የሐረር ሕይወት ፋና ሆስፒታል ግንባታ መዘግየት ቅሬታ ቀረበበት

0
851

ግንባታው ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረውና የአራት ዓመት ተኩል የመጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ የተያዘለት የሐረር ሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ግንባታው በመዘግየቱ ከማኅበረሰቡ ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል። ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፤ አሁን በሐረር ከተማ የሚገኙት ኹለት ሆስፒታሎች ከተጠቃሚዎች ቁጥር አንፃር አገልግሎታቸውን የማዳረስ አቅም ስለሌላቸው የሚፈለገውን ያክል ግልጋሎት እያገኙ እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል።

በከተማዋ የሚገኘው አንድ ሪፈራል ሆስፒታል በመሆኑ ለሐረር ከተማ እና ከአጎራባች ገጠር ቀበሌዎች ለሚመጡ ታካሚዎች በቂ አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ ገልፀው በዚህም ምክንያት ወደ ድሬዳዋ በመሔድና እና አልፎ አልፎም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሕክምና እንደሚያገኙ አስረድተዋል። ራቅ ያሉ አካባቢዎች ለሕክምና በመሔድ የሚጠፋው ገንዘብና ጊዜም እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ በላይ በመንገድ ላይ የሚሞቱም ሕመምተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የቀረቡትን ቅሬታዎች በሚመለከት የስፔሻላይዝድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሔኖክ ሙሉነህ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ ከኅብረተሰቡ የተነሳውን ቅሬታ ተገቢና የሚጠበቅ እንደሆነ ጠቅሰው የተለያዩ ምክንያቶች ለግንባታው መዘግየት አስተዋጽዖ አድርገዋል ብለዋል። በተለያዩ ጊዜያት የኀላፊዎች መቀያየር ለግንባታው መዘግየት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚገልፁት ሔኖክ፤ በዘገየ ቁጥር ደግሞ የግንባታ ግብዓቶች በተጓዳኝ መጨመር ሌላኛው ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል። ከአስተዳደራዊ ክፍተት የተነሳ ለሆስፒታሉ የመጣው የካንሰር ሕክምና መሣሪያ ሳይገጠም ለአንድ ዓመት መቀመጡንም ጨምረው ገልፀዋል።

በቅርቡ ከፍተኛ መነቃቃት በክልሉ መንግሥት መታየቱን ተከትሎ ተቀዛቅዞ የነበረው የሆስፒታሉ ግንባታ እየተፋጠነ እንደሆነና 80 በመቶ የሚሆነው ግንባታ መጠናቀቁን ኀላፊው ያስታወቁ ሲሆን የዚህ ሜጋ ፕጀክት አካል የሆነው የካንሰር ሕክምና ማዕከል በያዝነው ዓመት መገባደጃ ላይ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ከኀላፊው አስተያየት በተቃራኒ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳልሆነና ተጨማሪ ዓመታትን ይፈጃል ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል።

አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ በጀት የተያዘለት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በመካከለኛ እና ምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የማይኝለትና ብቸኛው የካንሰር ሕክምና የሚሰጥበት ማዕከል እንደሚሆን የተነገረለት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ በውስጡም አንድ ሺሕ አልጋዎችን እንደሚይዝ ይጠበቃል። ግንባታው በአፍሮ ፂዮን የግንባታ ተቋራጭ የሚከናወነው ሆስፒታሉ ጠቅላላ የጊቢው ስፋት 70 ሺሕ ካሬ ይሸፍናል። ሆስፒታሉ 9 ሺሕ ካሬ ላይ ያረፈ ሲሆን ዐሥር ፎቅ እና ሦስት ከምድር በታች ቤቶች እንደሚኖሩትም ይጠበቃል። ስምንት አሳንሰሮች እና ዐሥር ደረጃዎች የሚኖሩት ይህ ሆስፒታል የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ 360 ክፍሎችም ይኖሩታል ተብሏል።

ግንባታው አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ጠይቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here