና ኑሮም የላቸውም።

ፀጋ ባለፉት 6 ወራት ሳይፈረድባት በቃሊቲ የሴቶች ማረሚያ ውስጥ ከአንድ ዓመት ልጇ ጋር ቆይታለች። ኹለተኛ ልጇን ከተገላገለች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነበር ደረቅ ቼክ በመስጠት ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር የዋለችው።

“ፍርድ ቤት በሔድን ቁጥር ዳኞቹ ለአንድ ወር ቀጠሮ ይሰጣሉ። የመጀመሪያ ልጄ በኪራይ ቤት ነው ጥየው የወጣሁት ቀጠሮ በተሰጠ ቁጥርም የእሱ ጉዳይ ያሳስበኛል” የምትለው ፀጋ ፖሊስ በተጠረጠረችበት ወንጀል ላይ እስካሁን ማስረጃ ማምጣት አለመቻሉን ትናገራለች። “ለፍርድ ቤቱ እና ለማረሚያ ቤት አስተዳደር ደጋግሜ ቅሬታዬን ባሰማም መልስ ሳጣ ለሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር እና ለተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች ችግሬን አስረድቼ እንደሚረዱኝ ቃል ቢገቡም እስከአሁን ፍትሕ አላገኘሁም” ብላለች።

እንደፀጋ አስተያየት አብዛኛው መሰረታዊ ፍላጎቶች ቢሟሉም ዋናው እና መሰረታዊው ጥያቄ ግን ፍትሕ ማግኘት ላይ ነው ትላለች። አንዳንድ ታራሚዎች ውጪ ላይ ምንም ሕይወት ስለሌላቸው፥ የማረሚያው ሕይወት ይሻላል ብለው እንደሚያምኑም ትናገራለች። ከውሃ እጥረት ባሻገር የማረሚያው ጠባቂዎች ሕመም ሲያጋጥማቸው ወደ ሕክምና ቦታ ለመሔድ እንደማይፈቅዱላቸው እና ሥልክ ለመደወልም እንደሚከለከሉ ትናገራለች።

“አንድ ቀን ከፍርድ ቤት ስመለስ አንድ ሴት ጠባቂ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለማምለጥ ሞክሬ እንደነበር ነግራቸው ክፉኛ ተደበደብኩ። ከዛ በኋላም ወደ ፍርድ ቤት ተወስጄ አላውቅም፣ እንዴት ነው ሕፃን ልጄን ጥዬ የማመልጠው?” በማለት ትጠይቃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ የእስረኞች የሰብኣዊ መብት አያያዝ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል። ነገር ግን የሴት ታራሚዎች ጉዳይ እንብዛም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም። በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚልም አንዳንዶቹ በአስፈሪ የሚስጢር እስር ቤቶች ተይዘው ቆይተዋል።

የፌደራሉ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በሥሩ የቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ፣ ሸዋ ሮቢት፣ እና ድሬ ዳዋ ማረሚያዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን ይፋዊ ያልሆኑት ደዴሳ፣ ቢር ሸለቆ፣ ጦላይ፣ ሆርማት፣ ብላቴ፣ ታጠቅ፣ ሆለታ እና ሰንቀሌ ማቆያ ጣቢያዎችም ይገኙበታል።

እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች እና የአፍሪካ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት የሴቶች ማረሚያ ቤቶች መቆያ ክፍሎች ከወንዶችም እጅግ የጠበቡ እና አንዳንዶቹም ከመጥበባቸው የተነሳ አንድ ሴት ከተቀመጠች በኋላ እግር የማያዘረጋም ነው ይላሉ። ማቆያዎቹም የአካል ጉዳተኞችን፣ ነፍሰ ጡሮችን፣ የሚያጠቡ እና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ታራሚዎች ሁኔታም ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ እና ከእርግዝና በፊት እንዲሁም በኋላ ያሉ ጥንቃቄዎችን ከግምት ሳያስገቡ የተሰሩ መሆናቸው ይነገራል።

በኃይሉ ወልደዮሐንስ (የአለማቀፍ መብት የጤና መብቶች ተሟጋች) ‘Reforming Prison Policy to Improve Women-Specific Health and Sanitary Care Conditions’ በሚለው ጥናቱ ኢትዮጵያ የሴቶችን የጤና መብቶች የሚመለከቱ ፖሊሲ እና ሕጎች እንደሌሏት እንዲሁም ለሴት ታራሚዎችም በእኩልነት እነዚህ መብቶች እንዳልተረጋገጡ ያስረዳል። ሴቶች በእርግዝና ወቅት ወይም በወሊድ ወቅት ስለሚያገኙአቸው የጤና ግልጋሎቶች ካልሆነ በስተቀር ሴቶች ስላሏቸው የጤና መብቶች የሚደነግጉ አስገዳጅ ሰነዶች አለመኖራቸውንም ይገልፃል።

በኃይሉ ጨምሮም ከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የሆኑትን የአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ታራሚዎች መገለል እና ከፍተኛ ፍርሃት ስለሚኖራቸው የደረሰባቸውን ጥቃት ደፍረው እንደማይናገሩም ይገልፃል። የማረሚያ ቤቶች ፖሊሲዎችም ይህን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት አልተቀረፁም ሲል ይሞግታል።

በኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር የተሠራው ጥናት እንደሚያመለክተው በጋብቻ ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመመከት ለሚወሰዱ ራስን የመከላከል ድርጊቶች አብዛኛውን የሴት ጥፋተኞችን ቁጥር ይይዛል። ከጥቂት የከተማ አካባቢዎች በስተቀር አብዛኞቹ ሴቶች በቂ የሕህግ ምክር እና ድጋፍ የማያገኙ ሲሆን ይህ ለወንጀል ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተለይ ደግሞ በንብረት ክርክሮች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

ለረጅም ዓመታት ለሴቶች መብቶች መከራከር እና ሴቶችን መርዳት እጅግ ከባድ እንዲሆን ያደረገው የበጎ አድጎት እና ማኅበራት አዋጅ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል። እንደ ʻሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ሂውማን ራይትስʼ መረጃ ከሆነ 90 በመቶ የሚሆኑት የበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጁ ከወጣ በኋላ ከኢትዮጵያ ጥለው የወጡ ሲሆን የቀሩትም ከአቅማቸው 85 በመቶ ባነሰ ሲሰሩ ነበር። ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቀሰው 2000 ላይ ለ17357 ሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ የሰጠው እና ሠፋፊ ንቅናቄዎችን ሲያካሒድ የነበረው የሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር አንዱ እንደሆነ የማኅበሩ ፕሮጀክት ኃላፊ ወንድሜነህ ለማ ይናገራሉ። መንግሥት የሕጉን መውጣት ተከትሎ የማኅበሩን የባንክ አካውንት በመዝጋቱ ላለፉት 10 ዓመታት እንብዛም እንቅስቃሴዎችን ሳያደርግ መቆየቱንም ይጠቅሳል።

ይህንን ሕግ ያሻሻለው አዲሱ አዋጅ ከውጪ አገር የሚገኙ የፋይናንስ አማራጮችን በመፍቀዱ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ቅርንጫፍ ለመክፈት ማሰቡንም ይናገራሉ።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አስተዳደር ወደፊት ከመጣ ጀምሮ ሲካሔዱ ከነበሩ ከፍተኛ የሕግ ማሻሻያዎችም መካከል ይህንን አዋጅ በማሻሻል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሰረታዊ የሚባሉ ለውጦችን ካካሄደ በኋላ አቃጁ በሕግ አውጪው ፀድቋል። ይህም ለሴት የሕግ ታራሚዎች ለሚሰጡ የሕግ ድጋፎች መጠናከር የበኩሉን ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

ወንድሜነህ እንደሚሉትም በቀን ቢያንስ 41 ሴቶች ለማኅበሩ የማረሚያ ቤቱ አያያዝ እና ሁኔታ እጅግ ከባድ እንደሆነባቸው ሪፖርት ያደርጋሉ። “ሴቶች መጀመሪያውኑም ወደ ማረሚያ ቤቶች እንዳይሔዱ ጠንካራ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል፣ አንዴ ወንጀል እንዲፈፅሙ ተገፍተው ወደ ማረሚያ ቤት ከገቡ በኋላ የረባ እና ሕይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያመጣ ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።”

ሴቶችን ወደ እስር ከሚገፉት ዋና ዋና ማነቆዎች መካከልም የቤት ውስጥ ጥቃቶች እና የገቢ ጥገኝነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የተለያዩ ዓይነት አካለዊ እና ፆታዊ ጥቃቶች ከሚያጋጥማቸው ሴቶች መካከልም 32 በመቶ የሆኑት ብቻ ጉዳዩን ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ 16 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ በራሳቸው ሐብት እና ንብረትን ያፈራሉ። የፍትሐ ብሔር ሕጉ ሴቶች የልጅ ቀለብን በተመለከተ ከጋብቻ ሳይወጡ መጠየቅ የማይችሉ ሲሆን ዋና ዋና የሚባሉት ማነቆዎችም ከእነዚህ የሚቀዱ እንደሆነ ወንድሜነህ ይናገራል። ሴቶች ብዙ ጊዜ መብቶቻቸውን እንዲያውቁ ስለማይደረግ በተለይ በጋብቻ ውስጥ ከፍተኛ ችግሮች ይደርስባቸዋል። ወንድሜነህ በማረሚያ ቤቶችም በወሊድ ወቅት እና በአሳሳቢ ሕመም ወቅቶችም የሚጠቀሙበት አንቡላንስ ስለሌ ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ማረሚያ ቤቶች ለወንዶች ተብለው የተገነቡ በመሆኑ አብዛኞቹም የመከላከያ መጋዘን እና የአስተዳደራዊ መሥሪያ ቤቶች የነበሩም ናቸው። የመጀመሪያው እና በ1944 (እ.ኤ.አ) የፀደቀው የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ በግልፅ እንደሚደነግገው ሴት ታራሚዎች በሴት ፖሊሶች ብቻ መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራል።

በደርግ ዘመን በአብዛኛው ማረሚያዎች ወንድ ዘቦች በቀጥታ ሴት ታራሚዎችን ይቆጣጠሩ የነበረ ሲሆን በተለይም መንግሥትን ተቃዋሚ ለነበሩ ሴት ታራሚዎች ሁኔታው እጅግ አሰቃቂ እንደነበረም ታሪክ ያስረዳል። በምርመራ ወቅት እና ለተለያዩ ቅጣቶችም ሴቶች በተለያዩ የማረሚያ ቤት ኀላፊዎች እና ጠባቂዎቻቸው ይደፈሩ እንደነበር እና ጥቃቶች እንደሚፈፀሙባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ወታደራዊው መንግሥት ከወደቀ በኋላም የሴት ታራሚዎች ሰብኣዊ መብቶች መከበር እና አግባብ ባለው ማረሚያ ቤቶች ሴቶችን የማቆየቱን ጉዳይ ጀርባውን የሰጠው መንግሥት አሁን አሁን በተለይ በፖለቲካ እስረኞቹ ላይ ሲፈፀሙ የነበሩ አሰቃቂ ጥቃቶችን ይፋ በማውጣት መለወጥ የጀመረ ይመስላል። በዚህም የተለያዩ የፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ የነበሩ እንዲሁም በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ባልደረባ የነበሩ ግለሰቦችን መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደ ሕግ ማቅረቡም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የዞን ዘጠኝ አባል የነበረቸው እና ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ከመላኳ በፊት በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው የአዲስ አበባ የወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት ታስራ የነበረቸው ማሕሌት ቃሊቲ ከማዕከላዊ ጋር ሲነፃፀር ገነት ማለት ነው ትላለች። ማዕከላዊ ከአንድ ዓመት በፊት ከመዘጋቱ ቀደም ብሎ በእውን ቀርቶ በሕልም የማይታሰቡ ጥቃቶች ሲፈፀሙበት እንደነበር ምስክርነቷን ትሰጣለች።

“ቃሊቲ ከባድ የሚባለው ቅጣት ለብቻህ ተገለህ መታሰር ወይም ቤተሰቦችህ እንዳይጠይቁህ ማድረግ ነው። ማዕከላዊ ግን በጣም ጠባብ፣ ቀዝቃዛ እና ጨለማ ክፍል ውስጥ አስረውኝ የነበረ ሲሆን የመርማሪዎቹ ኮቴም ከላይኛው ወለል ይሰማኝ ነበር። እኔ በነበርኩበት ወቅትም ወደ 30 የሚጠጉ ሴት ታራሚዎች ነበሩ። በምሽት ነበር ምርመራ የሚያካሔዱት፣ አብዛኛው ሴትም የማሰቃት ድርጊት ተፈፅሞበታል።

ማዕከላዊ በውስጡ ሳይቤሪያ፣ ሸራተን እና ጣውላ ቤት የሚባሉ ክፍሎች የሚገኙበት እና በተለይም በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ዜጎች የሚታሰሩበት ነበር። እስካሁን አጨቃጫቂ በሆነ መንገድ ቢሆንም መንግሥት ማአካለዊን ጨምሮ በተለያዩ ድብቅ እስር ቤቶች ሲፈፀሙ የነበረውን ድርጊት ይፋ ቢያወጣም ሴት እስረኞች ላይ የደረሱትን ጥቃቶችን ግን በዝምታ አልፏቸዋል።
ምንም እንኳን በወንዶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ብቻ ጎልተው ቢወጡም ብዙ ሴቶች በቆሻሻ በተሞሉ ቤቶች ውስጥ ድንጋይ ላይ እንዲተኙ ይደረግ ነበር።

“ይቅር እና ሴት መሆኔን ሰው እንደሆንኩ እንኳን የተጠራጠርኩበት ቀን ነበረ” ስትል ማንነቷ እንዲጠቀስ ያልፈቀደችው እና መገናኛ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታስራ የነበረች ሴት “ሴቶች የአእምሮ ሕመም ካለበት ሰው ጋር ታስረው የመደፈር አደጋ እንደደረሰባቸውም ሰምቻለሁ” ተናግራለች።

ምንም እንኳን ማንም ሰው በቁጥጥር ሥር በዋለ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ቢልም ብዙ ሴቶች ለወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንደቆዩ ይናገራሉ። ማሕሌት እንደምትናገረውም ምንም ፋይል ሳይከፈትባቸው ለወራት በማረሚያ ውስጥ መቆየታቸውን ትናገራለች። “የሽብር ድርጊት ለመፈፀም በማሴር ነበር የተጠረጠርነው፤ እናም በወቅቱ አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፈለግ ቢለፉም ማስረጃ ግን አላገኙም ነበር። በወቅቱ እስከ 40 የሚሆኑ ሴቶች 4 ሜትር በ3 ሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ ይታጎሩ የነበረ ሲሆን ውሃ ቀን ቀን አለማግኘታችን እና ማታ ውሃው ሲመጣ ደግሞ መውጣት ያለመቻላችን እና ወደ ጤና ተቋም ለመሔድ ያለመፈቀዱም ሌላው ራስ ምታት ነበር።

እንደ ማሕሌት ዕይታ የኢትዮጵያ ሕጎች ጡንቻ በትልልቅ ወንጀሎች ላይ ጊዜውን ከማጥፋት ይልቅ በጥቃቅን ወንጀሎች ላይ እንደሚበረታ እና ሴቶች ላይም በተለያዩ መንገድ ጫናው የከበደ ነው።

ማሕሌት አሁን መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እረምጃዎች ሴቶችን የሚያበረታቱ ከመሆናቸውኑም ባሻገር ሴቶችን በተግባር ከርዕሰ ብሔርነት እስከ ተለያዩ ወሳኝ የኀላፊነት ቦታዎች ያመጣ ነው። ከእስር ቤት ሰቆቃ እና ትዝታዎቹ በላይ ይህ ተስፋን የሚፈነጥቅ መልካም ጅማሬ ነው ብላለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here