የ“ፌሚኒዝም”ን ዓይነት የተሻለ ዓለም ለመፍጠር

0
931

“ፌምኒዝም” ከቃሉ እስከ ጽህሰ ሐሳቡ ብዙዎችን ያጨቃጭቃል። ቤተልሔም ነጋሽ ከቀላሉ የመዝገበ ቃላት ብያኔው በመነሳት በሴትና በወንድ እኩልነት ላይ ተመስርቶ የሴቶች መብት እንዲከበር የሚሠራ ንቅናቄ ሲሉ ይንደረደራሉ። ፌሚኒዝም ጎጂ ባሕልን ከመቃወም ባሻገር በኢትዮጵያ መሰረታዊ መብቶች መከበር ያስፈልጋል ሲሉ መከራከሪያ ሐሳብም ያቀርባሉ። ወንዶችም ሴቶችም ደስተኛ የሆኑበትና የሚፈልጉትን ዓይነት ኑሮ የሚኖሩበትን ፍትሐዊ ዓለም ለመፍጠር መነሻው ሴትና ወንድ ልጆቻችንን እስከዛሬ ከተለመደው መልኩ ለየት አድርገን ማሳደግ ነው ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ለግሰዋል።

“ለእኔ ፌሚኒስት ማለት ‘አሁን ያለው የሥርዓተ ጾታ፣ የወንዶችና የሴቶች ግንኙነት ጉዳይ ችግር አለበት፤ ይህን ችግር እንፍታውና ለሁለቱም ጾታ የሚሆን የተሻለ ዓለም እንፍጠር’ የምትል ወይም የሚል ሴት ወይም ወንድ ነው።”

ናይጀሪያዊት ልብ ወለድ ፀሐፊና ፌሚኒስት ቺማማንዳ ኢዲቼ
“እንስታዊነት (ፌሚኒዝም) ለአንዲት ሴት ሥራ ስለማግኘት አይደለም። በሁሉም ቦታ ላሉ ሴቶች የተሻለ ዓለም ስለመፍጠር እንጂ። ካለው አንድ አምባሻ ላይ ስለመጋራትም አይደለም፤ ብዙ አምባሻዎች አሉና፤ ይልቁንም አዲስ አምባሻ ስለመጋገር እንጂ።”

ግሎሪያ ስቴነም
በግሌ ርዕሰ ጉዳዩ ምቾት ከሚሠጡኝና መነጋገር መወያየት መፃፍ ከማይሰለቹኝ ጉዳዮች አንዱ ፌሚኒዝም ወይም በአማርኛ እንስታዊነት ብለን ለመተርጎም የምንሞክረው ጽንሰ ሐሳብ ምናልባት ከቀዳሚዎቹ መካከል ነው።

ነገር ግን በአካልም ይሁን በማኅበራዊ ሚዲያና በኦንላይን የሚጋጥሙኝ ጥያቄዎች ለማወቅና ለመረዳት በመፈለግና በቅንነት የሚነሱ ሳይሆኑ “ተሳስተሻል ወይም እንዴት ብትደፍሪ ነው በአደባባይ እንዲህ ነኝ የምትይው?” የሚል ድምጸት ያላቸው ናቸው። “ምሁር ትመስያለሽ እንዴት ሆኖ ነው ፌሚኒስት ነኝ የምትይው?” ዓይነት ጥያቄዎች። ብዙዎች ፌሚኒዝም ምን እንደሆነ ይታወቃል ያልሆነው ሲለጠፍበት አይደለም ብሎ ማስረዳት ድካም ነው ይላሉ።

ቢሆንም በአውቆ ጠያቂውና ምንነቱን ለመረዳት ባለመፈለግ ወይም ባለመሞከር በጭፍን ከሚቃወመው ጋር አብሮ አጋጣሚውን ቢያገኝ ሊረዳውና ምናልባትም አጋር ሊሆን የሚችል ስለሚኖር ማስረዳቱ ጥቅም አለው በሚል ከዚህ በታች ያሉትን አጫጭር ማብራሪያዎች ለመስጠት ይህን ጽሁፍ ከትቢያለሁ።

ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ ፌሚኒዝምን ከቀላልና ከሚያግባባን የመዝገበ ቃላት ትርጓሜው “በሴትና በወንድ እኩልነት ላይ ተመስርቶ የሴቶች መብት እንዲከበር ቅስቀሳ የሚያደርግ (የሚሠራ) ንቅናቄ” በሚለው ከተቃውሞው ጀርባ ያለውን ምክንያትና አስፈላጊነቱን ለመጠቆም ነው።

“ፌሚኒዝም”ን ከውጤትአንፃር መቃወም
ባለፈው በአንድ የአገራችን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የሚተላለፍ ቃለመጠይቅ ለመቅረጽ ከጋዜጠኞች ከቀረጻ ባለሙያዎች ጋር ነበርኩ። ለውይይታችን እንዲያመች ከእኔና ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ካላትና በፌሚኒዝም ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ከተወከለች ወጣት ሌላ እንደተከራካሪ ሆኖ የቀረበ ምናልባት በፌሚኒዝም ላይ አሉ የሚባሉ ተቃውሞዎችን ይዞ የመጣ አቅራቢም ነበረበት።

ገና ከጅምሩ የቀረጻ ባለሙያዎቹ ዝግጅታቸውን እስኪያጠናቅቁ በነበረን ውይይት ከወንድ ጠያቂዬ ብዙ ግን የተለመዱ የተቃውሞ ጥያቄዎች እንደሚመጡ ጠብቄ የነበረ ሲሆን ከዚያ ባሻገር ጉጉቴ ሁሌም መረዳት የምፈልገውና ፌሚኒዝምን አምርረው የሚጠሉና የሚቃወሙ “ፀረ- ፌሚኒስት” ሰዎች መነሻቸው ምንድነው የሚለው ስለነበር ያንን ለማወቅ ጓጉቼ ነበር።

በውይይቱ መካከል ጉዳዩ በመጨረሻ በእኔ “ለምንድን ነው ፌሚኒዝምን የምትጠላው?” የሚል ጥያቄና በወጣቱ “ሚስቴን፣ የማገባትን ሴት እንድትለውጡብኝ ከእኔ በተቃራኒ እንድትሔድ እንድታደርጉብኝ አልፈልግም” የሚለው የእሱ መልስ ላይ ሲደርስ መልስ ይሆነዋል የምለውን ከሰጠሁት በኋላ የታሰበኝ ምናልባት ይህ አውጥተው ባይናገሩትም በብዙዎች ዘንድ ያለ ፍርሃት እንደሆነና በአጠቃላይ “ሁሉም ሴቶች ፌሚኒስት ቢሆኑ ምን ይውጠናል” ሥጋት መኖሩን የሚመለክት እንደሆነ ነው። እንደሚባለው የተሻለ ቦታና ክብር እንዲሁም የበላይነትን ተጎናጽፎ ለቆየ ማኅበረሰብ የበላይ አይደለህም እኩል ነህ መባል ለመቀበል ቀላል አይሆንም።
ይህን የሚገልጽ አንድ ታዋቂ አባባል እንደሚለው “የበላይነትን (ተጠቃሚነትን) ለለመደ፤ እኩልነት ጭቆና ይመስላል”

“ፌሚኒዝም” ቃሉን መቃወም
ፌሚኒዝም ብለን በምንረዳው በግሌ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታም በምናተኩርበት ጽንሰ ሐሳብ ላይ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ጋር በመሠረተ ሐሳቡ ስስማማ ከላይ በምሳሌ ያነሳሁትን ወጣት ጨምሮ የብዙዎች ጥያቄ ፌሚኒዝም የሚለው ቃል ምቾት ይነሳል፤ ሌላ ፈልጉለት የሚለው አንድ የሚቀርብ ሐሳብ ነው። እንስታዊነት የሚለው ሥያሜ ጽንሰ ሃሳቡን ይገልፀዋል ወይ የሚለው ሌላ ሆኖ ገና ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ሐሳቡን በትክክል መረዳት፣ መጠየቅ፣ መከራከር፣ ማመን ማሳመን ይሻላል ወይስ በቃል መጣላት?

በበኩሌ ሐሳቡ እንዲታወቅና እንዲለመድ የተለጠበፈት አሉታዊ ትርጓሜ እንዲነሳ ከማስረዳት ውጪ ሥሙን ተዉ በሚለው አልስማማም። ሐሳቤን ያስረዳልኛል ያልኩትን የቺማማንዳ ኢዲቼ አባባል እነሆ፡-
“አንዳንድ ሰዎች ‘ለምን ፌሚኒስት ነኝ ትያለሽ ለምን በሰብኣዊ መብት የማምን ነኝ ወይም ተመሳሳይ ነገር አትይም?’ ይሉኛል። ምክንያቱም ያ ታማኝ አለመሆን ስለሆነ፤ እውነት ነው የሴቶች መብት የሰብኣዊ መብት አካል ነው። ነገር ግን የሰብኣዊ መብት የሚል ጥቅል መግለጫ ማስቀመጡ ሴትና ወንዶች መካከል ያለውን ልዩነትና ችግር መካድ ነው። ይህን ማድረግ ሴቶች ለክፍለ ዘመናት ከእሳቤው እንዳልተገለሉ ማስመሰል ነው። የሥርዓተ ፆታ ችግር ሴቶችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን መካድም ነው።”

“ፌሚኒዝም” ጎጂ ባሕልን ለመቃወም ያስፈልጋል
የፌሚኒዝም ዋነኛ ተቃውሞ ምናልባት ባሕልን ይለውጣል ወይም ፀረ ባሕል ነው የሚል ነው። ነገር ግን ባሕልን ሰዎች ሠሩት እንጂ ባሕል ሰዎችን አልሠራም። እንደማኅበረሰብ የዕድገት ደረጃ የሚለወጥ የሚሻሻል ወይም ፈጽሞ የሚቀር ነው። ለምሳሌ ቀደም ባለው የአገራችን ባሕል ታዳጊ ሴት ልጆችን ጠልፎ ማግባት ባሕል ነበር። ያለዕድሜ ጋብቻና ግርዛት ባሕል የነበረ ግን በሕግም በልማድም የተወገዘ የተከለከለ ነው፤ እንዳለመታደል ሆኖ ጨርሶ ባይጠፋም። ሌላውም የባሕል ዓይነት አንደኛውን የማኅበረሰብ ክፍል (ሴቶችን ተጭኖና ሕይወታቸው ትርጉም አልባ እንዲሆን አድርጎ) እየጎዳ ሌላውን ለመጥቀም ከቆመ ሊሻሻል ይገባል።
ለምሳሌ ባሕል ሴት ልጅ የቤት ውስጥ ሥራ ብቻዋን ትሥራ ወይም ልጆች የመደበኛ ሥራ ተቀጣሪም ሆነች አልሆነች ያለአባት እገዛ ብቻዋን ታሳድግ ያለ እንደሆነ ትክክልና ፍትሐዊ መሆኑ ሊጠየቅ ግድ ይላል።

በባሕል ሥም ብዙ ክልከላዎች በሴቶች ላይ ይደረጋሉ። ሴቶች እንደ አቅመ ቢስና ተጋላጭ ቡድን ብቻ እየታዩ ተሳትፎ እንዳይኖራቸውም እንቅፋት ይፈጥራል። ባሕል ጠንካራና ከባድ ተፅዕኖ ያለው ከመሆኑ አንፃር ሴቶችም ጭምር ይህንን በማመን ፌሚኒዝምን ሲቃወሙ፣ የሴቶች ቦታ ብሎ ባስቀመጠው ሁኔታና ቦታ ከማኅበረሰቡ ጋር በመስማማት ራሳቸውን በሚመለከት ጉዳይ ሳይቀር ሌሎች እንዲወስኑ ሲያደርጉ ይስተዋላል ።

ለእነኝህ ሴቶች ማለት የምችለው ሉዊዛ ሜይ አልኮት እንደምትለው ፤
“ሴት ስለሆንሽ ራስሽን በሳጥን ውስጥ ቆልፈሽ አታስቀምጪ፤ በዙሪያሽ እየተከናወነ ስላለው ነገር ተረጂ፣ በዓለም ሥራ ላይም የራስሽን አሻራ አኑሪ ምክንያቱም አንቺንና ያንቺ የሆኑት ላይ ተፅዕኖ ያደርጋልና” ነው።

“ፌሚኒዝም” ለኢትዮጵያ ለመሠረታዊ መብቶች መከበር ያስፈልጋል
ከላይ ከጠቀስኩላችሁና ከሌሎች ጠያቂዎች ጋር የማያግባባኝ እነሱ ነው በሚሉት አንፃር ፌሚኒዝም ቅንጦትና ፀረ ማኅበረሰባዊ እሴት፤ “አትልከፉን” ወይም “ሃይማኖት አያስፈልገኝም” አልያም “ትዳር አያስፈልግም” የሚል ብቻ ነውና ለእኛ አያስፈልገንም የሚለው ማጠቃለያ ነው።

ለኢትዮጵያ ፌሚኒዝም ያስፈልጋል የምንለው እኩል የትምህርት፣ የሥራ፣ የጤና፣ ከጥቃት የመጠበቅ በፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው። በአገራችን ሴቶች እነኝህ መብቶቻቸው አልተሟሉላቸውም፤ በተጠቃሚነት ረገድም ወደ ኋላ ቀርተዋልና።

ሴቶች ልጆች ዛሬም ትምህርት አያገኙም፣ ቢያገኙም ቤት ውስጥ ሥራ እንዲሠሩ ስለሚገደዱ ውጤታማ ለመሆን አይችሉም፤ በገጠር ደግሞ ኹለተኛ ደረጃ በሌለበት አካባቢ ወደ አቅራቢያ ሔዶ ለመማር ግድ ሲሆን ሴት ልጆች በተለያየ ምክንያት አይመረጥም።

በከተሞች ሳይቀር ሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ በማጣት (ከፍተኛ ታክስ የሚጣልበት በአገር ውስጥ የሚመረተውም ውድ በመሆኑ) ምክንያት ከትምህርት ቤት እንደሚቀሩ ጥናት በማረጋገጡ፣
በእነኝህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ለችግሮች መፍትሔ እንዲገኝ ለመጠየቅ፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የሴቶችን ሁኔታና ድምጽ ያገናዘቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ፌሚኒዝም ያስፈልገናል።

ከሁሉም በላይ ሴቶች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ከጥቃት እንዲጠበቁ ለማድረግ፣ ጥቃት ተፈጽሞ ሲገኝም ፍትሕን ለማስገኘት።
ለምሳሌ አንድ በየኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ የተለጠፈና በብዙዎች የተጋራ የሰሞኑን ዜና ልንገራችሁና ላብቃ።

“ሚስቱ ላይ አሲድ ያስደፋው ወንጀለኛ በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ!” ይላል ዜናው
ጥንዶቹ ላለፉት 7 ዓመታት በትዳር አብረውኖረዋል። የ5 ዓመት ሴት ልጅ ወልደው በማሳደግ ላይ ነበሩ። ምንም እንኳን ለበርካታ ዓመታት አብረው የኖሩ ቢሆንም በትዳራቸው ውስጥ መጠነኛ ግጭት በተደጋጋሚ ይስተዋል ነበር። በአብዛኛው የፀባቸው መንስኤ የሰላም ሥራ መሥራት መፈለግ ሲሆን ይህ ደግሞ ብዙም በባለቤቷ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። ከዛም ባል ለዚህ “ችግር” መፍትሔ አድርጎ የወሰደው ካንድ ግለሰብ ጋር ተመሳጥሮ ሁኔታውን አመቻችቶ ልጋብዝሽ ብሎ በምሽት ከቤት አስወጥቶ ፊቷ ላይ አሲድ እንዲደፋ ማድረግ ነበር። ከዛም ምንም እንዳልተፈጠረ አስታማሚ መስሎ ባል ሆኖ መቀጠል። ተጎጂዋ ጉዳይዋ እንዲታይላት ግፊትና ክትትል እንዲያደርግ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋር ካመለከተች በኋላ ፖሊስ ምርመራውን አካሒዶ ሁሉም ነገር የባል ተግባር መሆኑን ይደርስበታል።

የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ካጣራ በኋላ በባለቤቷ እና አሲዱን በደፋው ግለሰብ መካከል ያለውን ግንኙት የተጎጂዋ ሰላም ባለቤት አየለ ለፖሊስ ከማመኑም በላይ አሲዱን ከየት እንደገዛ፣ ከማንሱፐርማርኬት እንደገዛ፣ መቼ አሲዱን ለደፋዉ ሰው እንደሰጠ፣ አሲዱን በስንት ብር እንደገዛ ያንንም ደግም በቦታውም ጭምር በመሔድ እንዳሳየ አምኗል፣ ምስክሮችም መስክረዋል። ሰላም የአሲዱ ጥቃት ከባድ አካላዊ ጉዳት አድርሶባታል። 32% የሰዉነቷ ክፍል በአሲዱ የተቃጠለ ሲሆን፣ የቀኝ ዓይኗም ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል። የደረሰባት የአሲድ ቃጠሎ አንዳንድ የሰውነቷ ክፍል ላይ እጅግ ከባድ ጠባሳም ከመጣሉም በላይ እንዲህ በተቀነባበረ መንገድ፣ ሊታመንላት በሚገባው ባለቤቷ የዚህ አሰቃቂ ወንጀል ሰለባ መሆኗ እጅግ ጎድቷታል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርም፣ ሰላም የሚያስፈልጋትን የህግ ማማከር አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር፣ ትልቅ የሞራል ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል። እስከመጨረሻውም ጉዳዩን በአካል ተገኝቶ በመከታተል፣ እስከፍርድ ድረስ በነበረው ሒደት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ባለቤቷ ነው አሲዱንያስደፋው፣ ለዚህም ጥፍተኛ ነው ሲል ወስኗል። ወንጀለኛውም ፍርድ ቤት ላይ አምኖ ነገር ግን ቅጣት እንዲቀነስለት ፍርድ ቤቱን የቅጣት ማቅለያ በማቅረብ ጠይቋል። በዚህም መሠረት የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 10/2011 ከጠዋቱ 4 ሰዓት በዋለዉችሎት በ16 ዓመትከ 6 ወርፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

በማጠቃለያዬ ደግሞ ማለት የምፈልገው ወንዶችም ሴቶችም ደስተኛ የሆኑበትና የሚፈልጉትን ዓይነት ኑሮ የሚኖሩበትን ፍትሐዊ ዓለም ለመፍጠር መነሻው አንድ ነው፣ ሴትና ወንዶች ልጆቻችንን እስከዛሬ ከተለመደው መልኩ ለየት አድርገን ማሳደግ።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here