የጎንደር ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

0
385

በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ወኃ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች ረቡዕ፣ ግንቦት 13/2011 የተቃውሞ ሰልፍ ማካሔዳቸው ታውቋል። የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት፣ ተማሪዎች ሰልፍ ያካሔዱት በአግባቡ ትምህርት ሳይከታተሉ ፈተና ውሰዱ በመባላቸው ነው።

“የማካካሻ ትምህርት ሳይሰጠን እንዴት እንፈተናለን” የሚል ጥያቄ ያዘለው የተማሪዎች ሰልፍ፣ በመከላከያ ሠራዊት መበተኑን እነዚሁ የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። የዓይን እማኞች ይህን ይበሉ እንጂ፤ የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቡድን መሪ ሥዩም ታደሰ ግን ተማሪዎቹ ሰልፍ የወጡት የማካካሻ ትምህርት ሳይማሩ ቀርተው ሳይሆን ተፈናቅለው የነበሩ መምህራን ወደ ትምህርት ቤቱ ዘግይተው መምጣታቸውን በመቃወም ነው ሲሉ ለጀርመን ድምጽ አስታውቀዋል።

“ፈተና ተቀመጥን በሚል አይደለም። ወጥተው የነበሩ መምህራን አኹን ባለቀ ሰዓት መጥተው እነሱ አያስተምሩንም በሚል ነው እንጂ ማካካሻ ምናምን የሚል ነገር አይደለም። አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጎ፤ ትምህርታቸውን በበቂ ኹኔታ መሸፈን የሚገባቸው ነገሮች ተሸፍነዋል። ተማሪው እንዲሰበሰብ ተደርጎ፤ ውይይት ተካሒዶ ነው የተበተነው እንጂ መከላከያ አልበተነውም” ሲሉ አስተባብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here