እንቦጭን ጥቅም ላይ ለማዋል ሦስት ዓመት የሚፈጅ ጥናት ሊካሔድ ነው

0
730

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከኦሲፒ አፍሪካ ጋር ባደረገው ስምምነት እንቦጭን ወደ ማዳበሪያነት ለመቀየር የሚያስችል ጥናት ማካሔድ በሐምሌ 2011 የሚጀምር ሲሆን ጥናቱም በሦስት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል።

በባሕር ዳር ጣና ሐይቅ ላይ ምርምር እንደሚደረግ የኦሲፒ አፍሪካ ተወካይ ሰላምይሁን ኪዳኑ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ዐቀፍና አገር በቀል ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጥናቱን ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ እንደተደረሰና ጥናቱ ለሦስት ዓመታት እንደሚፈጅ ተናግረው ወደ ተግባር ለመግባት የሠው ኀይልና የገንዘብ ድጋፎችን ለማግኘት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ በ2003 በመገጭ ወንዝ ላይ በሦስት ሔክታር ላይ ተከስቶ የተገኘ ቢሆንም አረሙን በወቅቱ መቆጣጠር ባለመቻሉ በየጊዜው በተደረጉ ጥናቶች በኅዳር 2004 አረሙ 5 ቀበሌዎችን በማዳረስ 4 ሺሕ ሔክታር መድረሱ፣ በ2005 ዐሥራ አምስት ቀበሌዎችን በማዳረስ አረሙ 20 ሺሕ ሔክታር የሸፈነ ሲሆን፣ በሦስተኛ ዙር ወደ 50 ሺሕ ሔክታር በመስፋፋት 15 ቀበሌዎችን ማዳረሱን ማወቅ ተችሏል።

በጣና ሐይቅ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቆቃ ግዴብና በዝዋይ ሐይቅ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የእንቦጭ አረም የስርጭት መጠን ባለማወቅ፣ በየጊዜው ለመቆጣጠርና ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚመለከታቸው ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በመሆን ጥናትና ምርምር አለመደረጉን የኦዲት ሪፖርት አሳይቷል።

እንቦጭ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጣና ሐይቅ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቆቃ ግዴብና በዝዋይ ሐይቅ እና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የእንቦጭ አረም ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ናቸው።

በአሁን ሰዓት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂካል ዘዴ የእንቦጭ አረምን የማጥፊያ ዘዴ ለመተግበር በሚደረገው ጥናትና ምርምር 150 የእንቦጭ አረምን የሚመገቡ ጢንዚዛዎችን ከወንጂ ስኳር ፊብሪካ በማስመጣት በላብራቶሪ እያባዛ ይገኛል።

በ2010 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኦሲፒ በጋራ በመሆን ሥራውን ለመጀመር ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም በተባለው ጊዜ ወደ ሥራ ሳይገባ መቆየቱ ታውቋል። ኦሲፒ አፍሪካ መቀመጫውን ሞሮኮ እና ሴኔጋል ያደረገ ሲሆን በዋናነት ከማዳበሪያ ምርታማነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎችን ይሠራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here