በሰቆጣ የመኖሪያ ቤት ዕጣ አወጣጥ ጥሰት ተፈጽሞበታል ተባለ

0
507
  • አስተዳደሩ በመመሪያው መሰረት ነው የሰጠሁት ብሏል

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ለማይታወቁ 6 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በመስጠቱ የተደራጁ እና ወረፋ በመጠበቅ ላይ የነበሩ ማኅበራት ቅሬታቸውን አቅርበዋል። አስተዳደሩ መሬት ከሰጣቸው 16 ማኅበራት ውስጥ የምናውቃቸው ስድስቱን የመምህራን ማኅበራትና ኹለቱን የተመላሽ መከላከያ ሠራዊት አባላት ማኅበራትን ብቻ ነው ሲሉም ወቀሳቸውን አቅርበዋል።

ለሰቆጣ አስተዳደር ቅሬታቸውን ያቀረቡት ማኅበራቱ እንደሚሉት፣ ከ2008 ጀምሮ የተደራጁ ማኅበራት እውቅና ሳይሰጣቸው መቼ እንደተደራጁ በውል የማይታወቁ ማኅበራት ዕጣ ወጥቶላቸዋል። ከጥቅምት ወር 2011 ጀምሮ በ16 ማኅበራት የተደራጁ 324 ግለሰቦች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ዕጣ ደርሷቸዋል። ከእነዚህ ማኅበራት ውስጥ ስድስቱ መቼ እንደተደራጁ እና እንዴት ዕጣ እንደወጣላቸው የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል። በመሆኑም መመሪያው እና ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲደረግ ሲሉም ጠይቀዋል።

በተነሱት ቅሬታዎች ላይ ምላሽ የሰጡን የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ኀላፊ በኀይሉ መኮንን፣ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ ሕጋዊ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መሆኑን ገልጸው፣ ዕጣው ከመውጣቱ በፊት ቦታ ያላቸውንና የሌላቸውን ማኅበራት ለይተን የማስተቸት ሥራ ሰርተን ነው ወደ ትግበራ የገባነው ብለዋል።

ማንኛውም ቤት ፈላጊ እውቅና የሚሰጠው በመመሪያው የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት በማሟላት የምስክር ወረቀት የያዙ እንዲሆኑ እንደሚደነግግ ያስታወቁት አስተዳዳሪው፣ በመሆኑም ከተማ አሥተዳደሩ ከዚህ ቀደም ያደርግ እንደነበረው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ በአግባቡ የቆጠቡ እና የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ሙሉ በሙሉ ያሟሉ ማኅበራት ቅድሚያ እውቅና አግኝተው እጣ የወጣላቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን የአሠራር ክፍተት በመኖሩ፣ የማጣራት ሥራ ተሰርቶ አንድ ማኅበር እንዲታገድ መደረጉንና ጉዳዩም በሕግ እየታየ መሆኑን አስተዳዳሪው አስታውቀው፣ ሌላም ችግር የፈጠረ ማኅበር ካለም የማጣራት ሥራ ከተሠራ በኋላ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተናግረዋል።

የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ዕጣ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ከማኅበራቱ ቅሬታዎች እየተነሱ መሆናቸውን ያስታወቁት በኀይሉ፣ ለቅሬታ አቅራቢዎች ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ መፍትሔ ለመስጠትም ኮሚቴ ተቋቁሞ እያጣራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በተጀመረው ምርመራ መሠረት የሕግ ክፍተት የተገኘበት ማንኛውም ሰው በሕግ አግባብ የሚጠየቅ ይሆናል ብለዋል። መፍትሔውም በተቻለ ፍጥነት እንዲሰጥ እየተደረገ ሲሆን በአንደኛው ማኅበር ላይ የተወሰደውን ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ በሌሎችም ላይ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በሰቆጣ ከተማ በነዋሪውና በማኅበራቱ የሚነሱትን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አስተዳደሩ ዘግይቷል የሚሉ ቅሬታዎች መበራከታቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here