የሲዳማ ክልል መሆን እና ይዞ የሚመጣው መዘዝ

0
2228

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ለመግባት ግፊቶች በበረቱበት በዚህ ወቅት፣ የሲዳማ ክልል መሆን በሐዋሳ ዕጣ ፈንታ ምን አንድምታ ያመጣል? ጌዲኦ ከደቡብ ክልል ጋር የሚኖራት የወሰን ግንኙነት ስለሚቋረጥ የጌዲኦስ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ከሀብት ክፍፍል ጋር በተያያዘ የሚነሱት ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በሚሉና ተያያዥ ለሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ያጠኑ ባለሙያዎችን እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችን በማነጋገር የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ተግባራዊ መደረግ ሊያመጣ የሚችለውን አንድምታ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ
ሰማዩ በጠቆረበት፣ ዳመናው ያረገዘውን ዝናብ ለመዘርፈገፍ መጣሁ መጣሁ በሚልበት፣ የነጎድጓድ ድምጽ በሚያስገመግምበትና ብርዱ በሚያንዘፈዝፍበት ወርሃ ሐምሌ በባተ በዐሥረኛው ቀን ለሲዳማ ዞን የፖለቲካ ልኂቃን ብራማ ሆኖላቸዋል። በዕለቱ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የዞኑን የክልልነት ጥያቄ በመደገፍ ያፀደቀ ሲሆን ሕጉን ተከትሎም ለክልሉ ምክር ቤቱ ቀርቧል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትም የዞኑን የክልል የመሆን ጥያቄ በሙሉ ድምጽ ጥቅምት 23/2011 በማፅደቅ፤ በሕዳር 12/2011 ምክር ቤቱ በይፋ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሰረት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ጥያቄ አቅርቧል፤ ላለፉት ሰባት ወራትም የሕዝበ ውሳኔውን ተፈጻሚነት ትንፋሽ በሚያስቆርጥ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ብሔርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራል ስርዓትን በሕግ ካፀናችበት 1987 እና ይህንኑም ተከትላ ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ካዋቀረች ወዲህ፣ እንደ ሲዳማ ዞን አዲስ ክልል ለመመሥረት ጫፍ ደርሶ የፌደራል መንግሥት አባል ለመሆን የደረሰ ብሔር፣ ብሔረሰብም ሆነ ሕዝብ የለም።

ዳራ
የሲዳማ ብሔረሰብ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው። ሲዳማ የሚለው ቃል ለሕዝቡና ለመሬቱ የተሰጠ ሥያሜ ሲሆን፣ “ሲዳንቾ” የሚለው ቃል ደግሞ ለኹለቱም ፆታዎች ሲዳማነታቸውን የሚገልጽ ነው። ብሔረሰቡ በዋናነት ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ በኦሮሚያ ክልል በባሌ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ አርሲ ዞኖች እና በክልሉ በወላይታና በጌዲኦ ዞኖች ውስጥ ይኖራል። በቀድሞ ጊዜም ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በኋላም ክፍለ አገር ይባል እንደነበር በድርሳናት ላይ ተጠቅሷል።

የብሔረሰቡ ዋና የምጣኔ ሀብት መሠረት እርሻና ከብት እርባታ ሲሆን፤ አነስተኛ የዕደ ጥበብ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ይከናወናሉ። በብሔረሰቡ እንሰት፣ ቡና፣ በርበሬ፣ ጐመን፣ ሽንኩርት፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ አጃ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ቦሎቄ፣ አቦካዶ፣ አናናስ፣ ማንጐ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አብሽ፣ ኮረሪማ፣ በሶብላ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ቦይና፣ ሸንኮራ አገዳና ጫትን በዋናነት ያመርታል።

የብሔረሰቡ ቋንቋ “ሲዳምኛ” ሲሆን ከምሥራቅ ኩሻዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ይመደባል። ከካምባታ፣ ከጠምባሮ፣ ከኦሮሞ፣ ከሀላባ ከቀቤና እና ከጌዴኦ ቋንቋዎች ጋር ይቀራረባል። ብሔረሰቡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ወላይትኛን ኩታ ገጠም በሆኑ አካባቢዎች ይጠቀማል።

የክልልነት ጥያቄው መነሻ
የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ ከፊት ሆኖ በመንፈስ የሚመራው በታዋቂው የሲዳማ ፖለቲካ ልኂቅ ወልደ አማኑኤል ዱባለ በጥር 1969 የተመሰረተው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ነው። ንቅናቄው ከተመሰረተ ከአራት ዐሥርት ዓመታትን በላይ ካስቆጠሩት ኦነግ እና ሕወሓት ተርታ ያሰልፈዋል፤ በዕድሜም ብቻ ሳይሆን ይከተሉት በነበረው የማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮት መመሳሰላቸውን ልብ ይሏል።

እስከ ዕለተ ሞታቸው ሲአን’ን ሲመሩት የነበሩት ወልደአማኑኤል ዱባለም ከሲዳማ ባላባት ወገን የሆኑ፣ የሰፊ መሬት ባለቤት ከሆኑ የሲዳማ ፊውዳል ቤተሰቦች የተገኙ ናቸው። በዚሁ ምክንያት የሰፊ መሬት ባለቤት ፊውዳሎች ብቻ በሚገቡበት የአፄው ዘመን ፓርላማ ተመራጭ የነበሩ ሰውም እንደነበሩ በሕይወታቸው ዙሪያ የተጻፉ ድርሳናት ያትታሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የዶክትሬት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ሳሙኤል አለማየሁ ሲዳማ ክልል እንዲሆን ከሚሟገቱ የብሔሩ ተወላጆች መካከል አንዱ ናቸው። ሲአን እንደ ሕወሓት እና ኦነግ ጎላ ያለ ባይሆንም፣ በሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች አምባ ይዞ በደርግ ላይ የትጥቅ ትግልም የሞከረ ንቅናቄ መሆኑን የሚናገሩት ሳሙኤል፣ ኢሕአዴግ በ1983 አዲስ አበባ እና መላ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ በተመሰረተው የሽግግር ምክር ቤት ሲዳማን ወክሎ ተሳታፊ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የእንግሊዝኛው የድረ ገጽ መጽሔት ‘አዲስ ስታንዳርድ’ በግንቦት 22/2011 Special Edition: Chronicles of Sidama people’s struggle for self rule በሚል ልዩ ዕትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዴቨሎፕመንት ጥናት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ሽፈራው ሙላቱ (ዶ/ር) ባስነበቡት ጽሁፍ እንደጠቀሱት የንቅናቄውን መሪ ወልደ አማኑኤል ላይ በጠራራ ፀሐይ የተቃጣውን የመግደል ሙከራ ተከትሎ በሰኔ 1984 ከሽግግር ምክር ቤቱ መልቀቁ ታውቋል።

ሳሙኤል በመሰረታዊነትም የሚነሳው ዋናው ለሲአን ከሽግግሩ መገለል ኢሕአዴግ መሆኑን ያሰምሩበታል። ደቡብ ክልልን በአንድ ጨፍልቆ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የሚባለውን ፓርቲ አቋቁሞ “አስተዳዳሪያችሁ እሱ ነው” ከማለቱ በፊት አብዛኞቹ በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔረሰቦች የራሳቸው ፓርቲዎች እንደነበሯቸውና እስኪገለል ድረስም ሲአን ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ግንባር ቀደሙ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ብዙዎች ሲናገሩ እንደሚደመጠው በኢሕአዴግ ፊታውራሪነት ተግባራዊ የተደረገው ፌደራሊዝም ስሁትነት ከሚገለጥባቸው ክልሎች አንዱ ከ50 በላይ የሚሆኑ ብሔሮችን አጭቆ የያዘው፣ ሌሎች ክልሎች በብሔራቸው ሲሰየሙ፣ በአቅጣጫ የተሰየመው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ በዚህ ክልል ውስጥ ከሚኖሩ በርካታ ብሔረሰቦች አንዱ የሲዳማ ብሔረሰብ በአቅጣጫ ሥም ከተሰየመው ክልል ወጥቶ፣ በብሔሩ ሥም የሚጠራ የራሱን ክልል የመመስረት ጥያቄ ሲያቀርብ ዘለግ ያሉ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራሉ።

የሲዳማ ብሔር ከሚያቀርባቸው መከራከሪያዎች ቀዳሚው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን፣ ለብሔር ብሔረሰቦች የተሰጠውን እስከ መገንጠል የሚዘልቀውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው የሚሉት ሳሙኤል, ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጋው የሲዳማ ሕዝብ ቁጥር እና የያዘው ሰፊ የቆዳ ስፋት በደቡብ ክልል ካሉ ብሔረሰቦች ቀዳሚውን አብላጫ ቁጥር ሌሎች ደጋፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በአገር ዐቀፍ ደረጃም ከሶማሌ ሕዝብ ቀጥሎ አምስተኛው ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ነው የሚለው መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ሌላው መከራከሪያ ሆኖ የቀረበው ዞኑ ቡና አብቃይ ከሆኑት አንዱ በመሆኑ፣ ክልል ለመሆን የተፈጥሮ ሀብትም አያንስም በሚል እንደሆነ ሳሙኤል አክለዋል። የሐዋሳ ከተማ የሲዳማ ዞን አንድ አካል እንደመሆኗ የሲዳማ ልኂቃን ከተማዋን ለሲዳማ ክልል ዋና ከተማነት አጥብቀው እንዲመኟት ያደረገ ሁነኛ ምክንያት ነው ሲሉም ያክላሉ።

እንደ ሳሙኤል ገለጻ፣ በዚሁ ትግላቸው ሲዳማዎች ሞትን እና እስራትን አስተናግደዋል። በ1995 ይህንኑ የክልል ጥያቄ አንግበው አደባባይ የወጡ ከአዋሳ ዙሪያ የሲዳማ ገጠራማ ቀበሌዎች የመጡ የሲዳማ ተወላጆች በጥይት የተቆሉበት “የሎቄው ግድያ” በመባል የሚታወቀው እልቂት በሰፊው የሚታወቅ ነው። ከሎቄው ግድያ በኋላ ጋብ ብሎ የነበረው የሲዳማ የክልል ጥያቄ ከምርጫ 1997 ማግስት በኋላ አገርሽቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራሳቸው አዋሳ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪ እንዲሰጡ ግድ ብሎ ነበር። መለስ በ1999 በሐዋሳ ከተማ ተገኝተው ከአገር ሽማግሌ እስከ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙበት ውይይት ቢያደርጉም የሲዳማዎች ክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች
በ1992 (እ.ኤ.አ) በነበረው የሽግግር መንግሥት የተዋቀሩ 14 ክልሎች እንደነበሩ የሚናገሩት የሲዳማ ነፃነት ግንባር የውጭ ጉዳይ ኃላፊ እና የሕዝቦች ጥምረት ለነፃነት እና ዴሞክራሲ ዋና ጸሐፊ ደንቦባ ናቲ “በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ ኅብረተሰቡም ሳይመክርበት በሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ተብሎ የተቋቋመውም ሳይመክርበት በመለስ ዜናዊ እና የዚያን ጊዜ የደቡብ የኢሕአዴግ ተወካይ በነበሩት ቢተው በላይ ብቻ ውሳኔው ተግባራዊ ሆኖ አምስት ክልላዊ መንግሥታት አንድ ሆነው እንዲዋቀሩ ሲደረግ ሲዳማ ተቃውሞውን ሲያሰማ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

ተሸጋግረው ሲጨርሱ ወደ ዘጠኝ ክልሎችና አንድ የከተማ መስተዳደር፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አንድ የከተማ መስተዳድር ተጨምሮ ኹለት ሆኑ። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ብሔሮች ክልል ለመመሥረት ፈልገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል ወይም ትተውታል። ሲዳማ፣ ጌድኦ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ በርታና ጉሙዝ ተጠቃሽ ናቸው። በጣም በመግፋትና በማምረር እንዲሁም ገሀድ በማድረግ ብሎም ለግጭትና ሕይወት መጥፋት ምክንያት በመሆን የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ግምባር ቀደም ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም በተደጋጋሚ ከፍተኛ ትችቶች ሲያቀርቡበት የቆየ ሲሆን፣ በአንድ ወገን የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይሰጣቸዋል የሚሉ ደጋፊዎች ሲኖሩ፣ ይህ በአገሪቱ ግጭትን በማባባስ አገሪቱን ሊበታትናት ይችላል የሚሉ ተቺዎች ያለማቋረጥ ሲከራከሩበት ቆይተዋል።

ተፈጻሚነት አግኝቶ በተግባር ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ኖሮት እየተተገበረ ያለው የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም፣ በተለይ በደቡብ ክልል አወቃቀር ላይ ከፍተኛ ትችት እንዳለበት የሚናገሩት ሲሳይ፣ “ይህም ብሔርን መሠረት ያደረገ አወቃቀር የተከተለ ክልላዊ ሥርዓት ያለው ፌዴራሊዝም ተተግብሮ እያለና የሐረሪ ክልል አነስተኛ ቁጥር ያለው የሕዝብ ብዛት ኖሮት ሳለ፣ 56 ብሔር ብሔረሰቦችን በአቅጣጫ መትሮ አንድ ላይ በክልልነት ማቀፉ አግባብ አይደለም ከሚል መነሾ የሚመነጭ ነው” ችግሩን ያስረዳሉ።

ከደቡብና ከጋምቤላ ክልሎች በስተቀር ሁሉም ክልሎች ሥያሜያቸው ሳይቀር አብላጫ ቁጥር ባለው ብሔር የተሰየሙ ሲሆን፣ በዚህ አግባብ ከተሔደ ሕገ መንግሥቱም ስለሚፈቅድ በኢትዮጵያ ከ80 ያላነሱ ክልሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት መምህር የሆኑት አሰፋ ፍሰሐ (ፕሮፌሰር)፣ ባዘጋጁት የማስተማሪያ ጽሑፍ ላይ አመልክተዋል።

እንደሳቸው ምልከታ በክልል ደረጃ በፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያ ተገፍቻለሁ ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ልኂቃን፣ የራሳቸውን ክልል የመመሥረት ግፊቶችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።

ፕሮፌሰሩ አክለውም በ2001 ባቀረቡት ትንታኔ፣ 56 ብሔር ብሔረሰቦች ያሉትን የደቡብ ክልል እንደገና በተለያዩ ክልሎች ማደራጀት ከተጀመረ ማብቂያው የት ነው ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህም የፓንዶራ ሳጥን መክፈት ነው ሲሉ ይተቻሉ።

ፓንዶራ በግሪክ አፈ ታሪክ የነበረች ገጸ ባሕርይ ሥም ሲሆን፣ ከገነት እሳት የሰረቀውን ፕሮሜቲየስን ለመቅጣት ሲል የአማልክት ንጉሡ ዚየስ የላካት ሴት ነች። ይህችም ሴት በድንገት ያገኘችውን በሽታን፣ ሞትንና በርካታ ክፉ ዕጣ ፈንታዎችን የያዘውን አቁማዳ ሳታስበው ትከፍታለች። አቁማዳውን በፍጥነት ብትከድነውም፣ በውስጡ ተስፋ ታፍኖ ሲኖር ሌሎቹ ክፉ ዕጣ ፈንታዎች ሁሉ ወጥተው ነበርና ከፍተኛ ጉዳትን አስከተሉ።

ይህም በጊዜ ሒደት አቁማዳው ወደ ሳጥን ተቀይሮ እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል። አባባሉም ብዙ ያልተተነበዩ ችግሮችን የሚያስከትል ጉዳይን መነካካት በሚል ትርጉሙ ጥቅም ላይ ይውላል። እንደፕሮፌሰሩ ዕይታ የደቡብ ክልልም የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የፓንዶራ ሳጥን እንደሆነ ይጠቀሳል።

የክልልነት መከለያዎች
የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር በሰፊው ከሚወቀስበት አንዱ ለክልልነት የተወሰዱት መሥፈርቶች ናቸው። በእርግጥ በዓለም ላይ አንድ ወጥ መሥፈርት የለም። አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ጀርመንን በዋናነት መሥፈርትነት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥን ከግምት ያስገቡ ሲሆን በሌላ በኩል ናይጀሪያ፣ ስፔን፣ ቤልጂየምና ሕንድ በተወሰነ መልኩ ካናዳ ደግሞ ከመልከዓ ምድር በተጨማሪም ብሔርን ከግምት ያስገቡ መሆናቸውን አሰፋ ፍሰሐ (ፕሮፌሰር) መጽሐ ያብራራል።

ከላይ ከተጠቀሱት አንጻር የኢትዮጵያ ቅይጥ ነው የሚሉት ሲሳይ፣ በኢትዮጵያ ለክልል ምሥረታ ከግምት መግባት ያለባቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46(2) መሠረት፣ አራት መሥፈርቶች መኖራቸውን ያወሳሉ፤ እነሱም፣ የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ናቸው። ከላይ ከተጠቀሱት መሥፈርቶች አንፃር አንድ ብሔር በዛ ብሎ የሚገኝባቸው እንደትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ማንነትና ቋንቋ ገነን ብለው ይታያሉ። በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚና የመሳሰሉት መሥፈርቶች ቢኖሩም መልከዓ ምድር ጎልቶ እንደሚታይ ይተነትናሉ። ግምት ውስጥ የገባው በአንድ አካባቢ መገኘታቸው እንጂ ቋንቋቸው ወይም ማንነታቸው አይደለም በማለት ነው።

ፈቃድንም በተመለከተ እነሲዳማ፣ ከፋ፣ ጋሞ፣ ጉሙዝ፣ በርታና ጉራጌ በተለያዩ ወቅቶች የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ጥያቄ አንስተው የነበሩ መሆኑን ያነሱት ሲሳይ፣ “ወደውና ፈቅደው ነው ክልሎቹን የመሠረቱት ማለት ሊያጠራጥር ይችላል። በመሆኑም ቅይጥ እንጂ ብሔር ላይ ብቻ ተመርኩዞ ተመሠረቱ ማለት አዳጋች ነው” ሲሉ ቀድሞውኑም ከክልሎቹ ፈቃድ ውጭ ሁሉም በደቡብ ክልል ውስጥ መታቀፋቸውን ያስታውሳሉ።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት የክልል አመሠራረትን በተመለከተ የሕገ መንግሥቱ ውይይት ላይ እንደ አማራጭ መከራከሪያነት ቀርቦ የነበረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ወቅት የነበረው መልከዓ ምድርን መሠረት ያደረገው ጠቅላይ ግዛታዊ እና ክፍለ አገራዊው አወቃቀር ነበር። ለመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና ለአስተዳደራዊ ምቹነትና ቅልጥፍና ቅድሚያ የሚሰጥ ማለት ነው።

አሁን ያለውን አከላለልን በተመለከተ አንድ የማይታበል ሀቅ መኖሩን የሚጠቁሙት ሲሳይ፣ እሱም በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት ያለመጣጣም ችግር መሆኑን ያነሳሉ። በቆዳ ስፋት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከኦሮሚያ ቀጥሎ ኹለተኛ መሆኑን አንስተው፣ በሕዝብ ብዛት ሲታይ ደግሞ የደቡብ ክልልን 1/3ኛ፣ ወይም ከትግራይ ጋር የተቀራረበ መሆኑን ያስረዳሉ። ከቆዳ ስፋት አንፃር ደግሞ ኦሮሚያ 33.05 በመቶ፣ ሶማሊያ 19.82 በመቶ፣ አማራ 17.34 በመቶ፣ ደቡብ 10.28 በመቶና ትግራይ ደግሞ 5.53 በመቶ ኢትዮጵያን ይጋራሉ። በሕዝብ ብዛት ደግሞ ኦሮሚያ 36.7 በመቶ፣ አማራ 23.3 በመቶ፣ ደቡብ 20.4 በመቶ፣ ሶማሊያ 6 በመቶና ትግራይ 5.8 በመቶ ነው።

የቆዳ ስፋት ድርሻን ከሕዝብ ብዛት ድርሻ ጋር ስናነፃፅረው፣ እንዲሁም ክልሎቹ ያሉበትን የልማት ደረጃ ከግምት ስናስገባ በጀት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ መኖሩ አሌ የሚባል አይደለም የሚሉት አሰፋ በበኩላቸው፣ ነገሩ የሚከፋው ክልሎች አብዛኛው በጀታቸው የሚሸፈነው ከፌዴራል መንግሥቱ በሚያገኙት ድጎማ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህን ጊዜ አንዱን ማስደሰቱ ሌላውን ቅር ማሰኘቱ እንደማይቀር በመጠቆም። ክልል መሆንም በራሱ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብ አይከብድም ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ስለሆነም የግድ መሥፈርቱ ወደ አንዱ የሚያጋድል መሆን ያለበት ይመስላል። ለዚያም ነው ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ከኹለት አንዱ የተመረጠው ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

የሐዋሳ እና ጌዲኦ ዕጣ ፈንታ
እንደ ሲሳይ አመለካከት ሐዋሳን ማዕከሏ ያደረገች የሲዳማ ክልልን ዕውን የማድረጉን ነገር በተመለከተ በሲአንም ሆነ በደኢሕዴን ውስጥ ያሉ፣ ከፌደራል እስከ ክልል በተዘረጋ ግዙፍ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የተሰየሙ፣ የወንበር ዕድል ያልቀናቸው ማናቸውም የሲዳማ ልኂቃን በጠቅላላ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በወል የሚጋሩት ናፍቆት ነው።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ እንደሚሉት፣ በአንፃሩ ከመለስ እስከ ዐቢይ በዘለቀ ሁኔታ የአገሪቱ መንግሥት የሲዳማ ክልልነትንም ሆነ አዋሳን የሐሳባዊው ክልል ዋና ከተማ አድርጎ የማፅናቱን ሐሳብ እምብዛም አይወዱትም። የዚህ ዋናው ምክንያቱ የሐዋሳ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው የሐዋሳ ከተማ የክልሉ ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል ኻያ ሰባት ዓመት አለፋት።

በዚህ ዓመታት ውስጥ ከተማዋ በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ ውብ ከተማ ከመሆኗም ባሻገር የአገሪቱ ኹለተኛ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ የፌደራሉ መንግሥት ፖለቲካዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ኩነቶች የሚከወኑባት፣ ከወዳጅ አገር የመጡ የፌደራሉ መንግሥት እንግዶች የሚስተናገዱባት፣ ዓለም ዐቀፍ መዋዕለ ነዋይ የሚርመሰመሱባት፣ ቱሪስቶች የሚዳረሱባት በፌደራሉ መንግሥት በስስት የምትታይ ከተማ ነችና።

ሲዳማ እራሷን ችላ ክልል መሆኗ ሕገ መንግስታዊ መብት መሆኑ ይታወቃል፤ ነገር ግን ክልል ከሆነች በኋላ ሐዋሳን የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ለማድረግ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። አንዱ እንቅፋት ከነዋሪዎችዋ መካከል የሚበዙት የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች መሆናቸው ነው። በ1999ኙ ሕዝብ ቆጠራ የነዋሪው ብዛት 157 ሺሕ 139 ነበር። የገጠር ቀበሌዎች ሲጨመሩ ደግሞ 258 ሺሕ ግድም ነው። ከከተማ ነዋሪዎች መካከል የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ከ38 ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ ወላይታዎች 35 ሺሕ በመሆን በኹለተኛ ደረጃ ይከተላሉ። ሲዳማዎች ደግሞ በ28 ሺሕ 3ኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ኦሮሞ በ13 ሺሕ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሲዳማ ክልል ከተባለ የሐዋሳስ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው የሚለው ምላሽ ማግኝት ይገባዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ከሕግና ከፍትሓዊነት አንጻር ሦስት መሰረታዊ ችግርች እንዳሉት ይነገራል። አንደኛ – የሲዳማ ክልል ሲመሰረት በስተሰሜን በኩል ሐዋሳ አለች። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና በመላው የደቡብ ክልል ሕዝብ ያደገች ከተማ ናት። በክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ብዙ ወጭ ሐዋሳ ላይ ፈሷል። ይችን ዉብ ኅብረ ብሔራዊ ከተማ ከአዲስ አበባና ከባሕር ዳር ቀጥሎ፣ ምን አልባት ከባሕር ዳር በላይ፣ ትልቅና ዘመናዊ የሆነች ከተማን ለአንድ ጎሳ ብቻ መስጠት ኢፍትሓዊነት ነው የሚሉት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ በመሆኑም ሲዳማዎች ክልል ካልተሰጠ ብለው ድርቅ ካሉ ያለ አዋሳ መሆኑን እንዲረዱ ማድረጉ አስፈላጊና ውሳኔያቸውን መልሰው እንዲመረምሩ ሊረዳቸው ይችላል ይላሉ። የሐዋሳ ከተማ ራሷን የቻለን ቻርተር ከተማ ሆና እንድትቀጥልም መደረግ ነው ያለበት። ሐዋሳ የነዋሪዎቿ እንጂ የሲዳማዎች ብቻ አይደለችም ሲሉም ያክላሉ።

መልስ አልባ ጥያቄዎች
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቲዎስ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፤ ሚሊዮን ታኅሣሥ 24/2011 ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ “የሐዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን ውስጥ ስለምትገኝ የሐዋሳ ጉዳይ ከሲዳማ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፤” ብለዋል። የክልሉ መቀመጫ ከሐዋሳ የሚነሳ ከሆነ ሌላ ከተማ ለደቡብ ክልል መቀመጫ እንደሚሆን ርዕሰ መስተዳድሩ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ኹለተኛው፣ ችግር ብለው የሐዋሳ ዩኒቨርስቲው መምህር ያነሱት ደግሞ፣ ከሲዳማ ክልል በስተደቡብ የሚገኝ ሌላ ትልቅ የደቡብ ክልል ዞን አለ፤ የጌዴዎ ዞን። የሲዳማ ዞን የሲዳማ ክልል ይሁን ከተባላ የጌዴዎ ዞን ከተቀረው የደቡብ ክልል ዞኖች ጋር ይለያል ማለት ነው። ኩታ ገጥምነቱ ስለሚቀር። የጌዴዎ ዞን ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱ ክልል ሊሆን ነው? ወይስ በሲዳማ ክልል ውስጥ ሊጠቃለል ነው? ስለዚህ የሲዳማ ክልል የመሆን ጉዳይን በተመለከተ ሲዳማዎችን ብቻ ሳይሆን የጌዴዎ ዞን ነዋሪዎችን የሚመለከት ነው የሚሆነው። እናም ሌላ ትልቅ ጉዳይ መኖሩም ሊሰመርበት ይገባል ባይ ናቸው።

ሦስተኛው፣ ክልል ምሥረታ ላይ ሕገ መንግሥቱ ስለንብረትና ዕዳ ክፍፍል የሚያነሳው ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ሲሳይ፣ ለአብነት ሲዳማ ዞን ክልል ሲሆን፣ ሐዋሳን ይዞ ይገነጠላል እንበል። የደቡብ ክልል ሐዋሳ ላይ ብዙ የመሠረተ ልማትና የቢሮ ግንባታዎችን አከናውኗል። በአጠቃላይ በደቡብ ክልል ውስጥ ለሚኖሩት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲባል የተገነቡና ወጪ የተደረገባቸው መሆናቸውን በማስታወስ፣ ሲዳማ እነዚህን መሠረተ ልማትና ቢሮዎች ይዞ ከደቡብ ሲገነጠል ደቡብ ከእንደገና በሚመሠረተው ዋና ከተማ ላይ ከዓመታዊ በጀቱ እየቆነጠረ ለሌሎች የልማት ሥራዎች ማዋል የሚችለውን ለቢሮና ለመሳሰሉት ግንባታዎች ሊያውለው ነው። ሲዳማ ግን ከእነዚህ ተገላግሏል ሲሉ የደቡብ ክልልን መፃኤ ዕድል ያሳያሉ።

ከዚህ አንፃር ደቡብ ሲጎዳ ሲዳማ እንደሚጠቀም የጠቆሙት ሲሳይ፣ ፌዴራል መንግሥቱም ለአዲሱ ክልል ወይም ለቀሪው የክልል መሆኛ ወጪ እንዲደጉም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳልተጣለበትና፣ ክልሉ የተበደረው ገንዘብ ቢኖርበትና በተለይም ብድሩ የዋለው የሲዳማ ዞንን የሚጠቅም ተግባር ላይ ከሆነ ይህንን ብድር ከተገነጠለ በኋላ የመክፈል ወይም የመጋራት ግዴታ ይኑርበት ወይም አይኑርበት የሚገልጽ ሕግ የለንም ሲሉ የሕግ ክፍተቱንም ይጠቁማሉ።

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ጋዜጣ ታኅሣሥ 8/2011 ጥያቄ ያቀረበላቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ሚሊዮን፣ “ልክ ነው ይህንን የሚገዛ ሕግ በአገሪቱ የለም። ነገር ግን ካሁን በፊት በክልሉ የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ስንሠራ በነበረን ልምድ ተጠቅመን ኮሚሽን በማቋቋም እናከናውናለን” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ልዩ ዞን ወይም ወረዳ በሚመሠረትበት ጊዜ ምን መሆን እንዳለበት የደቡብ ክልል ያወጣውን ሕግ ስናይ፣ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የብሔረሰቦች ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 60/1995 በዝርዝር ባያብራራውም፣ በድምፅ ውሳኔው መሠረት ለብቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚጀምሩት ብሔረሰቦች ቀድሞ ከነበሩበት ዞን ወይም ወረዳ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀምጧል። በፌዴራሉ ሕግ ክልል ሲመሠርቱ ስለንብረት ክፍፍል የረሳውንና ያልተቀመጠውን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ዞንና ወረዳ (ልዩም ይሁን አይሁን) ሲመሠርቱ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያስቀምጥና ስለተግባራዊነቱም የብሔረሰቦች ምክር ቤት እንደሚከታተል ይህ አዋጅ በአንቀጽ 26 ገልጾታል።

ሲሳይ በበኩላቸው፣ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፤ ክልሉ ለአዲሱ ክልል “ሥልጣኑን ሲያስረክብ” የሚል አገላለጽ ከመጠቀም ውጭ በምን ያህል ጊዜ ማስረከብ እንዳለበትም እንደማይገልጽና፣ ድምፀ ውሳኔው ከተከናወነ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የሥልጣን ርክክብ መከናወን አለበት? የሚለው ጉዳይ እንዳልተመለሰ ይናገራሉ። ይህም ሌላው በሕግ መቀመጥና መታወቅ ያለበትና የነበረበት ጉዳይ እንደሆነ በመምከር።

ከተማዋ እንዲህ አድጋ ላያት የምታማልል እንድትሆን ከፌደራል እስከ ደቡብ ክልል የዘለቀ የወል ንዋይ ፈሶባታል የሚሉት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህሩ፣ “የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ሐዋሳን በማሳደጉ በኩል ከሲዳማ ሕዝብ እኩል አስተዋፅኦ አላቸው። ሐዋሳ የደቡብ ክልል ከተማ ሆና ስትከተም ከተማዋን ያስዋበው በጀት የሚፈሰው በሁሉም የክልሉ ብሔረሰቦች ሥም ነው። ዞን ቀርቶ የወረዳ ከተማ የማይመስሉ እጅግ ያላደጉ ዱራሜን፣ ተርጫ፣ ጅንካ የመሰሉ ከተሞችን የያዙት በክልሉ ያሉ ዞን ሕዝቦች የሚፅናኑት በሐዋሳ ነው” ሲል ሐዋሳ ከደቡብ ክልል ከተነጠለች የደቡብ ክልል ቀጣይ ከተማ ጉዳይ አሳሳቢነት ላይ አስተያየቱን ሰንዝሯል።

እንደመፍትሔ
ሲሳይ መንግሥቴ እንደሚሉት፣ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ማየትም ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከሌሎች አገራት በበለጠ ተገንጥሎ አዲስ አገር መመስረትንም ሆነ፣ ተገንጥሎ አዲስ ክልል መመስረትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መደንገጉ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት አዲስ ክልል መመስረት ያለ ፌደራሉ ምክር ቤት ይሁኝታ እንደማይቻል የገለጹት ሲሳይ፣ አንዳንድ የክልሉ መንግሥታት የሕገ መንግሥቱን ጥብቅ ክልከላ ተከትለው፣ “በአሜሪካ ፌዴሬሽን ውስጥ አዲስ ክልል ከነባር ክልል ተገንጥሎ መመስረት ሙሉ በሙሉ ክልክል ነው እስከማለት ይደርሳሉ።”

በቅርብ ጊዜ ደግሞ፣ ሕንድ የተከተለችው መንገድ ምናልባትም ለእኛ አገር ጥሩ ትምህርት የሚሆን ነው የሚሉት ሲሳይ, ከብዙ ዓመታት የክልል እንሁን ጥያቄ በኋላ፣ በ2014 (እ.ኤ.አ) የሕንድ ፌደራል ምክር ቤቱ ቴላንጋና ከእናት ክልሉ አንድራ ፓርዴሽ ተገንጥሎ የራሱን ክልል እንዲመሰርት ተወሰነ። የዓለም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዋና መዲና ተብላ የምትታወቀውና የአንድራ ፓርዴሺ ዋና ከተማ ሐይድራባድ የአዲሱ ክልል ቴላንጋና፣ ዋና ከተማ እንድትሆን ነበር ውሳኔ የተሰጠው ይሁንና አንድራ ፓርዴሺ የእራን ዋና ከተማ አማርሻቲ እስኪያለማ ድረስ የ10 ዓመት የሽግግር ጊዜ (እስከ እ.ኤ.አ 2024) ተሰጥቶት፣ በአሁኑ ወቅት ሀይድራባድ የአዲሱ ክልል ቴላንጋና እና እናት ክልሉ አንድራ ፓርዴሺ የጋራ ዋና ከተማ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ወደ እኛ ስንመጣ ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄዎች እየበዙ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ እንደዚህ ያሉ የሚያቻችሉ መፍትሔዎችን ማሰብ ጠቃሚ እንደሆነ የፌደራሊዝም መምህርና ተመራማሪው ሲሳይ ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here