ራሷን መቻሏ…

0
601

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በትዳር ውስጥ በርካታ ሴቶች የቤት እመቤት ናቸው። የቤት ‘እመቤትነት’ ቃሉ የተሞካሸና የተቆላመጠ ሆኖ ነው እንጂ እንደ ሥሙ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። በኑሮ ደረጃቸው ባለሀብት ለሆኑ ጥቂቶች ካልሆነ በቀር፤ በርካቶቹ የአገራችን የቤት እመቤቶች የቤታቸው ሠራተኛና አገልጋዮች ናቸው። በየቤታቸው ጓዳ ጎድጓዳ ኀላፊነት ስለሚወስዱ፤ ስለአለቅነታቸው እንጂ ስለተመቻቸው አይደለም ‘እመቤትነታቸው’ ብዬ አምናለሁ።

ነገሩ በእርግጥ የምርጫ ጉዳይ ነው። የአገራችን ጥቂት የማይባሉ ፊልሞች የሚፈጥሯቸው ዓይነት ጥገኝነት የሚመርጡ ሴቶች ካሉ፤ እመቤት ሆነው በትዳር አጋራቸው ገቢ ሊኖሩ ይችላሉ። በምናውቀውና በብዛት በምናየው እውነት ደግሞ፤ ልጆች ለማሳደግና በቤት ውስጥ ሌላ ሠራተኛ ላለመቅጠር፤ ቤተሰባቸውንም በሚገባ ለመንከባከብ፤ በምርጫና ፍላጎታቸው ሚስቶች ከቤት ይውላሉ።

ደግሞ ሳይፈልጉት ከቤት ለመዋል የሚገደዱ ሚስቶችም አሉ። ገና ትዳር ሊመሰርቱ በዋዜማው ሥራቸውን ለመተው ቃል እንዲገቡ የተገደዱ ጥቂት አይደሉም። ጥያቄው ግን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህ ነገር ምን ያህል ያስኬዳል የሚል ነው። ሚስቶችም ቢሆኑ በቤት ውስጥ አገልግሎት ተወስኖ በመቀመጥ እንዳይስማሙ ከበቂ በላይ ምክንያት አለ ባይ ነኝ።

አንዱ ምክንያት የኑሮው ክብደት ነው። ከቤተሰብ አባላት መካከል በአንድ ሰው ገቢ ላይ ብቻ ተማምኖ ኑሮን መግፋት አይታሰብም። ወጪ እንጂ ገቢ ሲጨምር የማያስታውቅበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ልብ ይሏል። ከዚህም ሲከፋ፤ መቼም ክፉውን በሩቁ ይያዘውና፤ ቤቱን ቀጥ አድርጎ ያስተዳድር የነበረ አባወራ በሞት ቢለይ፤ ቤተሰቡ ዕጣ ፋንታው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት።

በተለይ ልጆች አቅማቸው ለሥራ ያልደረሰ ሲሆኑ ክብደቱን መገመት አይከብድም። ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ሴቶች እንዲህ ያለ የሕይወት ገጠመኝ የደረሰባቸው ናቸው። በእርግጥ በደህና ጊዜ በትዳር የተጣመሩ ጥንዶች፤ ባልም ሚስትም እየሠሩ ገቢ የሚያስገኙ ሆነውም፤ ጫናው በሴቷ ላይ እንደሚበረታ ግልፅ ነው። እርሷ የቤቷንም ሥራ ጨክና አትተወውማ!

የት እንደሆነ ባላውቅም አንዴ ካነበብኩት ጽሁፍ ተከታዩን ሐሳብ ቀሰምኩ። በቤት ውስጥ ብቻ ሆና ቤተሰቧን የምታገለግል ሚስት ወይም የቤት እመቤት ቤቷን ከብዙ ወጪ ትታደጋለች። የቤት እቃዎቿ በጥንቃቄ ይያዛሉ፤ ያሰኛትን መልካም ነገር ለቤተሰቧ ልታቀርብ ትችላለች። ከዛ ሲሻገር ግን፤ ቤቷንም ተቆጣጥራ፤ ወጥታ ሠርታም ለቤቷ ገቢ የምታስገኝ ሴት፤ ከቀደመችው እጥፍ ትርፋማ ናት። ተስፋ ይዘን በምናደርገው የኑሮ እንቅስቃሴ ነገዋ አያሰጋትም። ራሷን መቻሏ እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ነው። ባሎች ሆይ! ልብ በሉማ!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here