የሰኔ 16 ተቀናቃኝ ትርክቶች ከሰልፉ እስከ ዐቃቤ ሕግ ክሶች

0
626

ከጠዋቱ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ በሮቿን ወለል አድርጋ የከፈተችው አዲስ አበባ “ለውጥን እንደግፍ ዲሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በዘለቀ የሕዝብ ተቃውሞ በተፈጠረው ጫና የመጣውን ለውጥ ለማወደስ የተሰበሰቡ ሚሊዮኖችን ማስገባት ጀምራለች። ‘በይሆናል፣ አይሆንም’፣ ‘በሰላም ያልቃል አያልቅም’ እና ‘ችግር ይፈጠራል፣ አይፈጠርም’ ሥጋት ተወጥረውም ቢሆን የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዙሪያ የመጡት ሰልፈኞች ያለወትሯቸው ፅድት ባሉት የአዲስ አበባ መንገዶች መትመማቸውን ተያይዘውታል።

ሰልፉ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተደረጉ ካሉ ተመሳሳይ ሰልፎች በተለየ ከፍተኛውን ትኩረት ስቦ ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገኛሉ ተብሎ መታሰቡ ለዚህ አበርክቷል። በቀጥታ ስርጭት በተለዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በቅርበት ከመከታተላቸውም ባለፈ የዓለም ዋና ዋና መሠረታዊ የብዙኀን መገናኛ አውታሮች ሁነቱን ለመዘገብ መስቀል አደባባይ ገብተዋል።

ሰልፈኞች ከ150 ብር እስከ 300 ብር ሲቸበቸብ የከረመው እና የጠቅላዩን ፎቶ የያዘውን ካኒቴራ በመልበስ እና የተለያዩ መፈክሮችን በማንገብ የተሰማቸውን በመግለጽ ከሰልፉ ሰዓታትን አስቀድሞ አደባባዩን ማጥለቅለቅ ጀምረዋል።

ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከሦስት ወር በኋላ በአጭር ቀናት ውስጥ ተሰናድቶ ወደ 2 ሺሕ ገደማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ እና ቁጥሩ ላይ መሥማማት ባይኖርም እስከ ሚሊዮኖች የተገኙበት ሰልፍ ሆኖ አልፏል።

ሰልፉ ለምን ተዘጋጀ?
ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሥዩም ተሾመ የሰልፉ ቅፅበታዊ ምክንያት የተደራጁ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው እና የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ መደረጉ ነው ይላሉ። አክቲቪስት እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ሥዩም ከአንዴም ኹለቴ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸው “ነጻ ያወጣኝ ዐብይ ነው፤ ይህ ለውጥ ለኔ የግል ጉዳይ ነው። በምንም እንዲቀለበስ አልፈቅድም፤ ለዛም ነው ሰኔ 16 እንገናኝ ያልኩት” ይላሉ።

በሌላ በኩል አክቲቪስት እና የሚዲያ ባለሞያው ዳንኤል ብርሃኔ ሰልፉ አዘጋጆቹ እንደሚሉት ሳይሆን በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተጠራ እና ምክንያቱም ሕወሓት ላወጣችው መግለጫ ምላሽ መስጠት ነው ይላሉ። ሕወሓት ከማዕከላዊው ሥልጣን ወደ ክልል ከሔደችበት ጊዜ አንስቶ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሳታሰማ ቆይታ በኢትዮ-ኤርትራ እና የመንግሥት ንብረት የሆኑ ኩባንያዎች ወደ ግል የመዞር ውሳኔ ይፋ መደረግን አስመልክቶ ባወጣችው መግለጫ የተፈጠረ ሥጋት ነበር ይላሉ። እንደ ዳንኤል ሰልፉ የድጋፍ ማሳያ ፉክክር የታየበት እና ሕወሓት የጋራ ጠላት የተደረገበት ነበር።

ሥዩም በበኩላቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ከምርጫ 97 በኋላ የሰኔ 16ቱ ሰልፍ ፍርሐቱን ሰብሮ የወጣበት እና መብቱን ባደባባይ የተገበረበት ነው ይላሉ። የሰልፉ መሪ ቃል በሚያዚያ 30/1997 እሁድ ቀን ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ በጠራው የድጋፍ ሰልፍ ከነበረው መሪ ቃል የተወሰደበት ዋነኛ ምክንያቱም ሰልፉ ካለው ትርጉም ባሻገር ነው ይላሉ።

ዳንኤል በተቃራኒው በኢትዮጵያ ታሪክ ማንም ሰው በሥልጣን ላይ ያለን መሪ ለመደገፍ ወጥቶ ሰልፍ ተከልክሎ አያውቅም ሲሉ ይሞግታሉ። ምንም እንኳን የሰልፉ ርዕስ ‘ለውጥን እናወድስ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ’ ቢሆንም በተለያዩ የመገናኛ ብዘኀን እንዲሁም በመንግሥት ዘንድ የድጋፍ እና ምስጋና ሰልፍ በመባል ተደጋግሞ ተጠርቷል፤ ይጠራልም።

“የዴሞክራሲ ዋና ፅንሰ ሐሳብ፣ በተለይም እንደኛ ባሉ ድሃ አገራት ውስጥ ለውጥ እና መሻሻል ማለት ነው” የሚሉት ሥዩም “ለውጡ የዜጎችን እኩል መብት እና ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የሕግ የበላይነት፣ እና ፍትሐዊ ሀብት ክፍፍልን ያከበረ ቀጣይ ተቋማዊ ለውጥ ማስቀጠል ሲቻል ነው” ይላሉ።

አክለውም አብዛኛው የሰልፉ ተሳታፊ የነበረ ሰው አሁን መሪ ቃሉን ባያስታውሰውም እንኳን ታሪካዊ የአብሮነት ፌስቲቫል ነበር ብለው ማመናቸውን ይናገራሉ።
ዳንኤል ግን አብዛኛው የሰልፍ ተሳታፊ ዐቢይን ደግፎ የወጣ ቢሆንም፥ ቀላል የማይባለው ደግሞ ፋሽን በመከተል ወይም ከብዙኀኑ ተነጥሎ ላለመታየት ነው ሲሉ ይናገራሉ። ሰልፉ ወይም ባጠቃላይ በግዜው የነበረው ድጋፍ የጋራ ጠላት ተደርጎ በተወሰደው ሕወሓት ላይ የተመሠረተ እንጂ የዓላማ መሥማማት የፈጠረው አልነበረም ይላሉ። ዳንኤል አክለውም ወቅቱን ያልጠበቀ እና የፀጥታ ችግር ሊኖር እንደሚችል እየታወቀ እና አዲስ የፀጥታ መዋቅር ተይዞ መደረግ ያልነበረበት ነበር ብለዋል።

ፍንዳታው
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምሥል በተለየዩ ቀለማት ካኒቴራዎች ላይ አትመው በለበሱ ሚሊዮኖች ፊት እርሳቸው ደግሞ በአፍሪካ ካርታ ላይ እጃቸውን ወደላይ በመዘርጋት የድል መልክት የሚያሳዩትን የኔልሰን ማንዴላ ምስል ያለበት አረንጓዴ ካኒቴራ ለብሰዋል። በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የታጀቡት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በአራቱም አቅጣጫ ለከበባችው ሕዝብ ሰላምታ ሰጥተው ከባቡር ሐዲዱ ሥር ባለው መድረክ ላይ ተሰይመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን አድርገው እስኪጨርሱ ድረስ በመጨናነቅ ታፍነው ራሳቸውን ከሳቱ ነፍሰጡር እና ሕፃናት ውጪ ቦምቡ እንከፈነዳበት ሰዓት ድረስ ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ ነበር።

“አንድ የመጨረሻ ፕሮግራም ይኖረናል” የሚለው የመድረክ አጋፋሪው ግሩም ጫላ በእግሊዝኛ “This is the day that Ethiopians are proud.” (‘ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ቀን ነው’) እንዳለ፥ እምብዛም ድምፁ የማይሰማ ፍንዳታ ነገር ተሰማ። አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች የፕግራሙ አንድ አካል ነበር የመሰላቸው “ይደገም” ያሉ ወጣቶች ነበሩ። ረጅም ጭስ ከመድረኩ በስተቀኝ ወደላይ ከመሔዱ ባሻገር በቦታው ያለው ሰልፈኛ ወደ ሌላ አካበቢዎች መትመም ጀምሯል።

ከመቀፅበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች ባለሥልጣናት በጠባቂዎቻቸው ተመንትፈው ከመድረክ ተሰወሩ። ከመድረክ ከሚሰሙ የማረጋጊያ ድምፆች ባሻገር፥ ሰልፈኛው እርስ በእርስ የማረጋጋት ሥራ ይሠራ ጀመር። በተለይ ጉዳቱን የተመለከቱ ሰዎች ወዳልተመለከተው በመሔድ እርስ በእርስ መረጋገጥ እንደይኖር ሲያረጋጉም ነበር።

የፀጥታ አካላትም ያለወትሯቸው ወደ ዳር በመውጣት ቆመው ከመመልክት ባለፈ እንደዚህ ቀደሙ “ተበተኑ” ወይም “ተሰብሰቡ” ከማለት ተቆጥበው ዳር ላይ ሆነው ይመለከታሉ።

“ኢትዮጵያን ፈጣሪ እንደሚወዳት ያወኩበት ቀን ነው” የሚሉት ሥዩም “ሚሊዮኖች በወጡበት ሰልፍ ቦንብ ፈንድቶ ኹለት ሰው ብቻ ሞተ ማለት ተዓምር ነው። በርግጥ የኹለቱ ሰዎች ሞት ለኔ በሕይወቴ ሁሉ የማልረሳው ጠባሳ ሆኖ ይኖራል” ብለዋል።

ቦንቡን ማን አፈነዳው?
“ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለጠሩት ሰልፍ ዓላማ ደጋፊ የሚያበዛ እና ዓላማውን የሚያግዝ ነው” ሲሉ ዳንኤል ስለቦንቡ መፈንዳት ይናገራሉ። “ጠቅላይ ሚኒስቴሩ መግለጫ የሰጡበት ፍጥነት ማንም ያርገው ማን ቀድሞ የታቀደ መሆኑን ያሳያል። እንደዚህ ዓይነት የግድያ ሙከራ ሲኖር እንኳን ሚዲያ፥ የሚያምኗቸው ሚኒስቴሮችም የማያውቁት ቦታ መወሰድ ነበረባቸው።”

“ምናልባት ቤተ መንግሥቱ ሰላሙ የተጠበቀ ቦታ ነው ቢባል እንኳን፥ በዛ ፍጥነት የቀጥታ ስርጭት መሣሪዎች ተወሰድው ስለወንጀሉ ሁኔታ መረጃ ይዞ ማብራራት ለጥርጣሬ ይዳርጋል” ሲሉ ይናገራሉ። በዚህ ንግግራቸው ላይም “የከሰሩ እና የተሸነፉ ኀይሎች” ብለው ጣታቸውን ወደ ትግራይ ሕዝብ የጠቆሙበት እና በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከልም መቃቃር የተፈጠረበት ነው ይላሉ።

ዳንኤል በፌስቡክ ገጻቸው ስለተወረወረው ቦንብ ኤፍ ዋን ነው ብለው በመጻፋቸው ምክንያት የተለያ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረው ቃሉን የተጠቀሙትም ሁሉንም ጠመንጃ ክላሽ እንደሚባለው ማንኛውንም ፈንጂ ኤፍ ዋን ብሎ መጥራት የተለመደ ስለሆነ ነው እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉት ቀድሞ መረጃ ስላለኝ አይደለም ይላሉ።

ሥዩም ግን “ጥፋቱን ያደረሱት ሰዎች የተቃውሞ ሰልፋቸው የከሸፈባቸው እና ለድጋፍ የወጣው ሰው ምንም ግድ የማይላቸው እና ጠቅላይ ሚኒስቴሩም እንዳሉት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበሩ እና አጀንዳቸው የከሸፋበው ግለሰቦች ናቸው” ይላሉ።

ክሱ ምን ይላል?
ምንም እንኳን ዳንኤል እና ሥዩም በተለያየ ጎራ ላሉ ሰዎች ኀላፊነቱን ቢሰጡም፥ ፍርድ ቤት ላለፈው አንድ ዓመት ጉዳዩን በመመልከት ላይ ነው።
ከቦንብ ፍንዳታው ጋር በተያያዘ በአንድ መዝገብ ኹለት ክሶች የቀረቡ ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹ አራት ተከሳሾች ጌቱ ግርማ፣ ብርሀኑ ጃፋር፣ ጥላሁን ጌታቸው እና ባሕሩ ቶላ ሲሆኑ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ጥቃት ለመፈፀም በመዘጋጀት እና በመደራጀት ወንጀሉን ፈፅመዋል ብሎ ዐቃቤ ሕግ ክሱን መሥርቷል።

ክሱ እንደሚለው ከሆነ ዐቢይ ተቀባይነት የሌለው እና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የማይፈልግ መሆኑን ለማሳየት በሚያስችል መልኩ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሥም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ጥቃቱን አስተባብረውታል። ለዚህም ኑሮዋን በኬኒያ ያደረገችው ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) ዕቅድ በማውጣት እና ከቡድኑ ጋር በመሥማማት ሰኔ 16/2010 በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጥቃት ለማድረስ እና ሰልፉን ለመበተን የቦንብ ጥቃት በማድረስ ተጠርጥረው ክሱ ተመሥርቶባቸዋል።

በኹለተኛው ክስ ላይ ሥሙ ያረፈው አምስተኛ ተከሳሽ ደሳለኝ ተስፋዬ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም እንደሆነ እያወቀ፣ እንዲሁም ወንጀሉን ሊፈፅሙ የተዘጋጁት ተከሳሾችን ለማስያዝ የሚያስችል መረጃ እያለው ለፖሊስ መጠቆም ሲኖርበት ባለመጠቆሙ ክስ ተመሥርቶበታል። የቦንብ ጥቃት ለመፈፀም የተዘጋጁትን ሰዎች በመኖሪ ቤቱ በማሳደር፣ ለጥቃት የተዘጋጀውን ቦንብ ሲቀባበሉ እንዲሁም ተልዕኮውን ሲቀበሉ ጥቃቱን ለመፈፀም ወደ መስቀል አደባባይ ሲሔዱ እያወቀ ይህንን ለፖሊስ ባለማሳወቁ እርሱም የሽብር ድርጊትን ባለማሳወቅ ተከሷል ተብሏል።

ጌቱ ግርማ ወንጀሉን ካቀነባበረችው ገነት ወይም ቶለሺ ጋር በስልክ በመገናኘት መልዕክት እንደተቀበሉ ክሱ ያስረዳል። በተጨማሪም ጌቱ ከኹለተኛ ተከሳሽ ብርሀኑ ጃፋር ጋር ስለ ተልዕኮው በመነጋጋር እንዲሁም ቦንቡ እንዲዘጋጅ እና ቦንቡን የሚወረውረው እንዲያፈላልግ ከመነጋገራቸው ባለፈ ለሦስተኛ ተከሳሽ ጥላሁን ጌታቸው በዚህ ነገር ላይ እንዲሳተፍ ተልዕኮ መስጠታቸውንም ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል።

በዕለቱ በተፈፀመው ወንጀልም ሰልፉን በመቀላቀል በሦስተኛው ተከሳሽ አማካይነት ቦንቡን በማፈንዳት በኹለት ግለሰቦች ላይ የሞት፣ እንዲሁም ከ1 መቶ 14 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ማድረሳቸውም በክሱ ተጠቁሟል።

ተከሰሾች የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለው የተከራከሩ በመሆኑ፥ ዐቃቢ ሕግ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀማቸው ያስረዱልኛል ያላቸውን 140 የሰው እና 17 የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም የቀረቡለትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሰምቶ በመመርመር ግንቦት 29/2011 ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ በተጠቀሰባቸው የሕግ ድንጋጌ ሥር እንዲከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል። ተከሳሾቹም የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርበው እንዲያሳዩ ሲል ለሰኔ 25/2011 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ለውጥ አለ ወይ?
ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ነጻ አገር ያደረገቸውን ሽግግር እንደምሳሌ የሚያነሱት ሥዩም በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መኖሩን እና በዚህ የሽግግር ወቅት እየደረሱ ያሉ ግጭቶችም የሚጠበቁ ናቸው ይላሉ። ደቡብ አፍሪካ በአፓርታድ ውስጥ በቆየችባቸው ዓመታት ከሞተው ሰው ይልቅ እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 1994 ድረስ ያለቀው ከ14 ሺሕ በላይ ሕዝብ ይበልጣል ይላሉ።

ኔልሰን ማንዴላ መሪ ሆነው እስኪመረጡ ድረስ ባሉ አራት ዓመታት ውስጥ በጎሳዎች መካከል ሲነሱ በነበሩ ግጭቶች አሰቃቂ እልቂቶችን ያሳለፈችውን ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያመሣሥላታል የሚሉት የአፓርታይድ ጀነራሎች እና ደኅነነት አመራሮች ተመሳሳይ ፈተና ስለነበሩ ነው ይላሉ።

“በኢትዮጵያም ተመሳሳይ የአፓርታይድ ስርዓት ተዘርግቷል” የሚሉት ሥዩም እንደ ምሣሌነት ጥልቀት ያለው ችግር ከታየባቸው የአገሪቱ ክፍሎች መካከል በጌዲዖ እና በጉጂ መካከል የሆነውን ያነሳሉ።

ሥዩም ለውጡ የሚኮነንበትን የአገር ውስጥ መፈናቀል አሳንሰው እንደማይመለከቱት እና አፋጣኝ እርምጃ እንደሚያስፈልገው ቢያምኑም ለ20 ዓመታት የተገነባውን የአፓርታይድ ግንብ ግን እንዲሁ በአንድ ዓመት መለወጥ የሚቻል አይደለም ይላሉ። አክለውም ለውጥ ውስጥ ያለ ማንም ሰው ጥያቄ ይነሳበታል፤ ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ ከቻለ ይቀጥላል። ችግር የሚመጣው ለውጡ የቆመ ዕለት ነው ይላሉ።

አሁን “የአክሱምም፣ የወሎም ሰው ሲጠይቅ መልስ ይሰጠዋል” የሚሉት ሥዩም “በፊት ግን ምን አለ? የት ዋለ? እየተባለ እግር እግራችንን ሲከተሉን እንዳልነበር አሁን ‘ለውጥ አለ፣ የለም’ የሚለውን እንደልባችን በሚዲያ እንደዚህ እንወያያለን”ም ብለዋል።

ዳንኤል ግን ገና ብዙ ድርድሮች መደረግ አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ እና በተለይ በአራት ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተቀመጠ ለውጥ አለ ለማት እንደማይችሉ ይናገራሉ።

በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የጦርነት ሥጋት ቢቀንስም ግንኙነቱን ግን በሕግ እና ስርዓት ላይ የተመሠረተ ማድረግ ይቀራል ይላሉ። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይም በተለይ ከመንግሥት በጀት በፍጥነት መድቦ በራሳቸው የሚተማመኑ እና ለጥቅም ያላደሩ ፓርቲዎችን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። የጋዜጠኞች እስር መቀነሱ እና የሙያዊ ነጻነቱ መሻሻል አሳይቷል ቢሉም የሚዲያ አዋጁን በፍጥነት በማፅደቅ እና በተለይም ለኅትመት ሚዲያው የወረቀት ዋጋን በመቀነስ አቅማቸውን ማዳበር መጀመር አለበት ይላሉ። የታጠቁ ፖለቲከኞችን አገራቸው መግባታቸው ቢያደንቁም፥ ከገቡ በኋላ ግማሹ ካምፕ ግማሹ ጫካ ሆኖ የተዘበራረቀ አካሔድ መኖሩ ለውጡን ምልክታዊ እንጂ ገቢራዊ አያደርገውም ሲሉ ይናገራሉ።

ዳንኤል ሕውሓትን የለውጡ እንቅፋት የማድረግ አዝማሚያዎች ቢኖሩም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊነቱን አሳልፎ የሰጠ ሌላ ክልል የለም ሲሉም ይሞግታሉ። ሕወሓቶች ለሌሎች ክልሎች ወንጀለኛ መደበቅን አስተምረዋል የሚለውን ወቀሳም ድርጊቱ የመጥፎ ምሳሌነት መጀመሪያ የትግራይ ክልል አይደለም፤ በጎንደርም ይሔ ከዛ በፊት ታይቶ ነበር ይላሉ።

“ለውጥ የለም ለማለት አይቻልም፤ ነገር ግን ግርግሩን ከሽግግር ለመለየት አሁንም ውይቶች አና ድርድሮች በርትተው መካሔድ አለባቸው” ብለው ያጠቃልላሉ።
ሥዩም በበኩላቸው ሰልፉን በመጥራቴ አሁንም ደስተኛ ነኝ። ሕይወታቸው ያለፈው ልጆች ነገር ብቻ ዘወትር ይከክነኛል። “በሕይወቴ የምኮራበት ታሪካችን ነው። ኅብረ ቀለሙ፣ ጭፈራው እና ተስፋው ሁሉ ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው” በማለት ያስታውሱታል። በተጨማሪም ለውጡ ይቀጥላል ብለው እንደሚያምኑ እና ካልቀጠለ ግን መንግሥት ወይ በምርጫ አሊያም በአመፅ ይወርዳል ሲሉ ይደመድማሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here