እሌኒ ገብረመድኅን (ዶ/ር) ተወዳድሮ ያላሸነፈ ድርጅት በመምረጥ ቅሬታ ቀረበባቸው

0
889

ከሰኔ 2 እስከ 3/2011 በሚሊኒየም አዳራሽ የተደረገው የፈጠራ ሥራ ሐሳብ አመንጪዎች ውድድር ፍትሐዊነት በውድድሩ ላይ ተሳታፊ በነበሩ ወጣቶች፥ ውድድሩን ባዘጋጁት አካላት እና በዳኞች ቅሬታ ቀረበበት። ለቅሬታው መሰረት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ በግማሽ ፍጻሜ ዳኝነት ላይ የተሳተፉት ዳኞች አሸናፊ የሆነውን ድርጅት ጨምሮ የሌሎች ድርጅቶችን ውጤት ሳያስገቡ የፍፃሜው ውድድር እንዲካሔድ መደረጉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በወቅቱ ጊዜው በመምሸቱ ምክንያት ውጤታቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው የሔዱት ዳኞቹ፥ እንደወትሮው የፍፃሜ ውድድሩ በሚካሔድበት ጠዋት ውጤት የሚሰበስቡት እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) መጥተው ይወስዳሉ ብለው ቢጠብቁም የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ተመርጠው መመልከታቸው እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ውድድሩን ያዘጋጁት 12 የፈጠራ ሥራ ሐሳብ አመንጪዎች ማበልፀጊያ ተቋማት ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ቢሆንም በእሌኒ የሚመራው ‘ብሉ ሙን’፥ ሌሎቹን ወደጎን በመተው ዝግጅቱ በ’ብሉ ሙን’ ብቻ የተዘጋጀ እንዲመስል መደረጉም አሳዝኖናል ብለዋል። ምንም እንኳን ሲመጡ የነበሩ ድጋፎች በአጠቃላይ በአዘጋጆቹ ስብስብ ምክንያት ቢሆንም በተለይ ለሽልማት ስለዋለው ገንዘብ እና ስለስፖንሰሮች እንዳያውቁ መደረጉንም ተናግዋል።

አንድ የማበልፀጊያ ማዕከል ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የመጨረሻ ዙር ዳኞች በእሌኒ ብቻ የተመረጡ ከመሆናቸውም ባሻገር ያሸነፈው ድርጅት ላይ ራሳቸው ኢንቨስትመንት እና የሼር ድርሻ እያላቸው ውጤት ለብቻቸው ሲሰበስቡ መቆየታቸው አስገርሞናል ብለዋል። አክለውም ለአዳዲስ ኩባንያዎች ሥነ ምኅዳር ያላቸውን ገጽታ ተጠቅመው ለውጥ ያመጡ ይሆናል በሚል እስካሁን አብዛኛው የሐሳብ አመንጪም ሆነ የማበልፀጊያ ማዕከል ችግሮችን ታግሰው መቆታቸውን ተናግረዋል። ከዳኞቹ መካከልም ኢትዮጵያዊ የሌለ ሲሆን የአገሪቱን ተጨባጭ ችግር የማያውቅ እና ገበያው ምን እንደሚፈልግ ያልተረዳ ዳኛ ይህንን ውድድር መዳኘቱ በአዘጋጆቹ ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር ብለዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹትም ‘ስታርታፕ ኢትዮጵያ’ የተባለው ማኅበር ለመመሥረት እና ከመንግሥት ለወጣቶች የሚለቀቀውን ኹለት ቢሊዮን ብር የሚያስተዳድረውን ‘ስታርታፕ ፈንድ’ ለማቋቋም እሌኒ ጥያቄ ቢያቀርቡም አብዛኛው ማበልፀጊያ እምቢታውን መግለጹን ተናግረዋል። በወጣት ሥም የሚመጣን ፈንድ በጥቂት ሰዎች ይሁንታ ማስተዳደር አግባብ ነው ብለው እንደማያምኑ እና ማኅበሩም ሁሉም ባለድርሻ እና የሐሳብ አመንጪዎቸ የተሳተፉበት መሆን አለበት ሲሉም አክለዋል።

ቀድመው ምርጥ ዐሥር ከገቡት መካከል አንድ ተወዳዳሪ እንደገለጸው ገና በውድድሩ ጅማሪ የሚያሸንፈው ይታወቃል የሚል ሐሳቦች በመብዛታቸው፥ አንድ የሚውቁት ትልቅ የሥራ ሐሳብ አመንጪ ውድድሩን ጥሎ መውጣቱን እንደነገራቸው እና እነሱም እንዲወጡ እንደጠየቃቸው ነገር ግን ነገሮች በዚህ ደረጃ ይሆናሉ ብለው ባለማሰባቸው በውድድሩ መቆየት መምረጣቸውን ተናግረዋል። “መድረኩም ላይ ይህን ቅሬታ ለመናገር ዳድቶኝ ነበር” ብለዋል።

ለአዲስ ማለዳ የደረሰው እና ገቢ ያልተደረገው የአንድ ዳኛ ሪፖርት እንደሚያሳየው፥ አሸናፊ ድርጅቱ በቀን 300 ኪሎ ቡና የሚያደርቀው ማሽን በውጪ አገር ያለው ተመሳሳይ መሣሪያ በተሻለ ዋጋ የሚገኝ መሆኑን እና ላኪዎችም በቀላሉ ማስመጣት የሚችሉት በመሆኑ ፈጠራውን ዝቅተኛ ውጤት እንዲያገኝ አድርጎታል። በተጨማሪም ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው እና በአንድ መኪና ብቻ 400 ቶን ቡና የሚጭኑ ላኪዎችን ዓላማ ማድረጉ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ያነሰ ውጤት እንዲያስመዘግብ ማስቻሉን ዳኛው በሪፖርቱ ላይ አመልክተዋል።

አያይዘውም አምስቱም የመጨረሻ ዙር ዳኞች ከኢትዮጵያ ያለመመረጣቸው ደግሞ የአገሪቱን ችግር እና የገበያውን ፍላጎት የማያውቁ እና የባለቤትን ዕድሜውን ጨምሮ ሌሎች እውነታዎችን እንዳያገናዝቡ አድርጓል ሲሉ ይሞግታሉ።

በፈጠራ ሥራ ሐሳብ አመንጪዎች ላይ ላለፉት 10 ዓመታት የሠሩ እና ታዳሚ የነበሩ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት ‘የኔ ፔይ’ የተባለው ቡድን እና ‘ላንግቦት’ የተባለው ድርጅት አሸናፊ ይሆናሉ ተብሎ ተጠበቆ እንደነበር ተናገረው፥ በጭራሽ ግን ‘ግሪን ቢን’ ያሸንፋል ብለው አለመጠበቃቸውን ተናግዋል። አክለውም በዓለም ላይ ሚሊዮኖች የሚከታተሉት ‘ቴክ ክረንች’ የተባለ የቴክኖሎጂ ሚዲያ ውድድሩን ለመዘገብ ቢመጣም ውድድሩ ላይ የነበሩትን ክፍተቶች በመመልከቱ ለመዘገብ እንደማይፈልግ ገልጾ ስለ ኢንተርኔት መዘጋት ዘግቧል። በዜናው ላይም ስለ ‘ላነገቦት’ እና ‘የኔ ፔይ’ ብቻ በመጥቀስ በጨረፍታ አስነብቧል።

‘ብሉ ሙን’ ሲቋቋም ጀምሮ በገንዘብ ሲረዳ የነበረው ‘ሮያል ዳኒሽ’ ኤንባሲ ገንዘቡ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ሪፖርቶች ስላልቀረቡለት ድጋፉን አቋርጧል የሚለውን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩት ወቀሳዎች ላይ መልስ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ እና መልዕክት ወደ እሌኒ በተደጋጋሚ ብናደርግም ልናገኛቸው አልቻልንም።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here