በአዳማ እና ሞጆ መሃል ኹለት ኮንቴነር ቡና ተዘረፈ

0
467
  • ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ቢይዝም የተዘረፈው ቡና እስካሁን የት እንደገባ አይታወቅም

ንብረትነቱ ኩሩ ኢትዮጵያ ኮፊ ዴቨሎፕመንት ኃ/የተ/የግ/ማኅበር የሆነ 39 ሺሕ 900 ኪሎ ግራም የታጠበ የሲዳማ ደረጃ ኹለት የሆነ ቡና ግንቦት 19/2011 በኹለት ኮንቴይነር ተጭኖ ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ላይ ሳለ በሞጆና አዳማ መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ በዘራፊዎች መወሰዱ ታውቋል።

ከቡና ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ወደ ጅቡቲ ወደብ ተሸኝቶ በመጓዝ ላይ እያለ ዘራፊዎቹ ሹፌሩንና ረዳቱን በማገት ቡናውን ከነተሽከርካሪው መዝረፋቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ሻፊ ዑመር፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስና የአካባቢው ኅብረተሰብ ባደረገው ርብርብ ቡናውን ጭኖ የነበረው ተሽከርካሪ ግንቦት 20/2011 ከ5 ሺሕ 514 ኪሎ ግራም ቡና ጋር መያዙን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ላኪ ድርጅቱ 34 ሺ 386 ኪሎ ግራም ቡና እስካሁን አለመያዙን በመግለጽና ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ምርመራ ይደረግልኝ ሲል ለኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባሳወቀው መሰረት፣ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱም ግንቦት 29/2011 በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል አስቸኳይ ምርመራ ተደርጎ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲበጅለት በሚል ደብዳቤ መጻፉን ለማወቅ ተችሏል።

ሻፊ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እንዲህ ዓይነቱ ዝርፊያ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ችግር የሚያባብስ፣ የዘርፉን የግብይት ሒደት ሥጋት ውስጥ የሚጥል፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በሚገዟት አገራት ዘንድ ያላትን ታማኝነትና ተቀባይነት የሚያሳጣና አገሪቱን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚዳርግ ተግባር ነው።

በቡና ኤክስፖርት ተሰማርተው ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ላይ የሚገኙ ስድስት ድርጅቶች ቡናው ወደ ተላከበት ሕጋዊ መዳረሻ ከመድረሱ በፊት ቀላል የማይባል የመጠን ጉድለት እያጋጠመ መሆኑን በመጥቀስ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ምርመራ እንዲካሔድበት በተደጋጋሚ ሲያሳውቁ እንደነበር ከጻፉት ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

ስለ ጉዳዩ አሳሳቢነት የሚናገሩት ሻፊ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአካል በመገናኘት መምከራቸውን አስታውቀው፣ አሁንም ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀለት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩ በትኩረት ምርመራ እንዲደረግበት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሰኔ 3/2011 አስታውቋል። አዲስ ማለዳ የምሥራቅ ሸዋ ፖሊስ ቀሪ ወንጀለኞችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን በማወቋ ከፖሊስ ክፍሉ ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here