’ሴትነትን’ እንደ ሥራ ማስገኛ መንገድ

0
795

በሥራ ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት በብዙ የዓለማችን ክፍል የሚደርስ ድርጊት በመሆኑ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀሩ የሚዘግቡት ጉዳይ ነው። ሥራ ለማግኘት ውድድሩ ከፍተኛ ዕድሉ ደግሞ ጠባብ በሆነበት በኢትዮጵያ፥ አንዳንድ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ ኤምባሲዎችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ለመቀጠር ወይም የሥራ ዕድገት ለማግኘት ቀድመው ወይም ዕድሉን ካገኙ በኋላ ሴትነታቸውን በከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲያቀርቡ የሚገደዱ ሴቶች መኖራቸው በብዙ ይሰማል። የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ሴቶች በሥራ ላይ የሚደርስባቸውን ፆታዊ ትንኮሳ የድርጊቱ ተጠቂዎች ከሆኑት ውስጥ ኹለቱን በማሳያነት ተጠቅሞ፣ የአፍሪካ ኅብረትን ተመክሮና ሌሎች ሪፖርቶችን ተንተርሶ እንዲሁም በሴቶች መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በማናገር ርዕሱን የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ምህረት ኃይሌ (ሥሟ የተቀየረ) ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ባደረጉ በበርካታ የዓለም ዐቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች ውስጥ ከተለማማጅነት ጀምሮ እስከ ቋሚ ሠራተኛነት ብሎም የቡድን መሪነት ወይም አስተባባሪነት ደረጃ ድረስ የመሥራት ዕድል ገጥሟት ያውቃል። ይሁን እንጂ በየትኛውም ደረጃ ላይ ሆና በሠራችባቸው ዓመታት የሥራ ዘመኗ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ከውጭ አገራት ዜጎች ጋር እንደመሥራቷ መጠን ከዘመናት በፊት ተወግዷል፣ ዳግመኛ ላይነሳ ርቆ ተቀብሯል የተባለውን የዘር መድሎ በቅርበት የታዘበች እና ታግሳ ለማለፍ ትሞክር የነበረች ብትሆንም ከኹሉም አስቸጋሪው ግን በሥራ ቦታዋ በተለይም ደግሞ በአለቆቿ የሚቀርብላት ፆታዊ ጥያቄዎች ናቸው።

አዲስ ማለዳ ከግል ተበዳይ ጋር ባደረገችው ቆይታ ፆታዊ ጥያቄዎች ወይም ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በማለት ለማለዘብ የሞከረችባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ከወዲሁ ለማሳወቅ እንጂ ጉዳዩ ከዚህም ባስ ያለ ነው።

ምህረት በሥራ ቦታዎች ላይ ከአለቆች ለሴት ሠራተኞች የሚቀርበው የወሲብ ጥያቄ እና ይህንም ጥያቄ በእሺታ ለሚመልሱ እንስት ሠራተኞች ለተሻለ የሥራ ኀላፊነት እስከመታጨት የሚደርሰው አሳፋሪ ተግባር ጉዳይ ለመነጋገር በሰዓቱ በአንድ ቅምጥል መዝናኛ ሥፍራ ተገኝታለች።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት (‘ሶስዮሎጂ’) የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ2003 ያገኘችው ምህረት፥ ከመመረቋ አስቀድማ በተለማማጅነት በሕፃናት ላይ የሚሠራና በዋናነት በእንግሊዝ መንግሥት እና ሕዝብ ድጋፍ በሚንቀሳቀስ ድርጅት ውስጥ ትሠራ ነበር። “የመጀመሪያ የሥራን ሕይወት ያየሁበት ስለነበር በታላቅ ትጋትና ተመስጦ ነበር አገለግል የነበረው” ትላለች ምህረት ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዛ ትዝታዋን ስትተርክ። ታዲያ በዛ የወጣትነት፣ የአፍላ ጉልበትነት፣ ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት በምታሳየው ምህረት ላይ ከመሥሪያ ቤቷ የቅርብ አለቃዋ የሚቸራት ምላሽ ግን ከሥራ ይልቅ አድናቆቱ ወደ ተክለ ሰውነቷ መሆኑ በየቀኑ ግርምትን ይፈጥርባት እንደነበር ታስታውሰዋለች። “የቅርብ ረዳቱ ሆኜ ነበርና የተመደብኩት በየቀኑ በሰበብ በአስባቡ ቢሮው ድረስ እየጠራኝ እንቶ ፈንቶውን አውርቶ አንድም ቁም ነገር ሳይነግረኝ ያሰናብተኝ ነበር” ትላለች ምህረት። አለቃዋ ኢትዮጵያዊ ስላልሆነ ማድነቅ ባሕላቸው ይሆናል በሚል በቸልታ ታልፈው እንደነበር ከትዝታ ማህደሯን በመመርመር አዲስ ማለዳን አውግታታለች።

ቀናት በተቆጠሩ ቁጥር፥ ከቅርብ አለቃዋ የምትታዘበው ከመንገድ የወጣና ሙያዊ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እየባሰ ከመምጣቱ ባሻገር አንድ አርብ ቀን ዓይን ያወጣ የእራት እንብላ እና በዛውም የአዲስ አበባን የምሽት ቤቶች አብሮ ማድመቅ ጥያቄ ሲቀርብላት ቆሌዋ እንደተገፈፈ የምታስታውሰው ምህረት፣ “ምንም የምመልሰው ነገር አልነበረኝም። ባለሁበት ፈዝዤ ቀረሁ። ለምን ያህል ጊዜ እንደቆምኩም አላወለኩም፣ ወደራሴ የተመለስኩት ሰውየው አጠገቤ ደርሶ እጆቹን ትከሻዬ ላይ ሲያሳርፍ ነው” ብላለች የንዴት ይሁን የቁጭት በማይለይ ፈገግታ ታጅባ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ደመ ነብሷ ትከሻዋ ላይ ያረፉትን የአለቃዋን እጆች አውርዳ ከሩጫ ባልተናነሰ ቢሮውን ለቃ ወጣች። ከዛች ቀን በኋላ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ፤ ከአለቃዋ የሚደርሷት አጭር የፅሑፍ መልዕክቶች ቁጥራቸው እጅግ አያሌ እና ሥነ ምግባር የጎደላቸው እየሆኑ መጡ ገፋ ሲልም እኩለ ሌሊት ላይ አስደንጋጭ የሥልክ ጥሪዎች ይደርሷታል።

“እስካሁን የማልረሳው፥ በጣም ውድቅ ብዬ በተኛሁበት ሌሊት ላይ ሥልኬ ሲጮህ በጣም ደንግጬ ከመነሳቴ የተነሳ ሰውነቴ ይንቀጠቀጥ ነበር፤ ደዋዩን ሳየው አለቃዬ ነበር በሌሊት ደውሎ ስለማያውቅ ላንሳው አላንሳው እያልኩ ጥሪው ተዘጋ። ተሳስቶ ይሆናል በሚል ወደ እንቅልፌ ለመመለስ እያሰብኩ ድጋሚ ሲደወል አነሳሁት በጣም ጫጫታ ውስጥ ከመሆኑ የተነሳ የሚናገረው አይሰማም በአንዱ የምሽት ቤት ውስጥ ሆኖ እንደሚደውልልኝ ገባኝ። ንግግራችን በጥቂትም ቢሆን እየተደማመጥን ቀጥለን መኪና ልላክልሽና ያለሁበት ነይ ሲለኝ ጆሮው ላይ ሥልኩን ዘግቼ ሥልኬን አጠፋሁት” ስትል ብስጭቷ ጉዳዩ አሁን የተደረገ ያህል እያሳበቀባት ትናገራለች።

በእንዲህ መልኩ የተጀመረው የእኩለ ሌሊት የሥልክ ጥሪ ታዲያ አለፍ አለፍ እያለ በሳምንት እና በዐሥራ አምስት ቀን ምህረትን እንቅልፍ መንሳቱን አላቆመም። “ሌሊቱን ኹሉ ስበሳጭ አድርና በቃ በጠዋት ሔጄ ቢሮው ውስጥ አስጠንቅቄው ወይም ሰድቤው ሥራውን ለቅቄ እወጣለሁ ብዬ እፎክርና ጓደኞቼ በተለማማጅነት የገባሁበትን ቦታ ሲሰሙ የማይገኝ መሥሪያ ቤት መሆኑን ሲነግሩኝ ለማድረግ ያቀድኩትን ለማድረግ አቅም አጣለሁ” ስትል የነበረውን ሁኔታ እንዴት ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች።

እንደዚህ ዓይነት ሴት ሠራተኞችን ማዕከል ያደረጉ ከፈቃዳቸው ውጪ ወሲብ እንዲፈጽሙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መክተት ወይም ማስገደድ በተለይ መቀመጫቸውን መዲናችን አዲስ አበባ ባደረጉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ደረጃው ይለያይ እንጂ መኖሩ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ወሲብን በገፀ በረከትነት ማቅረብ የተለማማጅነት ዕድል ለማግኘት፣ ለመቀጠር ወይም የውስጥ ሥራ ዕድገት ለማግኘት አንደኛው ምናልባትም ወሳኝ መስፈርት የሚሆንበት አጋጣሚ የበዛ ነው የሚሉ ታዛቢዎች አሉ።

ለዚህ ደግሞ በተቋም ደረጃ በኅዳር 2011 ዋና መቀመጫው አዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት አንድ ጥናት ማካሔዱንና በጥናቱም አግኝቻለሁ ያላቸውን ግኝቶች ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ኅብረት ፆታዊ ትንኮሳን በተመለከተ አጣሪ ቡድን አሰማርቶ ያገኘውን ውጤትና መፍትሔ ባካተተበት ሪፖርት በርካታ የሥራ ኀላፊዎች በሥራቸው የሚሠሩ ሠራተኞችን ወሲባዊ ትንኮሳ ማድረጋቸው አረጋግጧል። ሪፖርቱ አገኘሁ ካላቸው ወደ ሰባት የሚጠጉ ግኝቶች መካከል ወሲባዊ ትንኮሳዎች በመሥሪያ ቤቴ ውስጥ ይካሔዱ ነበር ብሎ አምኗል። ኅብረቱ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራም፤ ወሲባዊ ትንኮሳዎች በተለይ ጎልተው የሚስተዋሉት በአጭር ጊዜ ሴት ተቀጣሪዎች፣ በወጣት ሴት የበጎ ፈቃድ ወይም ተለማማጅ ሴቶች ላይ ሲሆን ድርጊቱን ፈፃሚዎች ደግሞ ተቆጣጣሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች መሆናቸውንም አስታውቋል። ኅብረቱ አያይዞም ድርጊቱን ፈፃሚዎች ለሴቶች የእናስቀጥራችኋለን ቀቢፀ ተስፋ እንደሚሰጡም አስታውቋል።

ኅብረቱ ጉዳዮን የሚያጣሩ ቡድኖች ቃለ መጠይቅ ከሰጧቸው የኅብረቱ ሠራተኞች አገኘሁ ያለው ነገር እንደሚያትተው፤ በድርጅቱ ሕገ ደምብ ውስጥ ፆታዊ ጥቃትን በሚመለከት በግልፅ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ ችግሩ እንዲጎለብት ምክንያት ነው መባሉን አስታውቋል። በተመሳሳይ ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሌሎች አፍሪካ አገራትም ሥራን ከለላ በማድረግ ከፍተኛ የወሲብ ጥቃቶች በሴት ሠራተኞች ላይ እንደሚደርስ የዓለም ዐቀፍ የሕፃናት ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ኮሪና ኮዛኪ እንደማሳያ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ኮት ዲቮር በሰላም አስከባሪ ካምፕ ውስጥ የሚሠሩ ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር ዋቢ አድርገው በሐምሌ 2010 ይፋ አድርገዋል። አማካሪዋ ሴቶች ካለባቸው ድኅነት የተነሳ በመሥሪያ ቤታቸው የበላይ ኀላፊዎች የሚቀርብላቸውን የወሲብ ጥያቄ እንደ ሥራ ዋስትና በማየት እንደሚጠቀሙበትም ጨምረው ገልፀዋል።

የምህረት የተለማማጅነት ገጠመኝ ለዚህ እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል፤ የቅርብ አለቃዋ ጥያቄውን ታስተናግድ እንጂ ከተማማጅነት ወደ ቋሚነት እንዲሁም የተሻሉ የሚባሉ ክፍት ቦታዎች መኖራቸውን ይነግራት እንደነበረ ትናገራለች። እንደዚህ ዓይነት ገጠመኝ የእሷ ብቻ አለመሆኑን የምትናገረው ምህረት፥ እሷ ተለማማጅ በነበረችበት ወቅት ሌሎች ኹለት በሌላ ክፍል በተመሳሳይ ይሰሩ የነበሩ ሴቶች መኖራቸውን ታስታውሳለች።

ለሻይ እረፍት በሚያደርጉበት አንደኛው አጋጣሚ ከኹለቱ ተለማማጆች ጋር ስለዚህ ጉዳይ ተነስቶ እነሱም የዚሁ ችግር ሰለባ መሆናቸውን መናገራቸውን የምታስታውሰው ምህረት ችግሩ የእሷ ብቻ አለመሆኑ በአንድ ወገን እፎይታ እንደሰጣት አልሸሸገችም።

ኮዚና ኮናኪ በኮት ዲቮር ሰላም አስከባሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ሴቶች የሚቀርብላቸውን የወሲብ ጥያቄ መመለስ የሥራ ዋስትና እንደሚያስገኝ ካደረጉት ጥናት ያገኙትን ግኝት ምህረት ትስማማበታለች። በሥራ ቦታዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች አልፎ አልፎም በወሲብ ትስስር በአቋራጭ ከፍተኛ የኀላፊነት ቁንጮ ላይ መቆናጠጥ በቴሌቪዥን ለግንዛቤ ማስጨበጫነት ይሠሩ የነበሩ ድራማዎችን፣ ፊልሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን ተመልክታ ብታውቅም በገሃዱ ዓለም በተለይ ደግሞ “ሥመጥ” በሆኑ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በራሷ ላይ እስኪገጥማት ድረስ ይኖራል ብላ ግን እንዳልገመተች ተናግራለች።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በተቀበለች በቀናት ልዩነት አለቃዋ እስከዛሬ ሲያቀርብላት የነበረውን እና የሰለቻትን የወሲብ ጥያቄ ማስጠንቀቂያ አዘል ድምፀት ደግሞ ያቀርብላታል። ዕድሉን ብትጠቀምበት እንደሚሻላትና ካልሆነ ግን በኋላ እንደሚቆጫት፤ የቆይታ ጊዜዋ እየተገባደደ እንደሆነ ባስታወስ፤ “እውነት ለመናገር ከዚህ መሥሪያ ቤት ወጥቼ እንደገና ሥራ ፍለጋ መንከራተቱን ሳስበው ልቤ በጣም ፈርቶ ነበር” የምትለው ምህረት ይህ ሁሉ ሲሆን ለቤተሰቦቿ ምንም ነገር ተናግራ አታውቅም። አልፎ አልፎ ለወንድ ጓደኛዋ ታጫውተው እንደነበርና እሱም ሌላ ቦታ ሥራ እንድትፈልግ ወይም የኹለተኛ ዲግሪዋን እንድትማር ከመምከር ውጭ ሊረዳት የሚችለው ነገር አልነበረም።

የአለቃዋ ማስፈራሪያና “ጥያቄዬን ካልተቀበልሽ” የሚለው ዛቻውን አሻፈረኝ እንዳለች ነው። ከመሥሪያ ቤቱም ለቃ ለመውጣት የቀራት የዐሥራ አምስት ቀናት ዕድሜ ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ እንደተለመደው የሻይ ሰዓት ላይ ከጓደኞቿ ጋር እየተጨዋወተች ሳለ አንደኛዋ ተለማማጅ የልምምድ ጊዜዋ እንደተጠናቀቀ በቋሚነት በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ እንደምትቀጠርና እሷን የሚጠብቅ ክፍት ቦታ መኖሩን የሚያበስር ደብዳቤ በኢሜል ከቅርብ አለቃዋ እንደደረሳት እየተፍለቀለቀች ትነግራቸዋለች። “በጊዜው እንዴት እንደቀናንባት እኔም ሆነ ሌላኛዋ ጓደኛችን በደንብ ያስታውቅ ነበር” ትላለች ምህረት። “በቃ ዛን ቀን እንደማይቀጥሩን አውቀን ተስፋ ቆረጥን ስለዚህ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ለቀጣዩ የሥራ ፍለጋ ሕይወት ራሳችንን ማዘጋጀት ነው።” በዚህ ጊዜ ታዲያ ምህረት በአለቃዋ በኩል ልምምድ ጊዜው የተራዘመላት መሆኑን እና መቀጠል የምትፈልግ ከሆነ ቦታዋ የተጠበቀ እንደሆነ ይነገራትና ኹለት ሐሳብ ውስጥ ገብታለች። “ውሳኔው ከባድ ነው ምክንያቱም አንድም በተለማማጅነት ቀጥዬ የአለቃዬን ትንኮሳ በመጋፈጥ የሥራ ዕድል እስኪፈጠርልኝ መታገስ ወይም ለቅቄ ወጥቼ ሌላ ቦታ ሥራ መፈለግ” ስትል ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቀውን ሁኔታ ታስታውሳለች። ከብዙ ማሰላሰል በኋላ የቀረበላትን የልምምድ ቦታ ተቀብላ ትቀጥላለች። “አንድ ቀን የሥራ ባልደረባዬ በቅርብ የሥራ ማስታወቂያ መሥሪያ ቤቱ ስለሚያወጣ እንድወዳደርና በእርግጠኝነት የመሥሪያ ቤቱን የሥራ ባሕል ለሚያውቅ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ነገረችኝ” በዚህ ጊዜ ታዲያ ምህረት ሕገ ደምንቡን ተከትላ ታመለክትና ለቃል ፈተና ትቀርባለች።

በሚያስገርም ሁኔታ አብረዋት ከነበሩት ኹለቱ ተለማማጆች መካከል አንደኛዋ የተቀጠረችበት ፊርማ ሳይደርቅ ከቃለ ምልልስ አቅራቢ ፈታኞች መካከል አንዷ ሆና እንዳገኘቻትና የነገሮች በዚህ ፍጥነት መለዋወጥ እንዳስገረማት ምህረት ገልጻለች። የሆነው ሆኖ ፈተናውን አልፋ በቋሚነት ለመቀጠር የበቃች ቢሆንም ፈተናዋ ግን አለማብቃቱ ደስታዋን ቅጽበታዊ አድርጎባታል። “ሥራዬን ብወደውም ከቀድሞ አለቃዬ ጋር በድጋሜ መሥራቴን ሳስበው ግን በጣም ነው ያዘንኩት፤ ይባስ ብሎ በተደጋጋሚ የመስክ ሥራ እንዳለው እና ከከተማ እንደምወጣ ሲነግሩኝ በጣም ነው የተማረርኩት” ትላለች። በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴዋ እንደቀድሞውም ባይሆን አለቃዋ ልማዱን አልተወም። ባለፈች ቁጥር ፀያፍ ነገሮችን ይናገራታል፣ ከፍ ሲል መቀመጫዋን ይመታታል፣ ጸያፍ የሥልክ መልዕክቶችን ይልክላታል፤ በቃ ነገሮች አሁንም መልካቸውን አልቀየሩም።

ምህረትን የሥራ ላይ ትንኮሳ በተመለከተ በሕግ ለመጠየቅ ያደረገችው ሙከራ እንዳለ አዲስ ማለዳ ለጠየቀቻት ጥያቄ ትርፉ ልፋትና መጉላላት እንዲሁም የሥራ ሕልውና ማጣት ናቸው ብላለች። ትቀርባት የነበረች የካበተ የሥራ ልምድና ቆይታ የነበራት፣ እየደረሰብኝ ያለውን ነገር በቅርበት የምታውቅ ሴትን ወደ ሕግ ለመሔድ ማሰቧን ስነግራት ከዚህ ቀደም የምታውቀውን ተመክሮ እንዳጋራቻት ምህረት ትናገራለች፤ “አንዲት ሴት ተመሳሳይ ችግር ገጥሟት ወደ ሕግ ብትሔድም ያተረፈችው ነገር ቢኖር ከሥራ ገበታዋ መፈናቀልን ብቻ ነው” ስትለኝ በሕግ ላይ የነበረኝን የተስፋ ጭላንጭል ጠፋብኝ ብላ ምላሽ ሰጥታለች።

ከተቀጠረችበት ሥራ መስፈርት ስለሚያስገድዳት ምህረት በተደጋጋሚ ከከተማ መውጣት እንድታዘወትር በማድረግ አለቃዋ በሔደችበት ኹሉ ሰበብ እየፈጠረ መከተሉን ተያያዘው። ይህን የታዘቡት ባልደረቦቿ ታዲያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድታደርግ ያስጠነቅቋት እንደነበር፣ አለቃውም በተደጋጋሚ እንደሚያስቸግራትና ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይከታት እንደነበረ በማስታወስ፥ በመጨረሻም በሥጋት የተሞላው የምህረት የመሥሪያ ቤቱ ቆይታ በጥል መጠናቀቁን አውስታለች፤ “ዕድሜዋ ለጋ፣ የሥራ ላይ ልምድ የሌላት ልጅ የቅርብ ተቆጣጣሪ አድርጎ ማምጣቱን ከሥራዬ ያለፍላጎቴ ተገድጄ ለቅቂያለሁ።”

ምህረት ቢሮዋን እንደቀልድ እያለቀሰች ከወጣች በኋላ አልተመለሰችም ለሦስት ወራት ያለ ሥራ ከተቀመጠች በኋላ በአንድ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ውስጥ ትቀጠራለች። በዚህ ጊዜ ታዲያ በሕይወት አጋጣሚ የምታውቃትና በኋላ ላይም ዋነኛ ጓደኛዋ ከሆነች ሴት ጋር ይገናኛሉ። ስለ አዲሱ ድርጅት የሚያስጎበኛት በማግኘቷ ባይተዋርነት ያልተሰማት ምህረት አሁን የገባችበት ፈጣሪ ያለፈውን ጊዜ ሊክሳት እንደሆነም አልተጠራጠረችም። ባልንጀራዋ ግን አንድ ነገር አሳሰበቻት፤ ፆታዊ ትንኮሳዎች፣ የወሲብ ጥያቄዎች፣ መጎንተል እና የመሳሰሉት ነገሮች በድርጅቱ ውስጥ የተለመዱና እምብዛም የሚገርሙ አለመሆናቸውን ነው።

ለእነዚህ ነገሮች አዲስ ያልሆነችው ምህረት በአጋጣሚዎች እየተደነቀች አንድ ወር እንዳሳለፈች አንድ አሜሪካዊ ዜጋ ነጭ በምትሠራበት ጠረጴዛ ላይ አድራሻውን የሚገልፅ ወረቀት አስቀምጦ እንደትደውልለትና አዲስ ስለሚጀምረው ፕሮጀክት እንዲያወሩ ይጠይቃታል። ጉዳዩን ለባልንጀራዋ ስታማክራት የሰውየውን ምንነትና በድርጅቱ ውስጥ ሥማቸው በክፉ ከሚነሱ ሠራተኞች አንዱ መሆኑን ጠቅሳ ከአብዛኞች ሴቶች ጋር አንሶላ መጋፈፉንና በተለይም በተለማማጅነት ገብተው የተቀጠሩ ሠራተኞች የእሱን የወሲብ ጥያቄ የተቀበሉ ብቻ እንደሆኑ ታጫውታታለች። “ነገሮችን ለማስታረቅ የሚከብድ ነገር ነው የተፈጠረብኝ። በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾችና መገናኛ ብዙኀን ላይ ስለ ሴቶች መብት መከበር ሲጮሁ የሚውሉ ተማርን የሚሉ ሴቶች በዚሁ ድርጅት ውስጥ ሳይ የሴቶች መብት የሚሉት ነገር ውሸት እንደሆነ ነው የተረዳሁት” የምትለው ምህረት የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ከተባለው ነጭ አሜሪካዊ የድርጅቱ ኀላፊ ስትሸሽ ኖራለች።

በድርጅቱ ውስጥ የደረጃ ዕድገት ቶሎ ቶሎ ስለሚመጣ እና የድርጅቱ ሠራተኛ ስለሚያመለክት በየጊዜው ለቃል ፈተና መቀመጥ የተለመደ ነው። በተደጋጋሚ አመልክታ ያሰበችውን ቦታ ማግኘት ያልቻለችው ምህረት፥ በአንድ አጋጣሚ ረዘም ላለ እረፍት ወደ አገሩ መሔዱን ተከትሎ የተተካችው ሴት አሜሪካዊት በጊዜው የወጣውን የኀላፊነት ቦታ እንድትይዝ በማድረግ የአመራር ቦታ እንደሰጠቻትና በዚህም ለሦስት ዓመታት በብዙ ትግልና ተጋድሎ እንዳገለገለች ትናገራለች። “እስካሁን ከአዕምሮዬ የማይጠፋው የኀላፊነት ቦታ ላይ ከተቀመጥኩ በኋላ ሐበሻ የላይኛው ክፍል ኀላፊዎችም የወሲብ ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸው ነው” ትላለች ።

በመጨረሻም ምህረት እንዲህ ስትል ረጅሙንና አሰልችውን የሥራ ሕይወቷን ጠቀለለችው። “በብዙ ውጣ ውረድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪየን ይዤ አለቃ እቀንሳለሁ ብዬ ባስብም የወንዶች አለም ነውና ያለንበት መማር ሳይሆን የአለቃን የወሲብ ፍላጎት ማርካት ለበለጠ ሹመት ያደርሳል። እኔ የቅጥር ሕይወት የበቃኝ አምሽቼ በምሠራበት አንድ ምሽት ከእረፍት የተመለሰው ያ ነጭ አሜሪካዊ ሳላስበው ከኋላዬ አቅፎ ፀያፍ ነገሮችን ቢሮው ውስጥ እንድናደርግ እና በምላሹም አሜሪካ በሚገኘው ዋና ቢሮ እንደሚያስተላልፈኝ የነገረኝ ጊዜ ነው” ትላለች።

ባለታሪካችን ምህረት ገና በለጋ ዕድሜዋ ያጋጠሟት አሰልቺ የሥራ ላይ የወሲብ ጥያቄዎች ተቀጥሮ መሥራት የሚለውን ነገር ከአዕምሮዋ እንድታወጣውና በቅጥር ተስፋ እንድትቆርጥ አድርገው ፊቷን ወደ ግል ንግድ እንድታዞር ሆናለች። ምህረት አሁንም በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ አገሯን የመጥቀም ፍላጎት እና እንዳሰበችው አለመሆኑ ደግሞ የእግር እሳት ሆኖባታል። “ቤተሰቦቼ ነጋዴዎች ቢሆኑም በንግድ የመሰማራት ሐሳብ ኖሮኝ አያውቅም” የምትለው ምህረት አሁን ከውጭ የሴራሚክስና ግራናይት ምርቶችን በማምጣት ሥራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።

የሴቶችን በሥራ ላይ የወሲብ ትንኮሳ ምህረት ብቸኛዋ ተጠቂ ሳትሆን ማሳያ ነች። በተመሳሳይም የሀና አማረን (የአባቷ ሥም የተቀየረ) ሕይወት በአጭሩ ማስቃኘት ይቻላል። ሀና ለአራት ዓመታት በሠራችበት እና በኤች አይ ቪ ዙሪያ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በቅርበት የሚሠራ ድርጅት ውስጥ አብረዋት ከተቀጠሩ ሰዎች ሴትነታቸውን ተጠቅመው በአጭር ጊዜ የቅርብና የሩቅ አለቆቿ ሲሆኑ እሷ የሚቀርብላትን የወሲብ ጥያቄዎች ላመስተናገድ አሻፈረኝ በማለቷ ለአራት ዓመታት አንድም ዕድገት ሳታገኝ በብስጭት እንደለቀቀች ለአዲስ ማለዳ አጫውታናለች።

“ይሠራ የነበረው ሥራ ከአዕምሮ በላይ ነው” የምተለው ሀና፥ በተለይ ደግሞ የውጭ ዜጎች በወር እና በዐሥራ አምስት ቀናት ቤታቸው የሚያዘጋጁት ድግስ ላይ አንዳንድ የሐበሻ ሴቶች ከነጮች ጋር በአደባባይ ሲዳሩ ማየት የሚያሸማቅቅ መሆኑን ትገልጻለች። ያለበቂ ዝግጅትና ብቃት ከአለቆች ጋር በሚኖር ግንኙነት ሴቶች ይሾማሉ የምትለው ሀና፥ በዚህ ጉዳይ በመማረር ኑሮዋን ከቤተሰቦቿ ጋር አገረ አሜሪካ አድርጋለች።

ሰላም ሙሴ የሚዲያ እና ስርዓተ ፆታ ባለሙያ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በአማካሪነት የሚሠሩ እና በ“ሴታዊት” እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያበረከቱ ባለሙያ ናቸው። ሰላም በርካታ ሴቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ፆተዊ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸው እንደሚታወቅ ገልጸው ይሁንና ግን ተጠቂዎቹ ወደ አደባባይ ወጥተው ያለመናገራቸው ችግሩን እንዲባባስ እንዳደረገው ይጠቅሳሉ። ወደ ሕግና ወደ አደባባይ በይፋ ላለመናገራቸው ደግሞ ሴቶች መጀመሪያ ጥያቄው እና ማሽሟጠጡ በእነሱ ላይ ስለሚብስ ነው ይላሉ። “ስቀሽለት ይሆናል፣ ፊት አሳይተሽው ይሆናል፣ ምን ለብሰሽ ነበር እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በመጀመሪያ ደረጃ ተበደልን ለሚሉት ሰዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች በመሆናቸው አንደኛው የሴቶች ፍራቻ ነው።”

ሰላም በአብዛኛው እንደዚህ ዓይነት ጥቃት አድራሾች በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ብቻ የታጠሩ ሳይሆን በሀብትና በትምህርት የገፉ ሰዎች ጭምር መሆናቸው የሥራ ዋስትና ለማረጋገጥ ብዙዎቹ ተጠቂዎች ዝምታን እንደሚመርጡ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ባሰማራሁት አጣሪ ቡድን አገኘሁት ያለውን ውጤት ባካተተበት ሪፖርት ላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን የሥራ ላይ ትንኮሳ በተመለከተ እንደ መፍትሔ የትኛውም ግለሰብ በወሲባዊ ትንኮሳ የተከሰሰ ምንም ዓይነት ምህረት ሳይደረግለት ከሥራው እንዲወገድና በሕግ እንዲጠየቅ እንደሚያደርግ በግልፅ አስቀምጧል።

እነዚህን እና መሰል ችግሮችን በተመለከት አዲስ ማለዳ የስርዓተ ፆታ ባለሙያዋንና በዚህ ዙሪያ በርካታ የምርምር ፅሁፎችን ያሳተሙትን በአዲስ አበባ ሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑትን ሰብለ ሙሉጌታን አነጋግራለች። “የሕግ መላላት ዋነኛው ክፍተት ነው” የሚሉት ሰብለ ሴቶች በመሥሪያ ቤታቸው የሚያጋጥማቸውን ችግር ይዘው ወደ ሕግ በሚቀርቡበት ወቅት እንደ ተራ ነገር ስለሚቆጠርና የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ይህን ስለሚያውቁ ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ። “በመስሪያ ቤቶች ውስጥ ወንዶች አንቺ ከማን ትበልጫለሽ ዓይነት አስተሳሰብን በሴቶች ላይ ሲያስተጋቡ እና ቀዳሚዎቹ ሴቶች ከፍላጎታቸው ጋር ከተስማሙ ሌሎች ሴቶችም መስማማት አለባቸው ዓይነት አስተሳሰብ የችግሩ አቀጣጣይ ነው” ሲሉም ያክላሉ።

በሕግ በኩል ግን ውጭ ጉዳይን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት አካላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች በርካታ አቤቱታዎች በተለይም ደግሞ ፆታዊ ጥቃቶችን በሚመለከት እንደሚደርሳቸው እና ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እንደሚያልፉ ጠቁመዋል። በስተመጨረሻም “ከወዲሁ መፍትሔ የሚበጅለት ጉዳይ ነው የሚባል ሳይሆን ሥር የሰደደ ጉዳይ በመሆኑ አስቸኳይ የሕግ ማዕቀፍ እና በግልፅ የተቀመጠ ቅጣትም ሊኖረው ይገባል” ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here