ምርጫ ሲመጣ፣ የመረጃ ነፃነት በምርጫ ወቅት ቢታይ

0
866

መጪውን የ2012 አገራዊ ምርጫ እሳቤ ውስጥ በመክተት ቤተልሔም ነጋሽ ከኹለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት የፀደውን “የአፍሪካ የምርጫ ወቅት የመረጃ ነፃነት መመሪያ” የሚል ሰነድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከወጣው መመሪያ ቁጥር 6/2010 ጋር አብረው ግንዛቤ በሚሰጥ መልኩ ቃኝተውታል። “ለመገናኛ ብዙኀንና ለጋዜጠኞች ምርጫ አዘጋገብን በሚመለከት የሥነ ምግባር መመሪያ” የተሰኘው ሰነድ ተግባር ላይ መዋል አለመዋሉንም ጠይቀዋል። ቤተልሔም መጪው ምርጫ የሚካሔድ እስከሆነ ድረስ የመረጃ ነፃነትን የሚመለከተውን ይህንን መመሪያ ለማየት፣ ተግባራዊነቱን ለመፈተሸ ጊዜው አሁን ነው በማለት ያሳስባሉ።

በቅርቡ የተሻሻለውን የምርጫ ቦርድ አዋጅ ማፀደቅና ለቦርዱ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለማዋቀር እንቅስቃሰሴ ማድረግን ጨምሮ ምርጫ ቦርድ ራሱን እንደገና ለማዋቀርና በሚቀጥለው ዓመት ለምርጫ ዝግጅት የሚረዱ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ቦርዱ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚለቀው መረጃ መሠረትና የሥራ ኀላፊዎቹ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በተከታታይ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት በሚቀጥለው ዓመት ሊካሔድ የታሰበው ምርጫ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይካሔዳል።

የመገናኛ ብዙኀን ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህንን ተግባር በአግባቡ ለማከናወን እንዲችሉም መረጃ የማግኘት አሠራር ሊኖርና ከሁሉም አካላት መረጃ የሚያገኙበት መብት በሕግ ሊረጋገጥላቸው የግድ ነው። በአገራችን መረጃና ሰነድ፣ በተለይ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች የማግኘት ችግር መዘርዘር ለቀባሪው አረዱት ነው። በድረ ገጽና መሥሪያ ቤቱም በአካል ሲቀርቡ በቀላሉ ሊገኙ የሚገባቸውና ለተገልጋዮች ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ሳይቀሩ፣ ከጥቂት ተመስጋኝ መሥሪያ ቤቶች በስተቀር፣ መረጃ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። አሁን ባለው መሻሻል፤ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በታየው ለመገናኛ ብዙኀን መልካም አጋጣሚ ነገሮች ተሻሽለዋል ቢባልም፣ መረጃ መስጠት ግዴታው፣ የመገናኛ ብዙኀንና የዜጎች መብት መሆኑን የሚረዳ የሥራ ኀላፊ ሙሉ በሙሉ አለ ለማለት ይከብዳል።

የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነፃነት ሕጉ በመሻሻል ሒደት ላይ በመሆኑ ከምርጫው በፊት ይሻሻላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ያለፈው ሕግ የነበሩበትን ክፍተቶች በማስወገድ የተሻለ የመረጃ ነፃነትን የሚያስጠብቅ እንደሚሆንም ስንጠብቅ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተሻለ ሁኔታ ያለበት በመሆኑ በተለይ በምርጫ ወቅት ተግባር ላይ ሊውል የሚችል መመሪያ አስፈላጊነትንም መጥቀስ ይገባል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰዎች ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው አባል አገራት ምርጫ በሚያከናውኑበት ወቅት የመገናኛ ብዙኀንና ኅብረተሰቡ ፍትሐዊ በሆነና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት እንዲችሉ፣ መገናኛ ብዙኀንም ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በሚል ዓላማ ያወጣው “የአፍሪካ የምርጫ ወቅት የመረጃ ነፃነት መመሪያ” የሚል ሰነድ መኖሩን ያወቅኩት በቅርቡ ነው። ቆይቼ እንደተረዳሁት ሰነዱ የፀደቀው ባንጁል ጋምቢያ ላይ ሕዳር 10/2017 በተካሔደው በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን 61ኛ መደበኛ ላይ ነው። እሳቤው አባል አገራት ሰነዱን እንደ ሞዴል በመጠቀም በምርጫ ወቅት የመረጃ ነፃነትን ለማረጋጋጥ እንዲሠሩበት፣ የየራሳቸውን ሕግና መመሪያ ሲያውጡም እንደ ስታንዳርድ እንዲያዩት ነው።

በዚያውም የተሳለጠ የመረጃ ፍሰት በአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈንና መልካም አስተዳደርን ለማምጣት ያለውን እገዛ በመረዳት በአንፃሩ በምርጫ ወቅት ወቅታዊ ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ፍሰት አለመኖር ሊያስከትል የሚችለውን ረብሻና ግጭት እንዲሁም የሰላም መታጣት ለመከላከል የሚያስችል ተግባር ለማከናወን እንዲያግዝ ነው። ሰነዱ በ2013 ሲሠራበት የነበረውንና በተግባራዊነትና ሁሉን አካታች በመሆን ረገድ ክፍተቶች ነበሩበት የተባለውን ሰነድ የተካ ነው።

በመገናኛ ብዙኀን ተሳትፎ እንደሚደርግና በተለይ ምርጫና መረጃን የሚያካትተው የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ሆኖ ስለሰነዱ አለማወቅ ትንሽ የሚያስተዛዝብ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሰነዱ እጄ እንዲገባና በጥልቀት እንድመለከተው ዕድሉን ያገኘሁት በአንድ ፓነል እንድሳተፍ ጥሪ ሲቀርብልኝና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስለተግባራዊነቱ አስተያየት እንድሰጥ ስጋበዝ ነበር።

ግብዣው “በአፍሪካ የምርጫ ወቅት የመረጃ ነፃነት መመሪያን ለመተግበር የሚጠይቀውን ሁሉ ማድረግ” (Doing what it takes: making the Guidelines on Access to Information and Elections in Africa work) የሚል ርዕስ የነበረውና በአፍሪካ ኅብረት በተካሔደው ኮንፈረንስ ወቅት ከነበሩት ተጓዳኝ የውይይት መድረኮች አንዱ በነበረው ላይ እንድሳተፍ ነበር። ፍሬደሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ የተሰኘው የጀርመን ተቋም የናሚቢያ ቢሮ የሚካሒደው የፌስሚዲያ ፕሮጀክት አካልም ነበር። በተሳትፎዬ ወቅት በፓነሉ አቅራቢ ከነበሩት ከጋምቢያ፣ ካሜሩንና ዙምባብዌ ከመጡ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች እንደተረዳሁት ሰነዱ በአገራቸው ሊተገበር ቀርቶ በጋዜጠኛውና በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ያለው እውቅና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ በግላቸውም አይተውት እንደማያውቁ ተናግረዋል። አጋጣሚውን የወደድኩት ግን ከአገራችን ሁኔታ ጋር በማገናኘት ባደረኩት ጥረት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 6/2010 ለማየትና ከሰነዱ ጋር ለማወዳደር ዕድሉ ስለገጠመኝ ነው።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ኹለቱን ሰነዶች ለማወዳደር ወይም ከላይ የተጠቀሰውን የአፍሪካ ኅብረት ሰነድ ማየት ሳይሆን የምርጫ ቦርድን “ለመገናኛ ብዙኀንና ለጋዜጠኞች ምርጫ አዘጋገብን በሚመለከት የሥነ ምግባር መመሪያ” የተሰኘ ሰነድ ይዘት ወፍ በረር ማስቃኘት፣ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ የምናካሒድ ከሆነም ጥቅም ላይ ይውላል አይውልም ለሚለው ተጠየቅ እንዲደረግበት ጥቆማ ለመስጠት ነው።

በ2002 የተካሔደው ምርጫ ከመካሔዱ በፊት ለዚያ ምርጫ እንዲያገለግል ተብሎ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የወጣው መመሪያ ቁጥር 6/2010 የሥነ ምግባር መመሪያው ያስፈለገበትን ምክንያት ሲጠቅስ “መጪው ምርጫ ተዓማኒ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ለመገናኛ ብዙኀን የሥነ ምግባር መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ፣ መገናኛ ብዙኀንን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ዕጩዎችን፣ እና የምርጫ አስተዳዳሪ አካላትን አንዳቸው የሌላቸውን መብት በሚጋፋ መልኩ እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ እንዲያስችል” መሆኑን ሲጠቅስ መገናኛ ብዙኀን ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያላቸውን የማይተካ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባትም ጭምር መውጣቱን ይጠቅሳል።

በወቅቱ የተካሔደው ምርጫ ብዙም አጓጊ ያልነበረና በወቅቱ የነበሩትን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ያሉትን ጥቂት የመገናኛ ብዙኀን ትኩረት ብዙም ያልሳበ ቢሆንም በወጣበት ወቅት ግን ተቃውሞ አስተናግዶ ነበር።

ለምሳሌ ለሥራው የሚያግዙ ሁሉንም ቅድመ ሁኔታዎችና አካላት ሁኔታ አካቷል የተባለለት የአፍሪካ ኅብረት መመሪያ የሚከተሉትን በምርጫ ሒደት ውስጥ ቁልፍ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አካላትን ዝርዝር ግዴታና ኀላፊነት የሚጠቅስ ነው። የምርጫ አስተዳዳሪዎችን የሚሾሙ አካላት፣ ምርጫውን የሚያስተዳድሩ/የሚመሩ አካላት፣ የሕግ አስፈፃሚ አካላት፣ የምርጫ ታዛቢዎችና ተቆጣጣሪዎች፣ የመገናኛ ብዙኀንና የኦንላይን ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የመገናኛ ብዙኀን ተቆጣጣሪ አካላት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት በዝርዝር ኀላፊነትና ግዴታቸው የተቀመጠ አካላት ናቸው።

የአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዝኛ ዜና ድረ ገጽ የግንቦት 24/2010 ዘግባ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን የምርጫ ዘገባ ሥነ ምግባር መመሪያውን የፕሬስ ማኅበራት ጥያቄ አነሱበት ወይም ተግዳሮት የሚል ዘገባ አስነብቦ ነበር። ዘገባው እንዳለው በምርጫ ቦርድ የፀደቀው መመሪያ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኀን ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ አሰጣጥና በውጤት ገለፃ ሒደት ላይ እንዳይዘግቡ ክልከላ ያደርጋል ወይም ገደብ ይጥላል የሚል ነው። ይኸውም መገናኛ ብዙኀኑ “ፖለቲካ አለመረጋጋት” ሊያስከትል የሚችል ዘገባ እንዳይሠሩና ውጤትን በተመለከተ ግምት የሚሰጥ ዘገባ እንዳያቀርቡ የሚከለክል ነው። ከዚህ ሌላ ጥቃቅን ስህተቶች የሚሠሩ ጋዜጠኞች የመዘገብ ሥራ ፈቃዳቸው ይሰረዛል ሲል ከባድ ተብለው የተቀመጡትን በተላለፉ ላይ የገንዘብና እስርን ጨምሮ የወንጀል ቅጣት ያስከትላል የሚለው ሌላው ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ ነው።

በወቅቱ ተጠይቀው በዘገባው መልሳቸው የተካተተው የሥራ ኀላፊ የሥነ ምግባር መመሪያው ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ሲባል የወጣና ጋዜጠኞች ሰው እንደመሆናቸው ስህተት እንዳይሠሩ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰው ነበር።
በበኩሌ እንደምረዳውና በወቅቱ ተቃውሞ ያቀረቡት የሚዲያ ባለሙያዎች ጠቅሰውት እንደነበረው የመመሪያው የመጀመሪያው ስህተት የሚመነጨው የጋዜጠኛ የሥነ ምግባር መመሪያ ተብሎ ሳለ በምርጫ ቦርድ መዘጋጀቱ ነው። የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲያወጡ የሚጠበቁት በአንድ ሙያ ውስጥ ያሉት ራሳቸው ባለሙያዎቹ ናቸውና። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ አንዱና ዋነኛ አካል፣ በተለይም ነፃነቱ አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውልና በዚያ ምክንያት ሕዝብና ግለሰቦች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጋዜጠኛው ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ከዚህም ሌላ የሥነ ምግባር መመሪያው የመገናኛ ብዙኀን ኀላፊነት በሚለው ዝርዝር ውስጥ አጠቃላይ አንቀጾችን በማስቀመጥ ፋንታ መገናኛ ብዙኀን በመሠረታዊ የሙያው ሥነ ምግባር መሠረት መሥራት የሚጠበቅባቸውን እውነታንና የግል አስተያየትን በሚመለከት ለይተው ማስቀመጥ እንዳለባቸው በመጥቀስ ይዘረዝራል። ከዚህ ሌላ ማንኛውም መገናኛ ብዙኀን ምርጫን በሚመለከት ዜናዎች፣ ቃለ ምልልሶችና መጣጥፎችን ምርጫን በሚመለከት ዘገባ ማውጣት አለበት ይላል። ይህም ግዴታ የመጣል አዝማሚያ ሲሆን እንደተቋቋመበት ዓላማና እንደ ይዘት ምርጫው መሥራት እንዳይችል በማድረግ የሚዲያ ነፃነትን የመጋፋት አዝማሚያ የሚያሳይ ነው።

ከዚህ ሌላ በምርጫ ውስጥ ያሉ ተዋናዮችን በሙሉ አካቶ ኀላፊነትና ግዴታቸውን ያስቀመጠ አይደለም።

በአጠቃላይ እነኝህና ሌሎች ያልተዘረዘሩ ክፍተት እንዳሉበት በማመንና፣ የማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ አሁን ከምናየው የሚዲያ ነፃነት የተሻለ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ምርጫው በሚቀጥለው ዓመት እንደሚካሔድ ካመንን የመረጃ ነፃነትን የሚመለከተውን ይህንን መመሪያ ለማየት፣ ተግባራዊነቱን ለመፈተሸ ጊዜው አሁን ነው። ይህ ተግባር ተጀምሮ ቢያንስ የሥነ ምግባር መመሪያን ሥራ ለጋዜጠኞች በመተው ከላይ የጠቀስኩትን የአፍሪካ ኅብረት መመሪያ በሞዴልነት ተጠቅሞ አጠቃላይ የመረጃ ነፃነት ሁኔታን በምርጫ ውስጥ ስለሚካሔድበት ሁኔታ የሚዘረዝርና ሁሉንም ተሳታፊ አካላት የሚገዛ፣ የመገናኛ ብዙኀንና ጋዜጠኞች የተሳተፉበት መመሪያ ማውጣት የግድ ይላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here