የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወር ጥሞና ያስፈልገዋል

0
789

በኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ፥ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት በምጣኔ ሀብት በኩል ሊወስዳቸው ካሰባቸው እርምጃዎች መካከል አንዱና በአማካሪ ቡድን በማስጠናት ላይ የሚገኘው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ማዘዋወርን በተመለከተ ይገኝበታል። የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) መንግሥት ሽያጩን በጅምላ ከማሰብ ወጥቶና ከአፍሪካ አገራት ተመክሮ በመውሰድ ለሕዝብ የሚጠቅም ውሳኔ እንዲወስን አሳስበዋል።

 

ቴሪ ቡቸል የተባሉ የዓለም ባንክ ተመራማሪ በ2003 (ሁሉም በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ናቸው) በርዕሰ ጉዳዩ ስለጠቀስው ጉዳይ ምርምር አድርገው ነበር። ምንም እንኳን የዓለም ባንክ ከአፍሪካ የመንግሥት ድርጅቶች ሽያጭ ጀርባ በማስፈራራትም በብድር በማባበልም ዋነኛ ተዋናይ ቢሆንም የኚህ ተመራማሪ ጽሁፍ የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት የጥናቱን ውጤት ለዛሬ አቅርቤላችኋለሁ፤ ይህንንም ያደረኩት በኹለት ምክንያት ነው፤

አንደኛ፡ ዛሬ፣ ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በብሩህ ተስፋ ወደዚህ የመንግሥት ድርጅቶች ሽያጭ ሲነጉድ፣ ይህ አካሔድ በ1980ዎቹና 90ዎቹ በአፍሪካ ላይ ያደረሰውን ጉዳት የማያውቁና፣ ካወቁም ግድ የሌለው ስለሚመስል ነው።
ኹለተኛው፡ የዛሬ ወር ገደማ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከሚሠራ ታላቅ ዛምቢያዊ ኢኮኖሚስት ወዳጄና ኬንያ ውስጥ አንድ ራት ላይ ተገናኝተን “እናንተ ሰዎች ስለዚህ ወደ ግል ማዛወር ነገር ዛሬ ገና ነው እንዴ የሰማችሁት? ለምን ከተቀሩ የአፍሪካ አገሮችና በተለይ ከአገሬ ከዛምቢያ አትማሩም?” ያለኝ ነገር አነሳስቶኝ ነው።

ወደ ተመራማሪው ጽሁፍ ልመለስ በ1990 ይህ ድርጅቶችን ከመንግሥት ወደ ግል የማዘዋወሩ ነገር አፍሪካ ውስጥ በጣም የተስፋፋ ጉዳይ ነበር ይላሉ። ሆኖም ግን ኮምቤ ኋይትና ባህታይ በተባሉ ተመራማሪዎች በ1996 ከተካሔደው ጥናት ውጪ አኀዛዊ መረጃዎችን በመጠቀም የተሠራ ጥሩ ጥናት የለም ይላሉ። የቴሪ ቡችስም ዓላማ ይህንን የምርምር ክፍተት ለመሙላት የታለመ ነው። ተመራማሪው ይህንን ምርምራቸውን በሚሠሩበት ወቅት ማለትም በ2003 ደግሞ በመላው አፍሪካ ለዚህ ከመንግሥት ወደ ግል የማዘዋወር ፖሊሲ ከፍተኛ የሕዝብ ጥላቻና ተቃውሞ የነገሠበት ጊዜ ስለነበር የተመራማሪው ዓላማ ሰፋና ጠለቅ ያለ የምርምር ውጤት ለማቅረብ ነው።

ከ1991-2003 ባለው ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ከ2300 በላይ እንደዚህ ዓይነት ከመንግሥት ወደ ግሉ የመንግሥትን ድርጅቶች የማዘዋወር ሽያጭ ተካሒዶ ነበር። ከዚህ ሽያጭም ከ9ኝ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ተገኝቷል። ይህንን ሽያጭ ተከትሎ ይህ ከመንግሥት ወደ ግል ማዘዋወሩ ተግባር ምን ምን ጉዳቶችና ጥቅሞች አፍሪካ ውስጥ አምጥቷል የሚለው የምርምሩ ዋነኛ ጥያቄ የሚከተሉትን መልሶች አግኝቷል።

አንደኛ፥ ይህ ሽያጭ ለመንግሥት በጀት ያመጣው ጠቀሜታ በአንድ ጊዜ ወይም አንድ ዓመት ብቻ እንጂ ዘላቂነት አልነበረውም።

ኹለተኛ፡ ሽያጩን ተከትሎ ብዙ ኩባንያዎች ወዲያውኑ ትርፋማነታቸውና ሽያጫቸው ጨምሯል። ይህ ግን በብዙ ኩባንያዎች በዘላቂነት አልቀጠለም።

ሦስተኛ፥ ይህንን የመንግሥት ድርጅቶች ሽያጭ ተከትሎ ከሥራ መፈናቀል በብርቱ ተስተውሏል።
አራተኛ፥ የውጪ ቀጥተኛ መዋዕለ ነዋይና የአክስዮን ገበያዎች ይህ ነው የሚባል ሚና በዚህ ሽያጭ ላይ አልተጫወቱም፤ ማለትም የሽያጭ ፖሊሲው እነዚህን ዓይነት ካፒታሎችን አልሳበልንም።

አምስተኛ፥ ለሁሉም ተዋንያን እኩል የውድድር ሜዳ ማዘጋጀትና ይህንንም ውድድር የሚመራና የሚቆጣጠር ተቋም ድርጅቶቹ ከመሸጣቸው በፊት የማቋቋሙ ነገር በሁሉም አገሮች የተረሳ ነገር ነበር። ይሄ ደግሞ ጉዳት አምጥቷል።

ስድስተኛ፡ ይህ የመንግሥት ድርጅቶችን የመሸጥ ጉዳይ አዳዲስ የፖለቲካ ልሂቃንና የድርጅቶቹን ገዢዎች ጥምረት በመፍጠር አገሮችን ከፍተኛ የሌብነት ቅሌት ውስጥ አስገብቷቸዋል። ይህም በሽያጩ አካሔድ ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዲጠፋ አድርጓል።
በመጨረሻም ይህ የሽያጭ ሒደት በኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ጥቅም ላይ ጉዳት አምጥቷል፤ ያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ መንግሥታት ቀደም ብለው አላሰቡበትም ነበር። የመንግሥታቱም ዋንኛ ትኩረት ከሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ላይ ነበር። በመሆኑም በኢኮኖሚውና በኅብረተሰቡ ላይ ሊያመጣ ለሚችለው ጉዳት ብዙም ደንታ አልነበራቸውም።

ለማጠቃለል ይህ እንግዲህ ከ2300 በላይ የአፍሪካ መንግሥታት ድርጅቶች ሽያጭ ላይ የተመሰረተ ጥልቅ አኀዛዊ ጥናት እንደሚያሳየው ከመንግሥት ወደ ግል የማዛወሩ ሥራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያየለ ነበር። መንግሥታችንም ሽያጩን በጅምላ ከማሰብ ወጥቶና ከዚህ ታሪክ ተምሮ ለሕዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይሔ የጠላት ወሬ ነው እንዳይባል ደግሞ ጥናቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት አሁን ካልሸጥክ ብሎ የሚያስጨንቀው፥ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ድጋፍ በመስጠት ላይ ያለዉ የዓለም ባንክ መሆኑ ለእሳቸው መከራከሪያ ከፈለጉ ደጋፊያቸው ለእኛ ደግሞ ግርምት ጫሪ ነው።
ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በአ.አ.ዩ. የምጣኔ ሀብት
ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
ag112526@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here