10ኛው ክልል ሐምሌ 11 ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል

0
500

ራሱን የሲዳማ የለውጥ አራማጆች ብሎ የሚጠራው የሲዳማ ተወላጅ ምሁራንን ያቀፈው ቡድን በመጪው ሐምሌ 11/ 2011 የሲዳማ ክልልን በይፋ እንዲመሰረት ቀን እንደቆረጠ እና በዚህ ላይም ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቲዮስ ጋር ውይይት ማድረጉን አዲስ ለማለዳ አስታወቀ። አራማጆቹ አዲሱ ክልል ሲቋቋም የሚመራበትን ሕገ መንግሥት እና አደረጃጀት በልኂቃኑ እና በዞኑ አስተዳደር ጥምረት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ባለፈው ሐሙስ፣ ግንቦት 29/2011 የሲዳማ ወጣቶች፣ የአገር ሸማግሌዎች እና የልኂቃኑ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ጋር በዚህ ውሳኔ ላይ ምክክር ሲያደርጉ ማምሸታቸውን በስብሰባው የተሳተፉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ምክር ቤት በይፋ ምንም መግለጫ ባይሰጥም በተቀመጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቂያ ላይ የሚያሳልፈው ውሰኔ የወጣቶቹን ጥያቄ በይፋ መቀበል አለመቀበሉን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ገብሩ ገብረሥላሴ፣ ጥያቄውን ማንሳታቸው ሕገ መንግስታዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም ነገር ሕጉንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ መሔድ እንዳለበት አመላክተዋል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ በማውሳት፣ የክልሉ ሕዝብም የመንግሥትን ምላሽና ሒደት በትዕግስት መጠበቅ እንደሚኖርበት አክለዋል።

ከወር በፊት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ ለመሥሪያ ቤታቸው መውድረሱን አረጋግጠዋል። ሕዝበ ውሳኔን ማካሔድ “የቦርዱን መሟላት የሚጠብቅ ጉዳይ ነው” ሲሉም መናገራቸው ይታወሳል።

ፍላታ ጂግሶ እንደሚሉት፣ በተቆረጠው ቀን የሲዳማ ክልልን ለመመሥረት ሕጋዊ መሰረት አለ። ፍላታ “የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ይኸንን ጥያቄ ለኹለተኛ ጊዜ ተቀብሎ ያስተናገደው ሐምሌ 10/2010 እንደነበር በማስታወስ፣ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ መካሔድ አለበት ነው የሚለው ሲሉ ይገልጻሉ።

ሕዝበ ውሳኔ ካልተካሔደ ግን የመብት ጥያቄ እንደመሆኑ፤ ሕዝበ ውሳኔ እንደ ሕግን ማስፈጸሚያ ሒደት (procedure) ስለሚወሰድ እና መብቱን ለመገደብ ስለማይችል፤ ሲዳማ በ2010 ጥያቄውን ተቀብሎ በወሰነ ጊዜ ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መሠረት እንዲቆይ ተደረገ እንጂ መብቱን ተግባራዊ አድርጓል ሲሉም ያክላሉ። ስለዚህ ሕዝበ ውሳኔ ማካሔድ ካልተቻለ እና በተለይ የደቡብ ምክር ቤት በዚያ ጉዳይ ገብቶ ማስፈጸም ካልቻለ፤ ያንን መብቱን መጠቀም እንዳልፈለገ ተቆጥሮ ሲዳማ በራሱ ክልል መሆኑን ያውጃል” ሲሉ ይገልጻሉ።

ፍላታ ዞኑ ወደ ክልል ካደገ በኋላ የሚኖረው አደረጃጀት ተሠርቶ ማለቁን አስታውቀዋል። “ሕገ መንግሥቱ ተሠርቶ አልቋል። ሕጎች በተለይ የሥራ አስፈፃሚ፣ ፍርድ ቤት እና እንደዚሁም የምክር ቤቱን ደንብ የሚመለከቱ ሕግጋትም እየተሠሩ ነው። እነዚህ ሥራዎች ሲዳማ ክልል ከመሆኗ በፊት ይጠናቀቃሉ” ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here