በአዋሽ የፍተሻ ጣቢያ በጨረር የመፈተሻ ማሽን (የኤሌክትሮኒክስ ካርጎ ስካኒንግ) ለኹለት ወራት ተበላሽቶ በመቆሙ የአገሪቱ ወሳኝ መግቢያ እና መውጫ የሆነው በዚህ ጣቢያ ሥጋት ተፈጥሯል። ማሽኑን በገጠመው የቻይና ድርጅት እና በገቢዎች ሚኒስቴር መካከል በተፈጠረ ያለመግባባት ማሽኖቹ ሳይጠገኑ መቆየታቸውም ታውቋል።
በቅድሚያ የተበላሸው ማሽኑን ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚያገናኘው ገመድ ሲሆን ይህንንም ለመጠገን ወደ አንድ መቶ ሺሕ ብር ለጥገና መጠየቁ ለማሽኑ ያለመጠገን ምክንያት ሆኗል። ማሽኑ ወደ ሥራ ከገቡ አንድ ዓመት የሆናቸው ሲሆን የጨረር ፍተሻው ከመጣ ወዲህ የኬላው ኮንትሮባንድ የመያዝ አቅም መጨመሩንም ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
ማሽኑ ከተገጠሙ በኋላም ከሚይዘው ኮንትሮባንድ ባሻገር “በማሽን እንፈተሻለን” በሚል ፍርሃት ኮንትሮባንዲስቶች ቀድመው ወንጀሉን እንደማይሞክሩትም ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ውስብስብ እና በሰው ፍተሻ የማይያዙ እቃዎችንም ማሽኑ ሲይዝ የቆየ ሲሆን በተለይም በመኪና አካል ውስጥ ተበይደው የሚያለፉ እና እንደወርቅ ያሉ ጥቃቅን እቃዎችንም በመለየት ሚናው ትልቅ እንደነበረም ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
የአዋሽ ፍተሻ ጣቢያ ከፍተኛ የሆነ የጭነት መኪኖች ሰልፍ የሚታይበትም ሲሆን ማሽኑ ሰዓታትን፣ አንዳንዴም እስከ አንድ ቀን የሚፈጅ ሲሆን በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፍም ከፍተኛ ማነቆ ከሚባሉት መካከል ይህ በኬላዎች ያለው የፍተሻ ስርዓት ነው። የጨረር መፈተሻው ይህንን ሰልፍ በማስቀረት ትልቅ ሚናም ነበረው።
በቅርቡ በተደረገ ምርመራ ዋናው የማሽኑ አካል የሆነው ʻቦርድʼ እና ሌሎች እቃዎች መበላሸታቸውም በቅርቡ እንደታወቀ የጣቢያው ተወካይ የሆኑት መሐመድ ኤድሪስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የጣቢያው ሰራተኞች ኮንተሮባንዶችን በመያዝ ላይ እንደሆኑ የሚናገሩት መሐመድ ዋና መሥሪያ ቤቱም እርምጃ እስከሚወስድ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011


