ቡና ላኪዎች በቶን እስከ 700 ሺሕ ብር ይከስራሉ

0
737

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ወደ ውጭ ከሚልኩት ቡና ውስጥ በቶን እስከ 700 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከስሩ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ። በዓለም ዐቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ መውረዱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የቡና ምርት ላይ ከፍተኛ ጥላ ማጥላቱን የሚገልጸው ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

ከኹለት ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ የመጣውን የዓለም ዐቀፍ የቡና ዋጋ ተከትሎ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ የማምረቻ ዋጋውን በማይሸፍን ደረጃ የአንድ ፓውንድ የቡና ዋጋ ከአንድ ዶላር በታች እየተሸጠ መሆኑን የባለሥልጣኑ ሪፖርት ያመላክታል። ይህንኑ በማጠናከር፣ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ዐቀፍ ገበያ የመደራደር አቅም ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ዋጋ በሚቆረጥለት ወቅት ከአንድ ቶን እስከ 3 መቶ ዶላር ድረስ በመክሰር እንደሚሸጥ አንድ ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሎጅስቲክ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ባለሥልጣኑ ጨምሮ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች በዓለም ዐቀፍ ገበያ ከስረው ከመሸጣቸውም በላይ ቡናው ከመሐል አገር ወደ ጅቡቲ በሚጓጓዝበት ወቅትም ጭነቱ ተከፍቶ ስርቆቶች እንደሚከናወኑ እና እስከ 50 ኬሻ ቡና እንደሚሰረቅም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የ2011 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት እንዳስረዳው በዘጠኝ ወር ውስጥ 191 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ለማቅረብ እና 700 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታስቦ እንደነበር አስረድቷል። ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ በዘጠኝ ወር ውስጥ 151 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጪ ልኮ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በመሰብሰብ ዕቅዱን 71 በመቶ ብቻ ማሳካቱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ ለዚህ እንደምክንያት የሚያስቀምጡት የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም ዐቀፍ ዋጋው ይልቅ አገር ውስጥ መሸጫ ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ ከምርት ገበያ የሚወጡት ቡናዎች ተመልሰው አገር ውስጥ ለሽያጭ በመቅረባቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስንታየሁ ግርማ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት መረጃ መሠረት በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና መጠን በተጓዳኝ ቅመማ ቅመም ምርት በእጅጉ መቀነሱን አስረድተዋል። ይህንም ሲያብራሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2.1ሽሕ ቶን ቅመማ ቅመሞችን ወደ ውጪ ለመላክ እና 4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ የተሠማሩ ባለኀብቶች ተረጋግተው ወደ ሥራ መግባት ባለመቻላቸው ከታሰበው በታች አፈፃፀም እንዲታይ እንደተደረገ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እንደ ስንታየሁ መረጃ በዘጠኝ ወር ውስጥ ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 3 ሺሕ ቶን ቅመማ ቅመም ወደ ውጭ የተላከ ሲሆን ከዚህም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here