ንግድ ባንክ በ28 ሺሕ ሠራተኞቹ ክስ ሊመሰረትበት ነው

0
721

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ከድርጅቱ ጋር ባላቸው የኅብረት ስምምነት መሰረት የሥራ ሰዓት እየተከበረ አይደለም እና የድርጅቱ የሥራ እርከን ደረጃዎች እየተጣሱ ነው በሚል ክስ ለመመስረት ዝግጅት መጠናቀቁ ታወቀ። የሠራተኞች ማኅበሩ ባሳለፍነው ሳምንት ጠበቃ የቀጠረ ሲሆን በቅርቡም በባንኩ ላይ ክስ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።

ድርጅቱ ከሠራተኞቹ ጋር በፈጸመው የኅብረት ስምምነት ውል መሰረት በሳምንት 41 ሰዓት የሥራ ሰአት እንዲሆን የተወሰነ ቢሆንም ሠራተኞቹ ግን ቅዳሜ ከሰዓትን በመሥራታቸው ምክንያት በሳምንት የሚሠሩት ሰዓት ወደ 46 ሰዓት ከፍ እንደሚል እና ይህም ለክሱ ምክንያት መሆኑን የድርጅቱ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የባንኩ የሠራተኞች ማኅበርም በወከሉት ሠራተኞች ምትክ ከባንኩ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ሲያደርግ በቆው ድርድር መፍትሔ ባለመገኘቱ ለሚመሰረተው ክስ ምክንያት መሆኑ ታውቋል። ማኅበሩ የወል ክሱን ለመመስረት እንደምክንያት የሆኑት በአሰሪና ሠራተኛ አዋጁ መሰረት አንድ ሠራተኛ በሳምንት ከፍተኛ ሊሠራ የሚገባው 48 ሰዓት ቢሆንም በኅብረት ስምምነት መሰረት ግን ዝቅ ለማድረግ እንደሚቻል መደንገጉ አንዱ እንደሆነ ታውቋል።

በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኀይል ቀጣሪ ከሚባሉ ድርጅቶች መካከል የሆነው ንግድ ባንክ ለተከታታይ ዓመታት በሠራተኞቹ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥቄዎች ሲቀርብበት ነበር። ይህንን የደመወዝ እና የሥራ እርከን ዕድገት ጥያቄዎች ከማንሳት ባለፈም በያዝነው ዓመት ሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ ታስቦ በሒደት መሰረዙም ይታወቃል።

በተለይም በፍራንክፈርት ስኩል ኦፈ ፋይናስ አማካኝነት ለረጅም ዓመታት ሲጠና የነበረው እና ባለፈው ዓመት የተተገበረው የመሥሪያ ቤቱ መዋቅር በድርጅቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ቅሬታዎች መባባስ ምክንያት መሆኑን ሠራተኞቹ ገልፀዋል። ስርዓቱም በከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን ከመጥቀም ባለፈ ለብዙኀኑ ምንም ለውጥ አላመጣም ብለው ይሞግታሉ።

በያዝነው ወርም በባንኩ የተደረገው የ15 በመቶ ኑሮ ውድነት አበል ክፍያ ለከተማ ሠራተኞቹ መክፈል መጀመሩን ሲያስታውቅ በአስቸጋሪ ቦታዎች ለሚሠሩ ሠራተኞች ሲከፈል የነበረው በርሃ አበል ላይም ዐሥር በመቶ በላይ ጭማሪ ማድረጉም ታውቋል።

የድርጅቱ ሠራተኞች ይህ ጭማሪም በከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ ላሉ ሠራተኞች ከሚያስገኘው ጥቅም የተለየ ለብዙኀኑ ሠራተኛ ያለው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ዝቅተኛ ደመወዝ ያለው ሠራተኛ የበለጠ ለኑሮ ውድነት ጫና የተጋለጠ ቢሆንም ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ድጎማ እንዲያገኙ የተደረገው ግን ክፍተኛ ደመወዝ ላላቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል። ባንኩ የቀጠረውን ጠበቃ ማንነትን ለማወቅ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ጥረት የሠራተኛ ማኅበሩን አባለት ለማነጋገር ብትሞክርም ምላሽ ግን ማግኘት አልቻለችም። በተጨማሪም የባንኩን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ለማገኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here