ጊዜ ያለፈባቸው የምግብ ምርቶች ከሸማቾች ማኅበራት ተያዙ

0
652

የአራዳ ክፍለ ከተማ የምግብና መድኀኒት ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ጊዜያቸው ያለፈባቸው በርካታ የምግብ ምርቶችን ከሸማች ማኅበራት መያዙን አስታወቀ። የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም በማሰብ መንግሥት ሸማቾችን በማደራጅት በተመጣጣኝ ዋጋ እቃዎችን በጀምላ እንዲያገኙ ይደረጋል።

ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ከ285 ሺሕ ብር በላይ የሚገመቱ በአቀማመጥ ችግር የተበላሹ በርካታ የጥራጥሬ እህሎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ከሸማቾች ማኅበራት ሱቆችና ከተለያዩ ሆቴሎች መያዛቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ የምግብና መድኀኒት ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ትዕግስት በዳዳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሸማቾች ማኅበራት አቀማመጥ ችግር የነቀዘ ጤፍ፣ አተር ክክ፣ ሶፍት፣ አጃክስ፣ ፓስታ፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ድፍን ምስር፣ መኮረኒ ምስር ክክ እና ሌሎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ጊዜያቸው ያለፈባቸው የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጣፋጭ መጠጦች፣ ውሃ፣ የሺሻ ዕቃ፣ የሕፃናት ብስኩቶች፣ የሴቶች የንፅሕና መጠበቂያ (ሞዴስ)፣ ዳይፐር፣ ኢንዶሚን፣ ፓስታ፣ ጁሶች በተለያዩ የንግድ ቤቶች መያዛቸው ታውቋል። በክፍለ ከተማው ከተያዙት ውስጥ በተለይም የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ ሞዴስ፣ ዳይፐርና የመዋቢያ ዕቃዎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ ሲሸጡ መገኘቱም ተነግሯል።

ደረቅና ፈሳሽ ምግቦቹ ጉዳቱ ከምንም እስከ ከፍተኛ ደረጃ ሊለያይ ይችላል ያሉት ትዕግስት የተመረዘ ምግብ የወሰደ ሰው ምልክቶቹም የሆድ ቁርጠት፣ ማስመረስ፣ ትኩሳት፣ ማዞር እና የማያቋርጥ ተቅማጥ ያጋጥማል ያሉት በየረር አጠቃላይ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አንተነህ ዳኛቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“ደረቅ የተሸገ ፓስታ በአግባቡ ከተያዘ ከ1-2 ዓመት ሳይበላሽ እንደሚቆይና ከጊዜ ብዛት የተነሳ ግን የፈንገስ፣ ሻጋታ ወይም የቀለም ለውጥ ከታየ ለምግብ አገልግሎት ባይውል ይመከራል” በማለት የተናገሩት ዶ/ር አንተነህ፤ “ፈሳሽ ሳሙናዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው እስከ 6 ወር ክዳናቸው ያልተከፈቱ እስከ 1 ዓመት ሊቆዩና ሊያገለግሉ ይችላሉ” ሲሉም አክለዋል።

ክፍለ ከተማው ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ቢሮ ጋር በመሆን የተያዙት ምግብ ነክ የሆኑ እና ያልሆኑ እቃዎች እንዲወገድ እንደሚያደርጉ ትዕግስት ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ዕቃ ሲገዙ የመጠቀሚያ ጊዜ በማየት መግዛት እንዳለባቸውና ሲያጋጥማቸው በአጭር ጽሑፍ 8482 የአዲስ አበባ ምግብና ቁጥጥር ቢሮ በፍጥነት ጥቆማ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ከመስከረም 2011 ጀምሮ በየወረዳዎቹ የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ የነበረ ሲሆን በክፍለ ከተማ ደረጃ በአንድ ወር ውስጥ ምግብ ነክ 1,745 ኪሎ ግራም፣ መጠጥ 678.57 ሊትር፣ ጤና ነክ 231.49 ኪሎ ግራም፣ ጤና ነክ 1173.36 ሊትር ከ1015 ሱቆች መያዛቸውንና ሆቴሎች በከፊል መዘጋታቸውን ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here