ንግድ ባንክ ለሠራተኞቹ የኑሮ ውድነት አበል መክፈል ሊጀምር ነው

0
651
  • በከተሞች ላሉ 15 በመቶ የኑሮ ውድነት አበል እና እስከ 10 በመቶ የበርሃ አበል ጭማሪ መደረጉ ታውቋል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለረጅም ዓመታት ሳይተገበር የቆየውን የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ሊሰጥ የተቀረፀው 15 በመቶ አበል መተግበር የተጀመረ ሲሆን የበረሃ አበል ላይም ጭማሬ መደረጉን በግንቦት 13/2011 የባንኩ ፕሬዘዳንት ባጫ ጊና በጻፉት ደብዳቤ (ሰርኩላር) አስታውቀዋል። ከግንቦት 7/2011 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆኑ የተነገሩት እኚህ ጥቅማ ጥቅሞች የባንኩን ምርታማነት ለማሻሻል ታስበው ተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባንኩ አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ለሚሠሩ ሠራተኞቹ ከ700 እስከ 1500 አካባቢ የሚደርስ ክፍያ የሚጨምር እንደሆነ የባንኩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከወራት በፊት የድርጅቱ ሠራተኞች በተደጋጋሚ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ነበረ ሲሆን በተጨማሪም ከሥራ ገበታ ያለአግባባ መነሳት፣ የዕድገት ጥያቄዎች እና የሥራ ድርሻ ክፍፍል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ሲነሱም ነበር። ቁጥራቸው ወደ 2 ሺሕ 722 የሚጠጉ ሠራተኞች የሥራ እርከን ጭማሪ አንስተው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 700 የሚሆኑት ምላሽ ሲገኙ ቀሪዎቹ ግን በጥያቄያቸው ገፍተውበት ነበር።

በመጨረሻም የባንኩ የሠራተኞች ማኅበር በመሚመራው ጥያቄ የሥራ ማቆም አድማ ቀነ ቀጠሮ ሠጥተው የነበረ ሲሆን የባንኩ ማኔጅመንት ሁኔታዎቹን ለማሻሻል ቃል በመግባታቸው መቅረቱ ይታወቃል።

ባንኩ እስከዛሬ የኑሮ ውድነት አበል አያስፈልግም በማለት የበረሃ አበል ብቻ ይከፍል የነበረ ሲሆን አሁን ግን አበሉ የሚያስፈለግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል በማለት ለመተግበር ማሰቡ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ኀይል ቀጣሪ ከሚባሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ንግድ ባንከ ከ33 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን በማሠልጠን ያስተዳድራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here