“አንበሳው መጻፍ እስኪማር፤ ሁሉም ታሪክ አዳኙን ያወድሳል” የአፍሪካውያን አባባል

0
570

ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ ቋንቋ ብዙ ጻሕፍት ማፍራት ባለመቻሏ ሌሎች ለእኛ የሚኖራቸው ግምት የተሳሳተ እንደሆነ ቤተልሔም ነጋሽ በሥራ አጋጣሚ በተዘዋወሩባቸው የአፍሪካ አገራት መታዘባቸውን መነሻ በማድረግ የራሳችንን ታሪክ መጻፍ ካልቻልን ሌሎች በፈለጉት መንገድ ታሪካችንን እንደሚጽፉትም ማስረጃ በማጣቀስ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። በርግጥ ኹለት ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ መኖራቸውንና ከአንድ እጅ ጣት ቁጥር ያልበለጡ ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ያተረፉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጻሕፍት መኖራቸውን ግን አስታውሰዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪዬን በውጪ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ እንደመሥራቴ በወቅቱ ከተሰጡን ኮርሶች አንዱ የአፍሪካ ሥነ ጽሁፍ (African Literature) ነበር። መምህራችን በወቅቱ ከአንድ ኹለት ሰዎች በስተቀር በመቶዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ጻሕፍት ባሉበት ዝርዝር ኢትዮጵያውያን የሉበትም ሲሉ በቁጭት ይነግሩን እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ሳስብ የአፍሪካ ሥነ ጽሁፍና ታዋቂ ጻሕፍትን ዝርዝር ለማየት መረጃዎችን ሳስስ ያየሁትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በመቶዎች ከሚቆጠሩ የአፍሪካ ደራሲያን ዝርዝር ማግኘት የቻልኩት ዳኛቸው ወርቁ (The thirteenth Sun) ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም (Warrior King፡ The Afersata እና Shinega’s Village) ብቻ ነው። ዋነኛውና አንዱ ተግዳሮት የቋንቋ እጥረት ነው።

ምናልባት በሌሎች ጽሁፎችም እንደምለውና እንደማምንበት እኛ ኢትዮጵያውያን ስለራሳችን ያለን ግምት የተዛባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስለእኛ ያላቸው ግምት የተሳሳተ ሊሆን ስለመቻሉ ምንም ጥርጣሬ የሌለን ሰዎችም ጭምር ሳንሆን አንቀርም። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥቼ በጋዜጠኝነት ለመሠማራት በቻልኩበት ወቅት በደቡባዊቷ አፍሪካ አገር ዛምቢያ ስሔድ ዛምቢውያንና ሌሎች በዚያ የሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች ስለኢትዮጵያውያን ያላቸው መረጃ የተዛባ መሆኑ በመጀመሪያ ትንሽ ሲያስደነግጠኝ በኋላ ላይ በአካባቢዬ ካሉ የሥራ ባልደረቦቼና አብረውኝ ከሚኖሩት ጋር ያለኝን ግንኙነት፣ በኋላ ባሕሪዬንና ማንነቴን አውቀው እስኪያስተካክሉ፣ የተዛባ እንዲሆን አድርጎ ነበር። በአጭሩ ለመግለጽ እናንተ ጥቁር አይደለንም፤ ከእስራኤል ወገን ነን፣ አይሁድ ነን ትላላችሁ ኩራታችሁ መከራ ነው። ሌላውን አፍሪካ ትጠላላችሁ ወይም ሌላው ጽንፍ ሴቶቻችሁ በጣም ቆንጆ ናቸው ከተባለ በኋላ ራሳቸውን የወሲብ ሸቀጥ አድርገው ያቀርባሉ የሚል ነው።

ሌላው ምሳሌዬ በግሌ በጣም ታሪካቸውን ከምወዳቸው ኢትዮጵያውያን ነገሥታት አንዱ የሆኑት የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በሚመለከት በውጪ አገር ቤተ መጻሕፍት ያገኘሁት አስደንጋጭ መጽሐፍ ነገር ነው። በእንግሊዝ የማስተርስ ዲግሪዬን በተማርኩበት ሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ባንዱ ቀን ቤተ መጻሕፍት መጽሐፍ ፍለጋ ግዙፎቹን መደርደሪዎች ሳካልል ያገኘሁት መፅሐፍ፣ ዛሬ እንዲህ ጽፌው ሊወጣልኝ ለቅርብ ጓደኞቼ እንኳን ስነግረው የሚገርመኝ ታሪክ ነው። ርዕሱ The Mad king የተሰኘ ሲሆን ስለኛው ቴዎድሮስ የተጻፈ ነው። በኋላ ስሰማ እንግሊዛውያኑ ይህን ቅጽል ለንጉሳችን እንደሚጠቀሙበት ይታወቃል። ከዚያ ይውጣልሽ ብሎ ኖቲንግሃም በምትሰኘው የማዕከላዊው እንግሊዝ ግዛት ባለ ለዝነኛው ከሀብታም ነጥቆ ለደሃ ሰጪ ያገሩ ጀግና ሮቢን ሁድ መታሰቢያ የታነፀ ሙዚየም ስጎበኝ አንዱ ጠርዝ ለኢቢሲኒያ ጦርነት ተብሎ በተወሰነ ጥግ፣ የእኛው አገር የጦርነቱ ሥፍራ ማሳያና በጦርነቱ ለተሳተፉት የተሰጠ የአቢሲኒያ ሜዳል ኮፒ ተቀምጧል። የተጻፈው ማብራሪያ ምን ቢል ጥሩ ነው እንግሊዝ ዝቅተኛውን ወጪ ያወጣችበት ምንም ወታደር ያልሞተበት የአቢሲኒያ ጦርነት ነው። ታረክ በዛ ወገን እንዴት እንደተጻፈ አያችሁ? ታሪካችንን ሌላው ዓለም በሚረዳው ቋንቋ የመጻፍን አስፈላጊነትስ?

ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ውጪ በሌላ ቋንቋ መጻፍ
“የአንድን ሰው ታሪክ ካልወደድከው፤ የራስህን ታሪክ ጻፍ” ታዋቂው ናይጄሪያዊ ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ
መጻፍ ሲታይ ቀላል የሚመስል (‘ከበሮ በሰው እጅ ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር’ እንደሚለው ብሒል) ሲሞክሩት ግን የሚከብድ ነው። በማንኛውም ቋንቋ ሐሳብን በሚገባ በልኩ አሰናድቶ መግለጽ ተሰጥዖ ይጠይቃል። የራሴን ቀላል ምሳሌ ብሰጣችሁ አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ ሆኖ ሳለ በተለይ ውብና ገላጭ አድርጎ ለመጻፍ እጥረት እንዳለብኝ የሚሰማኝ ሰው ነኝ። አብዛኛው ሰው እኔ የምጽፈውን ያህል አለመቻሉ በራስ መተማመን የሚሰጠኝ ቢሆንም በተለይ ወጣቶች በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ (በስፋት በትምህርት ቤትም ጭምር አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የምንማረው እሱ በመሆኑ) በትክክል ሐሳባቸውን በጽሁፍ ማስፈር አለመቻላቸው ትንሽ ያሳስበኛል።

አብዛኞቹ ጻሕፍት በኹለተኛ ቋንቋ ቀርቶ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንኳን መጻፍ ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ። ሆኖም ግን በርካታ ጻሕፍት በኹለተኛ ቋንቋ መጻፍ ብቻ ሳይሆን ውብ አድርጎ መጻፍም ችለዋል። እነኝህ ሰዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ሥያሜም ወጥቶላቸዋል። በእንግሊዝኛው exophonic ሲባሉ ቃሉ የመጣው በኹለት ቃላት ጥምር exo – “outside”; phonic – “voice ” የሚል ትርጓሜ አለው። እውቅናው ቀላል አለመሆኑ የሚገባችሁ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም የዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ Exophony የሚባል ኮርስ እንደሚሰጥ ስትሰሙ ነው። የኮርሱ ይዘት ደግሞ ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ባሻገር መጻፍ የሚል ነው።

መጻፍ ራስን ከመግለጽ፣ ከማስተዋወቅ፣ የራስን ድምጽና ታሪክ አተያይ ለማስፈር፣ ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ የሚረዳ ወሳኝ መሣሪያ ነው። ቋንቋና በጽሁፍ ሐሳብን ማስተላለፍ ከቀላሉ መረጃና ታሪክን ከማስተላለፍ በተጨማሪ ራስን ፈልጎ የማግኘት ሒደት ዋና አካልም ነው። ቺኑዋ አቼቤ እንደሚለው
“ማንም ሰው ማንነቴን ሊያስተምረኝ አይችልም፤ የእኔን ማንነት የሠሩትን ነገሮች ልትዘረዝሩ ትችሉ ይሆናል። ማን መሆኔ ምን እንደምፈልግ ግን – ራሴ ማግኘት፣ ማወቅ ያለብኝ ነገር ነው”

ራሳችን ታሪካችንን መጻፍ ካልቻልን ሌሎች በፈለጉት መንገድ ታሪካችንን ይጽፉልናል። ከላይ የጠቀስኩት በታሪካችን ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ነው።

የጦርነት ታሪክ የሚነገረው በአሸናፊው ወገን ነው። አብዛኞቹ ነገሥታት ታላላቅ ሆነው የተሳሉት እነሱን ተቃርኖ ወይም ወቅሶ ለመጻፍ የሚደፍር ባለመኖሩ ነው። ወራሪዎች ነባሩን ባሕል አጥፍተው ለእነሱ በሚያመቻቸው አገዛዝ ይተኩታል። እምነታቸውና ልማዳቸውን ያቃልሉባቸዋል፣ ቀጥሎም አገሬው ለራሱ ያለውን ክብር እንዲያጣ የበታችነት ስሜት እንዲሰማው ይሆናል። ይህ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ታሪክ የሆነ ነው። በዚህም ምክንያት ነው ታሪክ የአንድ ወገን ታሪክ ብቻ ነው ለማለት የምንገደደው። በአገራችን የሚያስማማንና ሁላችንም የምንቀበለው ታሪክ ያጣነውም ለዚህ ይመስለኛል። በእንግሊዝኛና በሌሎች ቋንቋዎች ስለእኛ የተጻፉ መጻሕፍት ደግሞ ሁሉም በሚባል ደረጃ በውጪ ዜጎች የተፃፉ ሲሆኑ በአሳዛኝ መልኩ በተለይ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ስለነበረው ታሪካችን በጣልያንኛ፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው ተጠቃሽ የሆኑት። ነገር ግን የራሳችንን ትርክት፣ ማንነት፣ አስተሳሰብ፣ የሕይወት ልምድ ለዓለም ለማጋራት ስለባሕልና እሴቶቻችን ለዓለም ለመንገር በውጪ ቋንቋ መጻፍ (ያም ቢቀር ጥሩ የምንላቸውን እንኳን ወደ ሌላ ቋንቋ ማስተርጎም መጀመር የግድ ይላል፣ ከአፍሪካ ሥነ ጽሁፍ ተርታ መግባትም እንዲሁ። ካልሆነ ባሕላችን ተበረዘ ምዕራባውያን ወረሱን ማለት ዋጋ የለውም።

በውጪ ቋንቋ መጻፍ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ለማስረዳት ይህን ካልኩ፣ እንደማበረታቻ ይሆን ዘንድ በውጪ ቋንቋ ጽፈው ታዋቂ የሆኑ ጻሕፍትን ላንሳ።

በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ውጪ በመጻፍ ዕውቅናን ያተረፉ መጻሕፍት
በኹለተኛ ቋንቋቸው ጽፈው ታዋቂነትን ካተረፉት መካከል የቭላድሚር ናቦኮቭን ታሪክ ብናነሳ ጸሀፊው በሩሲያ ታዋቂ ከሚባሉት ተርታ የሚመደብ ሲሆን የኖረውም እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1899 እስከ 1977 ነው። ከኮሚኒስት አብዮት በፊት ፊውዳል ከሚባል ቤተሰብ ውስጥ ልጅነቱን ያሳለፈው ኖቦኮቭ ከሩስኪ በተጨማሪ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ራሱን ሲገልጽ “እኔ ሦስት ቋንቋዎችን የምናገር እንደማንኛውም ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ባለው ቤተሰብ ውስጥ እንዳደገ ልጅ ነኝ” ይላል ነበር። ናቦኮቭ ዘጠኝ መጻሕፍትን በእንግሊዝኛ የጻፈ ሲሆን ‘አይከን’ (ምልክት) እንዲሆን ያደረገው ግን አራተኛውና ሎሊታ የተሰኘው ከመቶሺሕ ኮፒ በላይ የተሸጠለት በ1958 (እ.ኤ.አ) የታተመው፣ ከታተመ አፍታ ሳይቆይ በአሜሪካ ሥነ ጽሁፍ ማስተማሪያ የሆነው መጽሐፉ ነው።

ሌላው ከቋንቋው ውጪ በመጻፍ ዝነኛ የሆነውና ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ፀሀፊ ከ1883 እስከ 1931 (እ.ኤ.አ) የኖረው ካህሊል ጂብራን ነው። ጂብራን ሊባኖስ ተወልዶ እስከ 12 ዓመት ዕድሜው እዚያው ሲቆይ ምንም ዓይነት መደበኛ ትምህርት አልተማረም ነበር። ቤተሰቡ ከቤይሩት ተሰዶ አሜሪካ ከገባ በኋላ በደቡባዊ ቦስተን ከሌሎች ሶርያውያን ስደተኛ ልጆች ጋር ይኖር ነበር። አረብኛ ተናጋሪ የነበረውና በኋላ አሜሪካዊ የሆነው ካህሊል እንግሊዝኛ የተማረውም በዚህ ወቅት ነበር። በኋላ ስድስት መጻሕፍትን በእንግሊዝኛ ጽፏል። ከአሜሪካዊት ጓደኛውና ለጽሁፎቹ አርትዖት ሥራ ትሠራ ከነበረው ሜሪ ሃስኬል ጋር በመተባበር መጻሕፍቱን ተወዳጅ ሲያደርግ ሜሪ አረብኛ ተምራ የካህሊልን አስተሳሰብ ለመረዳት እስከመሞከር የደረሰ ድጋፍ አድርጋለት ነበር።

የጂብራን ታዋቂ ዝርውና ግጥም ስብስብ በ1923 (እ.ኤ.አ) የታተመው The Prophet በእንግሊዝኛ የተፃፈ ሲሆን በአሜሪካ ብቻ አራት ሚሊዮን ኮፒ ተሸጧል፤ በ40 ቋንቋዎችን ተተርጉሟል።

በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ውጪ ጽፈው ታዋቂነትን ያተረፉ ብዙ ጸሀፍትን ማንሳት የሚቻል ሲሆን ካሊድ ሆሲኒ የተሰኘው አፍጋኒስታናዊ የ The Kite Runner, A Thousand Splendid Suns እና The Mountains Echoed የሚሉት መጻሕፍት ሲኖሩት ስለትውልድ አገሩ አፍጋኒስታን ለዓለም ያስተዋወባቸው ናቸው። በፈረንሳይና የጻፈው አየርላንዳዊው ሳሙኤል ቤኬት፣ 2000 (እ.ኤ.አ) Interpreter of Maladies በተሰኘው ድርሰቷ በልብ ወለድ የፑልቲዘር ሽልማት አሸናፊ የሆነችው ቤንጋላዊቷ Jhumpa Lahiri ተጠቃሽ ናት።

ያልተነገረላቸው ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
በአፍሪካ ሥነ ጽሁፍ ከገቡልን ሰዎች ሦስት የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን በዓለም ዐቀፍ አሳታሚዎች በኩል በማሳተም ምናልባትም ብቸኛው ኢትዮጵያ የሚኖሩ ፀሀፊ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም ናቸው። ሣህለሥላሴን የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ በነበርኩበት ዘመን ቂርቆስ አካባቢ በሚገኘው፣ በትላልቅ የመጻሕፍት መደርደሪያ በተሞላው መኖሪያ ቤታቸው ተገኝቼ ቃለ መጠይቅ የማድረግ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ከጻፏቸው መጻሕፍት ብዛት አንጻር (በግሌ ‘እምዩ’ የተሰኘው የትርጉም ሥራቸው በልጅነቴ ካነበብኳቸውና ከማልረሳቸው መጻሕፍት መካከል ይጠቀሳል) ታዋቂ አለመሆናቸው በወቅቱ ገርሞኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሣህለሥላሴ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም ጉራጊኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን የመጀመሪያ መጽሐፋቸው በቸሃ ጉራግኛ የጻፉትና በውልፍ ሌስላው አማካኝነት Shinega’s Village በሚል ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የታተመው የወቅቱን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሕይወት የሚያስቃኝ ሲሆን በእንግሊዝኛ የጻፏቸው ሦስት መጻሕፍት ሲከተሉ የትርጉም ሥራዎችንም ሠርተዋል።

Warrior King በ1974 (እ.ኤ.አ) የታተመ ሲሆን አሳታሚው ሄይንማን ቡክስ ነው በአፍሪካ የመጸሕፍት ስብስብ (ቁጥር 163) ውስጥ ገብቷል፤ የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በልብ ወለድ መልክ የቀረበበት ነው። ኹለተኛው The Afersata (የመጀመሪያ ርዕሱ Firebrands በመባል ይታወቃል) እ.ኤ.አ በሎንግማን መጻሕፍት በ1979 የታተመ ሲሆን በ1966ቱ አብዩት ወቅት የተፈፀመውን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያስረዳ ነው።

ይህን ሁሉ ስል ግን በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያውን እንደ ዲናው መንግሥቱ፣ ነጋ መዝለቂያ፣ መዓዛ መንግሥቴ ያሉ ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ያተረፉ ጸሀፍትን በመዘንጋት ሳይሆን በአሕጉራችን እንደሚኖሩ ሌሎች አገራት ጸሐፍት በሚገባ አልተወከልንም፣ በዚህም ምክንያት በሌሎች ዘንድ ስለእኛ ያለው ምስል ትክክለና ስላልሆነ ልንናገር፣ ልንጽፍ አስተዋጽዖ ልናደርግ ይገባል በሚል ሐሳብ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here