የውጪ ባለሀብቶች በሚዲያ ውስጥ እስከ 25 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ሕግ ተረቀቀ

0
461

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተዋቀረው የሕግ አማካሪ ጉባኤ ሥር የሚገኘው የሚዲያ ሕግ አርቃቂ የሥራ ቡድን ቅዳሜ፣ ሰኔ 1 በቢሾፍቱ ከተማ ባካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ይፋ ያደረገው የሚዲያ ሕግ የመጀመሪያ ረቂቅ የውጪ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ ሚዲያ ላይ እስከ 25 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ደነገገ።

“የመገናኛ ብዙኀን ነፃነት አዋጅ” በሚል ተሰይሞ በተለያዩ ሕጎች ተበታትነው የቆዩ የሚዲያ ሕጎችን የሰበሰበው ረቂቅ ካሻሻላቸው መሰረታዊ ድንጋጌዎች መካከል ሥም ማጥፋትን ለሚዲያ በወንጀል የማያስጠይቅ እንዲሆን ማድረጉ ነው። ለዚህም ቢበዛ እስከ 100 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ በማስቀመጥ ማንኛውም ተበዳይ በፍትሃ ብሄር ይጠይቃል። ለህትመት ውጤቶች ተፈፀመ በተባለው ድርጊት ጀምሮ እስከ አንድ አመት ድረስ ለብሮድካስት ደግሞ እስከ ስድስት ወር ድረስ ባለው ቅሬታ አቅራቢዎች ካላመለከቱ መብቱ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል።

በተጨማሪም በረቂቁ በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው በእስር ሳይቆይ ክስ የመሚሰረትበት ሲሆን በእስር ማቆየት ካስፈለገ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ እንዲወስን ተደርጎ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጎ ክሱ በቀጥታ ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት።

በተጨማሪም ክሱ ከተመሰረት በ15 ቀናት ውስጥ እንዲነበብ የማድረግ ኀላፊነት የተጣለበት ፍርድ ቤቱ ክሱ መሰማት ከጀመረበት ቀን አንስቶ እጅግ ቢበዛ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፍርድ መስጠት ይኖርበታል።

ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራሞችን በተመለከተም ሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች ተገቢ ክብር እንደተሰጣቸው ሊያረጋገጥ፣ የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነትን ሊያስከብር እና መሠረታዊ ሰብኣዊ መብቶችን ሊጠብቅ ይገባል።

“ማንኛውም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም በኃይማኖቶች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን ኃይማኖት ወይም እምነት ማንኳስስ፣ ወይም በኃይማኖቶች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀሰቅስ የለበትም።”

በተጨማሪም መገናኛ ብዙኀን በመረጡት መንገድ ራሳቸውን ማደራጀት እንደሚችሉ የሚደነገግው የመጀመሪያ ረቂቁ ከዚህ ቀደም በማኅበር ያነሳ ነው።

ከሚሰጡት የተለያዩ ዓይነት የብሮድካስት ፈቃዶች ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ማግኘት የማይቸሉ ተብለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀመጡ ሲሆን ማንኛውም ዲጂታል ብሮድካስት ሚዲያ ጎን ለጎን የአናሎግ ብሮድካስት የመያዝ ግዴታ አለበት።
አዲስ የሚቋቋመውን የሚዲያ ኤጀንሲ በተመለከተም ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሁሌም ተቃራኒ ጾታ እንዲኖራቸው የሚስገድድ ነው።

በባለሥልጣኑ እንዲተዳደር አዲስ አሠራር የሚያቀርበው ረቂቁ በሚዲያው ኢንዱስትሪ ሲነሳ የቆውን ራስን የመቆጣጠር መብት ያካተተ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አባቱም ከመንግሥት ውጪ የሚመረጡ ናቸው። ዘጠኝ የቦርድ መቀመጫ ያለው አወቃቀር አምስቱ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የሚዲያ ባላሞያዎች እና ከተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍል የሚወጣጡ አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ መሆን እንደለባቸው ያስቀምጣል።

ቀሪ አራት አባላቱ ኹለት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም የሕግ አስፈፃሚው ተወካዮች ሆነው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቅራቢነት በፓርላማው ይሾማሉ።

እጩ የቦርድ አባለት ከሚዲ ሥራ ጋር የተያያዘ የትምህርት ዝግጅት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ረቂቁ የፖለቲካ ፓርቲ ኀላፊ ወይም ተቀጣሪ የሆነ ማንኛውም ሰው የቦርዱ አባል መሆን አይችልም።

ለኅትመት ሚዲያው ተከልክሎ የነበረው በግለሰብ ደረጃ ባለቤት የመሆን መብትን በማሻሻል “ዜጎች በግል ወይም የሰውነት መብት በሕግ በተሰጠው ድርጅት በየጊዜው የሚወጣ ኅትመት በባለቤትነት ለማቋቋም ይችላሉ” ሲል ቀይሯል። በተጨማሪም በብሮድካስት ሥራ ላይ ለመሠማራት ግን የሕግ ሰውነት መኖር ወይም ድርጅት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ይደነግጋል።

ምንጭ ላለመግለጽ መብት የሚነሱበትን አግባብ የሚያብራራው ረቂቁ ጋዜጠኞች ማንነቱ እንዳይገለጽ በማድረግ መረጃ የተቀበሉትን ሰው ማንነት የመግለጽ ግዴታ የሌለባቸው ሲሆን ፍርድ ቤት አስገዳጅ ምክንያቶች አሉ ብሎ ሲያምን እንዲገልፁ ሊያዝ ይችላል። አዋጁ አስገዳጅ በሚላቸው ሁኔታዎች ምክንያት በፍርድ ቤት የተሰጠውን የመረጃ ምንጭ የመግለፅ ግዴታ ባለመቀበል ምንጫቸውን ላለመግለጽ የሚወስኑ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለማክበርና ከገንዘብ ቅጣት በዘለለ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደማይችልም ያብራራል።

በሚዲያው ባለሞዎች ተራማጅ የተባለለት ይህ የመጀመሪያ ረቂቅ በተደረገው ውይይት በተገኙ ሐሳቦች እንዲዳብር ከተደረገ በኋላ ቀጣይ ረቂቆች ተዘጋጅተው የመጨረሻው ቅጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይላካል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here