“ኢትዮጵያ አትፈርስም!”

0
1076

አበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጀነራል) ከ1987 እስከ 1993 ድረስ የኢትዮጵያ አየር ኀይል ዋና አዛዥ በመሆን አገልግለዋል። ውልደታቸውና ዕድገታቸው መቀሌ ሲሆን እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን እዛው መቀሌ ተከታትለው በወቅቱ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ሥር ይገኝ ወደነበረው በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት በመዘዋወር የከፍትኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዩኒቨርሲቲው ተቀላቅለዋል። የኹለተኛ ዓመት የፊዚከስ ተማሪ ሆነው በዕድገት በኅብረት አሊባቡር ዘምተውም አገልግለዋል። በይበልጥ በትግል ሥማቸው – ጆቤ – የሚታወቁት አበበ፥ በ1968 መጀመሪያ ላይ ሕወሓትን በመቀላቀል የትግል ሕይወትን ‘ሀ’ ብለው ጀምረዋል።

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በ1983 ከተቆጣጠረ በኋላና የሽግግር መንግሥቱን በሚመራበት ወቅት በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ አዲስ አበባን የሚያጠቃልለውን የሰሜን ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ በመሆን አገልግለዋል። አየር ኀይልን በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በዋና አዛዥነት ከመሩ በኋላ በ1993 በአስገዳጅ ጡረታ ተገልለዋል።
በ1994 በ48 ዓመታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍልን መደበኛ ተማሪ በመሆን የተቀላቀሉት አበበ፥ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቴን በዚህ ሁኔታ በመከታተሌ ‘በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ’ እንዲሉ ኹለት መልካም አጋጣሚዎችን ፈጥሮልኛል ይላሉ። አብሬ ከምማራቸው ተማሪዎች ጋር ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት ስለነበረኝ ከነተግዳሮቱ አዲሱን ትውልድ በደንብ እንድረዳው አስችሎኛል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሌላው መልካም አጋጣሚ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በሰሜን አሜሪካ በዓለም ዐቀፍ ሕግ እና ሕገ መንግሥት ላይ እንዲሠሩ ዕድሉ ፈጥሮላቸዋል።

ዳግም ወደ ሥራ ሕይወት ሲመለሱ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከመምህርነት እስከ ፌደራሊዝም ተቋም ዳይሬክተርነት አገልግለው በጡረታ እንደገና ተገልለዋል። በአሁኑ ወቅት በሰላምና ደኅንነት የዶክትሬት ዲግሪ እጩ ናቸው።

በመጪው ሳምንት “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት፡ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ደውል” በሚል ርዕስ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ያቀረቡትን ጥናት መነሻ በማድረግ የፃፉት መጽሐፍ ለተደራሲያን ይቀርባል። መጽሐፉ በዋናነት የኢትዮጵያን ማኅበረ ፖለቲካ በሰፊው የሚዳስስ ሲሆን የኢትዮጵያን የደኅንነት ፖሊሲ ከአፍሪካ ቀንድ፤ ከቀይ ባሕርና ዓለም ዐቀፍ ሁኔታ አንጻር እንዲሁም የማንነት ጥያቄንና ፌደራሊዝሙን በጥልቀት እንደሚዳስስ አበበ ይናገራሉ።

ባለቤታቸው የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ጄነራል ሲሆኑ የኹለት ልጆች አባትና የሦስት ልጆች አያት የሆኑት አበበ፥ “ብሔርንና ዜግነትን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካ እደግፋለሁ፤ አግላይና ጠቅላይ ኢትዮጵያዊነትን እንዲሁም አግላይ ብሔራዊነትን እጠላለሁ” ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአጽንዖት ይናገራሉ።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከአበበ ተክለ ሃይማኖት ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ሰኔ 15 በአማራ ክልል ተካሔደ የተባለውን ድርጊት መፈንቅለ መንግሥት ነው ማለት ይቻላል?
አበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጀነራል)፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ “የመፈንቅለ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ ምንድን ነው? ከመፈንቅለ መንግሥት በመለስ ያሉት አመፆችስ ምንድን ናቸው?” የሚሉት ጉዳዮች በደንብ መታየት አለባቸው። አለበለዚያ ዋጋ የሌለው የቃላት ክርክር ብቻ ይሆናል።

በእኔ አመለካከት መፈንቅለ መንግሥት ዋናውን የመንግሥት አከርካሪ በተለይ መከላከያውን ማዕከል በማድረግ ለመምታት የሚደረግ ሙከራ ነው፤ ሊሳካ ወይም ላይሳካ ይችላል። ወታደራዊው ኀይል በሙሉ ቁመና ባለበት ሁኔታ መፈንቅለ መንግሥት ነው ማለት አይቻልም። የሆነው ሆኖ መፈንቅለ መንግሥት ነው አይደለም የሚባለው የአመጽ ደረጃውን ለማመልከት ነው። መፈንቅለ መንግሥት ነው ከተባለ በርግጥም መንግሥት ተሸብሯል ማለት ነው። ድርጊቱ የተፈጸመው ትልቅ ከሚባሉት ክልሎች መካከል በአንዱ ውስጥ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ስቧል።

መፈንቅለ መንግሥት ለማለት በጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥና የሠራዊቱ መዋቅር አካባቢ አከርካሪ ለመምታት የሚደረግ ሙከራ መሆን አለበት። ስለሆነም የጦር ኀይሎች እንቅስቃሴ መታየት ነበረበት። ቢያንስ ቢያንስ አንድ ብርጌድ ወይም አንድ ክፍለ ጦር፤ ብዙ ወታደራዊ መኮንኖች የሚሳተፉበት ያሉበት፣ መንግሥት እናቋቁማለን ብሎ ታስቦ የሚደረግ ሙከራ ነው። ይህ ሲሆን አገሪቱን ለአደጋ ያጋልጣል።

ባሕር ዳር ላይ የተወሰኑ ጀብደኞች ባደረጉት ጥቃት ከፍተኛ ጥፋት ደርሷዋል።ከፍተኛ ጥፋት በተፈፀመ ቁጥር መፈንቀለ መንግሥት ልንል አንችልም። በሚሊሻ የሚፈፀም መፈንቅለ መንግሥት ሰምቼም አላውቅም። የአመፁ መሪ በሚሊሻም ቢሆን የክልሉን ሚዲያ፣ ዓየር ማረፍያውን ተቆጣጥረው፤ ባሕር ዳር ያለውን የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዳይንቀሳቀስ በማድረግና ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት የተካሔደ አይደለም።

በአጭሩ መፈንቅለ መንግሥት የሽብር ዓይነት ሆኖ ደረጃው ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ የአገሪቱን መንግሥታዊ ስርዓት በተለይ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱን አከርካሪ ለመምታት የተደረገ እንቅስቃሴ አልነበረም። ይሔን ሁሉ ያልኩት ጄነራል ሰዓረ ከመሞታቸው ከሰዓታት በፊት “መፈንቅለ- መንግስት” ተብሎ በመታወጁ ጭምር ነው። መንግሥት መፈንቅለ መንግሥት ያለበት ምክንያት ለኹለት ነገር ሊሆን ይችላል። አንድም ተሸብሯል ወይም ኀይል ለመጠቀም ፈልጓል ማለት ሊሆን ይችላል።

መንግሥት መሸበር ግን አልነበረበትም። መንግሥት ሲሸበር በጣም መጥፎ ነው የሚሆነው፤ መፈንቅለ መንግሥት መባሉ በራሱ ሽብር የመፍጠር አቅም አለው። በውጪ ያለውንም [የአገር] ገጽታ ያበላሻል።

የጄነራል ሰዓረ ግድያ በጣም ከባድ ነው። ለአገሪቱም ከባድ ኪሳራ ነው። የእሳቸው ግድያ ቢሆን ግን መፈንቅለ መንግሥት ሊያሰኘው አይችልም። ምክንያቱም የጦር ጠቅላይ አዛዥ ቢሮ ማለትም የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አካባቢ ምንም ችግር አልገጠመም። ሌላ የሠራዊት እንቅስቃሴ ባልነበረበት ሁኔታ የመከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ ተቋማዊ አደረጃጀቱ የጠበቀ በመሆኑ ነው። በ1999 ወይም 2000 በነብ/ጄነራል ተፈራ ተፈፀመ የተባለው “መፈንቅለ መንግሥት” ገርሞኝ ነበር። ሽብር ሆኖ እያለ መንግሥት ምን ስለፈለገ ነው “መፈንቅለ መንግሥት” ያለው? ነበር ያልኩት በአጭሩ የሰኔ 15 ዘግናኝ ኪሳራ ቢደርስም ተመሳሳይ ነው።

መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ከባድ አደጋ እንዳይደርስ ምን ማድረግ አለበት፤ አደጋም ከደረሰም በኋላ የቀውስ አያያዙን እንዴት ይገመግሙታል?
ወቅታዊውን ሁኔታ ስንመለከት የባሕር ዳሩና የአዲስ አበባው ክስተቶች የመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የመረጃና ደኅንነት (‘ኢንተለጀንስ’) ተቋሙን ድክመት በተወሰነ መልኩ ያሳያሉ። የጀነራል ሰዓረ ግድያ ትልቅ ማሳያ ነው። ሌሎች ማሳያዎችም አሉ። ለምሳሌ በጌዲዖ የ800 ሺሕ ተፈናቃዮች ጉዳይ በጊዜው ታወቆ ተመጣጣኝና ወቅታዊ እርምጃ አልተወሰደም። ይሔ የሚያሳየው የፖለቲካ ስርዓቱ ደካማ መሆን የመረጃና ደኅንነት ሥራውን አብሮ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል።

ነገር ግን ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው ወይም ወቀሳ የሚሰነዘረው በመረጃና ደኅንነት መውደቅ ላይ ነው እንጂ ዋናው ችግሩ ከፖለቲካ ውድቀት ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ መፈንቅለ መንግሥት አካሔዱ የተባሉት ግለሰቦች በግልጽ ጦርነት ሲያውጁ ነበር። በግሌ በጣም በቅርበት ጉዳዮችን እከታተል ነበር። የተረዳሁት ነገር ቢኖር የአማራ ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል፤ እነዚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች ደግሞ ጦርነት ያውጃሉ።

ፌደራል መንግሥቱም ሆነ የክልሉ መንግሥት ይሔ ወንጀል ነው ብለው አላስቆሙትም። በዚሁ ምክንያት ፖለቲካዊ ከባቢው እየተረበሸ ሲሔድ የመረጃና ደኅንነቱ ሁኔታ በዛው ልክ እየተዳከመ ይሔዳል። መረጃና ደኅንነቱ በተመቻቸ የፖለቲካ ሁኔታ ነው የሚሠራው። የሚያጠናው ደግሞ የሕዝቡን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ሳይሆን አሸባሪዎች እንዳይኖሩ፣ በአገር ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ፣ የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ ጉዳዮች ነው። የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲበላሽ የመረጃና ደኅንነት ተቋሙ በዛ ልክ መዳከሙ አይቀርም። በመረጃና ደኅንነት ተቋም ብዙ ሥራዎች መስራት ይገባል ፖለቲካው ካልተስተካከለ ግን ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው። የመንግሥትና የሕዘብ አገልጋይ መሆኑ ቀርቶ የአንድ አንጃ መሣሪያም ሊሆን ይችላል።

የራያንና የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ስለሆነ ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን በኀይል እናስመልሰዋለን ከተባለ ጦርነት ማወጅ ነው። ይህ ደግሞ ወንጀል ነው። የክልሉ መንግሥት፣ ፌደራል መንግሥቱ ወይም ዐቃቤ ሕጉ ጣልቃ ገብተው ማቆም ነበረባቸው። ማንኛውም ጥያቄ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው መስተናገድ ያለበት።

በነገራችን ላይ ሕዝቡ የሚለው ሌላ፥ መንጋው የሚለው ሌላ እንደነበር የተካሔዱ ስብሰባዎችን መመልከት ይቻላል። የአማራ ሕዝብ እኛ ከትግራይ ጋር ጦርነት አንፈልግም፤ መንግሥት ግን አልደገፈንም ሲሉ ተደምጠዋል። ይሁንና በመንግሥት መዋቅር ሥር የነበሩት ፅንፈኞች በፈለጉት መንገድ መንጋውን ይነዱት ነበር። ለዚህ ነው መሰረታዊ ውድቀቱ የፖለቲካው ነበር ያልኩት።

የአገር መረጃና ደኅንነት ተቋምን ድርጅታዊ ብቃት እንዴት ይገመግሙታል?
በመጀመሪያ የመረጃና ደኅንነቱን ተቋም በተመለከተ ስህተት ተሠርቷል። የደኅንነት ተቋማት እኛን ነው የሚጠብቁን፥ እኛም እነሱን መጠበቅ አለብን። ጥፋት ያጠፉ ይጠየቁ በሚለው ላይ ምንም ችግር የለብኝም፤ መጠየቅ አለባቸው። ተቋሙን ግን ጠላት ካደረግነው፣ ካጣጣልነው ከባድ ጉዳይ ነው የሚሆነው። [ከተቋሙ] ከላይ እስከታች የነበሩ ሠራተኞች በብዛት እንዲሰናበቱ መደረጉ ትክክል አይደለም። ዐቃቤ ሕግም የሰጠው መግለጫ የተቋሙን ተዓማኒነት ያሳጣል። መስተካከል ያለበት መስተካከል፣ መጠየቅ ያለበትም መጠየቅ አለበት። የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ከነጉድለቱ ለ25 ዓመታት ጠብቆናል።

ለምሳሌ አልሸባብ በኬኒያ ውስጥ የፈለገውን በሚያደርግበት ወቅት እኛ ግን ደኅንነታችን ተጠብቆ ነበር። ይሁንና ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ መሥሪያ ቤቱ የነበሩበት ጉድለቶችንና ጥፋቶችን ማጋለጥ የተቋሙን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ እየከተተው ነው።

አንዳንዶች አሁንም ኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት አለባት በሚሉበት ሁኔታ የመከላከያ ሠራዊቱ ሚና ምን መሆን ይገባዋል?
በመሰረቱ መከላከያ የሰለጠነው፣ በጀት የሚመደብለት፣ አውሮፕላንና ታንክ የሚገዛው አገር ውስጥ ያለውን ደኅንነት ለመጠበቅ ሳይሆን ዋናው ተልዕኮው አገራችንን ከውጪ ጥቃት ለመከላከል ነው። በዚህ ሁኔታ የአገር ውስጥ ተልዕኮ ተጨማሪ ነው የሚሆነው። የውስጥ ደኅንነት ኀይሎችና የክልል ፖሊስ የማይችሉትና የግድ ሲሆን ነው መከላከያ ሠራዊቱ መግባት ያለበት። መከላከያ ሠራዊቱ ሳይፈለግ ነገር ግን ግድ ስለሆነ ብቻ ነው የሚገባው።

ስለዚህ አሁን ያለው የፀጥታ ችግር ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አንደኛ የነበረው ስርዓት ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ትግራዋይ መብቱን ሲጠይቅ አንተ ጠባብ ወይም ከ1993 በኋላ ደግሞ አንጃ ነህ ይባላል። አማራ ክልል ውስጥ የአማራ ሕዝብ መብት ሲጠየቅ ትምክህተኛ ይባላል። በተመሳሳይ በኦሮሚያም የኦሮሞ መብት ሲጠየቅ ኦነግ ነህ ይባላል። ዞሮ ዞሮ የችግሩ ምንጭ የዴሞክራሲ እጥረትና ፅንፈኝነት ሲሆኑ እነርሱንም ያመጣቸው ስርዓቱ ነው። መብትን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ አፈና ለፅንፈኝነት ሙቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

ፅንፈኝነት ስል ብሔርተኛነትና ኢትዮጵያዊነት ሁሉ ፅንፈኛ ነው እያልኩ አይደለም። እኔ ብሔርተኝነትን በኹለት መልኩ ነው የማየው። ፅንፈኛ ኢትዮጵያዊነት አለ፥ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያዊነት አለ፤ ፅንፈኛ ብሔርተኝነት አለ፥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አለ። አሁን በየትኛውም ክልል የፅንፈኝነት መነሳሳት አለ። ለምንድን ነው ይህ የሆነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሕዝቡ ስለታፈነ ነው። አፈና ባለበት ሕዝቡ ፅንፈኛው የሚታገልለት ይመስለዋል። አሁን ትግሉ መሆን ያለበት በፖለቲካ መታገል ነው፤ ደሞክራሲያዊ ምኅዳሩን ማሰፋት ነው መሰረታዊ መፍትሔው። ፅንፈኞች ጦርነት እንዲያውጁ ወይም ሌላ ወንጀል እንዲፈፅሙ መፍቀድ የለበንም። እነብ/ጀነራል አሳምነውን ብትወስድ የፈለጉትን ሲናገሩ ሕዝቡ አይሆንም በሚልበት ጊዜ የሕዝቡን ድምፅ የሚሰማ መንግሥት አልነበረም። አሁን የተፈጠረው ሁኔታ በሽግግር ወቅት የሚፈጠር ጉዳይ ነው። የእኛ ሽግግር እጅግ ከባዱ ዓይነት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጡ በኋላ የተሳካ ማሻሻያዎች ካደረጉባቸው ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምትነት በተደጋጋሚ ሲጠቅሱት የሚሰማው መከላከያውን ነው። ፖለቲካው ደግሞ ብሔርን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑና ከፅንፈኛ ብሔርተኝነት ብቅ ከማለት አንጻር በመከላከያ ሠራዊቱ አቋምና ግዳጅን በብቃት መወጣት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖው እስከምን ድረስ ነው?
መጀመሪያ በመከላከያ ተቋም ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የደኅንነት ፖሊሲ መኖር መቻል አለበት። የነበረው የደኅንነት ፖሊሲ የ1994ቱ አቶ መለስ እያሉ የተፃፈው ነው። ስለዚህ ፖሊሲ ሲነገርም አይሰማም። መንግሥት ተደብቆ የደኅንነት ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑን ሰምቻለሁ። የደኅንነት ፖሊሲ ተደብቆ አይሠራም። የደኅንነት ፖሊሲ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ የመከላከያ ማሻሻያ የሚባለው ነገር የሚገርም ጉዳይ ነው።

አንዳንድ ትናንሽ ለውጥ በሠራዊቱ ውስጥ እዚም እዛም ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ምን ዓይነት መከላከያ ሠራዊት ያስፈልጋል፣ ምን ዓይነት ይዘት ይኑረው፤ አደረጃጀቱ፣ አሠራሩ፤ ትጥቁ ምን ይምሰል የሚሉትን የሚወስነው የደኅንነት ፖሊሲ ነው።

አዳማ በተከበረው የመከላከያ ቀን ተገኝቼ ነበር። “ለውጡን እንደግፋለን” የሚል መፈክር አይቼ ጥያቄ አንስቻለሁ። መከላከያ ሠራዊት ለውጡን እደግፋለሁም አልደግፍምም ማለት የለበትም ምክንያቱም ለውጡ ፖለቲካዊ ስለሆነ ብዬ ተናግሪያለሁ።

በአጠቃላይ በመከላከያ ውስጥ አንዳንድ የሰዎችና የአሠራር ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ፤ መሰረታዊ ተቋማዊ ማሻሻያ ነበር ለማለት ግን አስቸጋሪ ነው።
ፖለቲካው ከተስተካከለ መከላከያውም የበለጠ እየተስተካከለ ይሔዳል። ፖለቲካው የብሔር መሆኑ አይደለም ችግሩ፤ የብሔር መብት አለ ተብሎ በአንድ በኩል መብት መስጠት፤ በሌላ በኩል መብት መንፈግ ስለሆነ ነው። እስካሁን ግን [የመከላከያ ተቋም] በተሸለ ሁኔታ ያለ ይመስለኛል። ፖለቲካው እየተበላሸ ከሔደ ግን መዳከሙ አይቀርም።

እርሶ ካሎት የካበተ ወታደራዊ ልምድ፣ በሰላምና ደኅንነት ዙሪያ ጥናትና ምርምር እንደማድረግዎ ምን ዓይነት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ?
በዋናነት የደኅንነት ፖሊሲ አመላከች አቀሜ የፈቀደውን መጽሐፍ ለውይይት እንዲሆን አቅርቢያለሁ። በመንግሥት በኩል ማለትህ ከሆነ አንድ ጊዜ ብቻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ባዘጋጁት መድረክ እንደተሳታፊ ተገኝቻለሁ።

የፌደራል መንግሥቱ መዳከምና የክልሎች ተገዳዳሪ ሆኖ መውጣት በሰፊው ይታያል ብለው አንዳንዶች ይናገራሉ። በተለይ በየክልሉ የሚገኙት ልዩ ኀይል ከሕገ መንግሥት ወይም ከአጠቃላይ የአገር ደኅንነት አንጻር መኖሩን እንዴት ይገመግሙታል?
ሕገ መንግሥቱን ስንመለከት የአገሪቱ ሰላምና ጸጥታ በክልሎችና በፌደራል መንግሥቶች ነው የሚጠበቀው ይላል። ስለዚህ ፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው ደካማ ክልሎች ስለነበሩን ነው። ክልሎች ሁሉንም ነገር ከማዕከላዊ መንግሥት ይጠብቃሉ፤ እነርሱ በራሳቸው የሚሠሩት አልነበረም።

አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አብዛኛው ሕዝብ ያለው በክልሎች ነው። ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥንካሬ ባሻገር ክልሎች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሰረት ጸጥታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው። ይህ ማለት ጠንካራ ክልሎች ሲኖሩ ጠንካራ ኢትዮጵያ ትኖራለች፤ ጠንካራ ኢትዮጵያ ስትኖር ጠንካራ ክልሎችም ይኖራሉ። አሁን ኹለቱም ተዳክመዋል።

ለዚህ መሰረታዊ ችግር ለሕዝቡ የማይመጥኑ መሪዎች ክልሎች ውስጥ ስለነበሩ ነው። በአብዛኛው ክልልች የነበሩት አመራሮች እንደማሳያነት ማንሳት እንችላለን። የወልቃይት ጉዳይ ለዘመናት ሲነሳ ነበር። የአማራ ክልል አመራሮች ጥያቄው ተገቢ ካልሆነ ሕዝቡን በማሳመን እንዲቀር ወይም ሕጋዊ መሰረት ካለው ሁሉም የሕግ አግባብ ተከተለው መፍትሔ ያላመጡበት ምክንያት ምንድነው? ታፍነን ነበር እንዳይሉ ታይቶ የማይታወቅ ዴሞክራሲ አለ ሲሉን ነበር። የማያሰራቸው ከሆነ ደግሞ ከሥልጣን መልቀቅ ነበረባቸው። ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም በተመለከተ ከ24 ዓመት በፊት በሕገ መንግሥቱ አስቀምጧል። የኦሮሚያ አመራሮች ይህን ልዩ ጥቅም ማስከበር ነበረባቸው። እነዚህ ሁሉ የደካማ ክልሎች መኖር ማሳያዎች ናቸው።

ጸጥታቸውን ራሳቸው የሚያስከብሩ ክልሎች መኖር ለአገራችን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ክልሎች ጸጥታቸውን ለማስከበር ኀይል መመደብ አለባቸው፤ ይሔ ኀይል ከክልል ክልል ሊለያይ ይችላል። ሁሉም ክልሎች ደግሞ ልዩ ኀይል ያስፈልጋቸዋል ማለትም አይደለም። እንደ የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል። ከመከላከያ ጋር አልሻባብን መግቢያ ያሳጠው ሰላማችንን ያስጠበቀው የሶማልያ ክልል ልዩ ኀይል እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል። አስከፊ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ስለነበር ተቋም ይፍረስ አይባልም ማስተካከል እንጂ። በትግራይ በኤርትራ ድንበር አካባቢ በተመሳሰይ ሊታይ ይችላል። ብዙ የታጠቀ ሕዝብ ባለበት አገር በተለይ በድንበርና አርብቶ አደር ባለበት ሁኔታ ልዩ ኀይል አያስፈልግም ማለት የዋህነት ይመስለኛል።

መሰረታዊ ችግሩ ላይ ማትኮር ይገባናል። በገዢው ግንባር እህት ድርጅቶች ውስጥ የሚታየው የጠላትነት መንፈስና እንቅስቃሴ ሳታስተካክል ምልክቶችን መፍታት አይቻልም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁንም የሥራ አስፈፃሚው ማኅተም መቺ ነው፤ ይሻሻል ይባላል እንጂ ይፍረስ አይባልም። ልዩ ኀይልን ሌላን ለማጥቃትና ለመተናኮል ማዘጋጀት ከሆነ ግን እሱ ፀረ ሕገ መንግሥት ነው፤ ወንጀል ነው።

ዋናው ጥያቄ ጠንካራ ክልሎች ያስፈልጉናል አያስፈልጉንም የሚለው ነው። ይህ ሁሉ ግርግር የተፈጠረው ጠንካራ ክልሎች ስላልነበሩ ነው። ሕዝባቸውን መሰረት ያደረጉ፣ ሕዝባቸውን የሚታደጉ ክልሎች መሆን አለባቸው።

በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል መንግሥታት መካከል ፍጥጫዎችና የቃላት መወራወሮች መስማት ከጀመርን ከርመናል። በቅርቡም የትግራይ ርዕሰ መስተዳደር ለአንድ መገናኛ ብዙኀን በሰጡት ቃለ ምልልስ ከሕዝባቸው ከፍተኛ የእንገንጠል ግፊት እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል። በአጠቃላይ በትግራይና በአማራ ክልል እንዲሁም በትግራይና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ያዩታል? የግንኙነቶቹ ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል ይላሉ?
አሁን ያለንበት የሽግግር ሁኔታ ያመጣው ከባዱ ነገር ይሔ ነው። ሽግግር በሌሎች አገራት ተሞክሮ ቀውስ ሲያጋጥም ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚዎች ስትራቴጂያዊ መመቻመች (strategic compromise) ያደርጋሉ፤ መፍትሔዎች ያስቀምጣሉ። ወደ እኛ አገር ስንመለስ ግን ኢሕአዴግ የሥልጣን ጥማት ነበረው፤ እኔ ብቻ የሚል ትዕቢትም እንዲሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ልፍስፍሶች ናቸው። የገዢውና የተቃዋሚዎች ስትራቴጂያዊ መመቻመች አንድ መልካም አጋጣሚ ይሆን ነበር፤ ይህ ግን አልሆነም።

ኹለተኛው አማራጭ ገዢው ግንባር በራሱ ውስጥ ስትራቴጂያዊ ማመቻመች ማድረግ ነበረበት፤ ነገር ግን አላደረገም። እንደ ፓርቲ ርዕይ አልነበረውም፤ ከርዕይ የሚነሳም ፍኖተ ካርታ የለውም። የኢሕአዴግ ግምገማ ያለፈውን እንጂ የወደፊቱን አሻግሮ የሚያይ አልነበረም።

ከግምገማቸው በኋላም ምርጫ ሲያደርጉ፥ አዴፓና ኦዴፓ በጓሮ በር ተመሳጥረው በሕወሓት ላይ ዱብ እዳ አዘነቡ፣ በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ሕወሓቶች አኩርፈዋል። አዴፓና ኦዴፓ ደግሞ ጠላታቸውን እንዳሸነፉ አድርገው ነው የወሰዱት። አዴፓና ኦዴፓ ፀረ ሕወሓት ግንባር ነው የፈጠሩት እንጂ ይህቺን አገር ከዚህ ወደዚህ እናደርሳታለን በሚል ግልፅ ዓላማ አልነበረም።

ይህ ማለት በግንባሩ ውስጥ ማሸነፍና መሸነፍ እንጂ ማመቻመች አልነበረም። የዶክተር ዐቢይ መመረጥ በስትራቴጂያዊ መመቻመች ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር። ይሁንና እኔ በግሌ በኢትዮጵያ ከመጋቢት 2010 በፊት የነበረውን ሁኔታ ከዛ በኋላ ካለው ጋር ሳነፃፅረው አሁን ያለንበት ይሻላል፤ ማስታገሻ ሆኗል። በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም የሠሯቸው ጥሩ ጥሩ ሥራዎች ነበሩ፤ አሁን ግን ጥሩና መጥፎ ሥራዎች እየተደበላለቁ አስቸግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በመቐለ ተገኝተው ከሕዝብ ጋር ከተወያዩ በኋላ በ25 ሰዎች ላይ ዳሰሳ አድርጌ ነበር። ከ25ቱ ኻያ ኹለቱ ዶክተር ዐቢይን ደግፈዋል፤ 2ቱ ያልወሰኑ ሲሆኑ አንዱ ብቻ ነበር የተቃወማቸው። በየራሳቸው መንገድ የሕዝቡ ሁኔታ ከሚያጠኑ ፖለቲከኞት እንደተረዳሁት የትግራይ ሕዝብ ለውጥ በከፍተኛ ይፈልግ ነበር። በኋላ ላይ ግን ዶክተር ዐቢይ ብዙ ነገር አበላሹ።

አሜሪካ ሔደው የተናገሩት ነገር፤ አፋር ሔደው የተናገሩት ነበር፤ መንገድ ሲዘጋ ዝም ማለታቸው፤ ዓቃቤ ሕግ ያስተላለፈው “የቴሌቪዥን የካንጋሮ ፍርድ”፤ ከኤርትራ ጋር የተደረጋው የሰላም ስምምነት አተገባበር ወዘተ በእነዚህ የትግራይ ሕዝብ የመከዳት ስሜት ተሰማው። ለውጥ የማይፈልጉ ኀይሎች እየተጠቀሙበት ነው።

በትግራይ ሕዝብ ላይ የመከዳት ስሜት ማደሩ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ። ይሁንና [የትግራይ]መገንጠል የተባለውን በተመለከተ እኔም ራሴ በጣም አፍሪያለሁ። ከአንድ መሪ የሚጠበቅ ሆኖ አላገኘሁትም። ምን ዓይነት ጥናት ተጠንቶ ነው? እኔ ሳድግ በነበረው ሁኔታ ትግራይና ኢትዮጵያ ለእኔ አንድ ናቸው። ለትግራዋይ ሥነ ልቦና ኢትዮጵያና ትግራይ አንድ ናቸው። የተወሰኑ አክቲቪሰቶች የእንገንጣል አጀንዳ እንደሚያራምዱ አውቃለሁ። መላው የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አይመስለኝም። ኹለተኛ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅመው ፍትሓዊ አንድነት ነው። ፀረ ፍትሕ የሆነች ኢትዮጵያ ፀረ ትግራይ፣ ፀረ ኦሮሞ፣ ፀረ አማራ ፀረ ሁሉም ናት፤ ፍትሐዊ ኢትዮጵያ ደግሞ ለሁሉም ትጠቅማለች።

[የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች] በሽግግሩ አመጣጥ በጠላት ዓይን ተያይተዋል፣ ብዙ ገንዘብ እየረጩ አክትቪስቶችን አደራጅተዋል። እንደ ኢሕአዴግ ይሰባሰባሉ፥ ነገር ግን የሚናገሩት ለየብቻ ነው። ይህ ሁኔታ መርገብ ይገባዋል፤ አደገኛ አካሔድ ነው።

በእርግጥም ይሔ በራሱ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ከዚህ በፊት ነጻነት የሌላቸው ብሔራዊ ድርጅቶች የሚመሩት የክልል መንግሥታት ነበሩ፤ አሁን ከነብዙ ያልጠሩ አስተሳሰቦችና መዝረክረክ ቢሆንም ነጻነት ያላቸው ብሔራዊ ድርጅቶች እየሆኑ ነው። ይሔ ሁኔታ ሁሉም የመደራደር አቅም ይዘው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፤ ይህም በራሱ የመድበለ ፓርቲ ስርዓትን ለመተግበርና ዲሞክራሲን ለመገንባት ጥሩ ዕድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ካላት የውስጥ ችግር ባሻገር የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናው በጣም ስሱ እና የብዙ ኀያላን አገራት መነኻሪያ መሆኗ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የመከላከያ ሠራዊቱ ብቃትና የመረጃና ደኅንነት አቅሙ አስተማማኝ ነው ማለት ይቻላል።

በመጀመሪያ የተሟላና ውሕድ የደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አለን ወይ? ገና እየተሠራ ነው ተብሏል። ሒደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ነው ወይ? ይህን መሰረት አድርጎ የተለያዩ የቢሆን መላምቶች (scenarios) የሚያስቀምጥና የሚከታተል አደረጃጀትና አሠራር አለ ወይ? በዚህ ረገድ ምን እየተደረገ እንደሆነ አላውቅም።

በ1990-1992 ከኤርትራ ጋር ስናደርግ የነበረው ጦርነት እና አሁን ያለው ሁኔታ በጠቅላላው ተለውጧል። የደኅንነት መዋቅሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩትን የደኅንነት ምክር ቤት ጨምሮ ይህንን ይገነዘባል ወይ? ቀጣዩ የመን ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች ብሎ ታሳቢ ያደርጋል ወይ? ከዚህ አኳያ ምን ዝግጅት እየተደረገ ነው? ኳታር የባሕር በር ባይኖራት ኖሮ ምን ትሆን ነበር የሚለውን አይቶ የባሕር በር እንዴት ማግኘት አለብን የሚለውን ያስባል ወይ?

በጅቡቲ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና የሌሎች አገሮች ጦር ሰፈሮች አሉ። ይህ ምን ማለት ነው? ምን መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልናል? ምንስ ተግዳሮት አለው? የሚለውን ነገር በተሟላ መልኩ የሚመልስ ፖሊሲ ሊኖረን ይገባል። የባሕር ኀይል የማደራጀት ፍላጎት እጅግ ወቅታዊና ብዙ ነገር አመላካች ነው። አየር ኀይላችንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ አለበት። በእኔ ግምት ጦርነት እንዳይኖር ሁሉንም ነገር ማድረግ ቢገባንም ከአሁን በኋላ ተገደን የምንገባበት ጦርነት የሳይበር፣ አየር፣ ባሕር ኀይሎች ያላቸው ልዩ ሚና ያገናዘበ ዝግጅት ያስፈልጋናል።

የ1994ቱ የደኅንነት ፖሊሲ ዋናው ችግር አቶ መለስ እንደፃፉት ከዛ ሚኒስትሮቹ ተሰበሰቡ፣ ልክ እንደ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ማስታወሻ ነው የያዙት። ፖሊሲው ብዙ ጠንካራ ጎኖች ነበሩት፣ ይሁንና ኢሕአዴግ በራሱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ኅብረተሰቡ አልተወያዩበትም። በእርግጥ ዶክመንቱ ውስጥ ኅብረተሰቡ መወያየት አለበት ግን ይላል። ስለዚህ አዲሱ እየተዘጋጀ ያለው ፖሊሲ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጠቅላላ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ መሆን አለባቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባሕር ላይ የሚኖራት የውጪ ፖሊሲ ምን መሆን ይገባዋል ይላሉ?
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር አገር ናት። ቀይ ባሕር ያለኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያ ያለ ቀይ ባሕር ሰላም ሊኖር አይችልም። የቀይ ባሕር ክልል በዋናነት የአፍረካ ቀንድና የመካከለኛ ምሥራቅና የገልፍ አገሮች ያጠቃለለ ነው።

የተለመደው ባሕላዊ የውጭ ጉዳይ አመለካከት አለ፤ ለምሳሌ አረቦች ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው የሚል። በመጀመሪያ ከእንደዚህ ዓይነት አመለካከት መራቅ አለብን። ጠላትነት ሊኖር ይችላል ነገር ግን አናጋንነው። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፤ ያለ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ሰላም አያገኝም። ስለዚህ ኢትዮጵያም ትፈለጋለች የሚለውን መያዝ አለብን።

በዋናነት በቀጣናው ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ብሎ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤ ትኩረት ማድረግ ያለብን መልካም አጋጣሚዎችን ማስፋት ላይ እንጂ ለተግዳሮቶቹ መዘጋጀት ላይ ብቻ መሆን የለበትም።

ሌላው የአረቦች የዘይት ሀብት በቅርብ ዐሥርታት ውስጥ ያልቃል የሚባለውን ታሳቢ በማድረግ ወደ ሌላ ኢኮኖሚ ዘርፎች ለሚያደርጉት ሽግግር ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ከሚፈጥሩላት ዕድሎች መካከል ነው። ለዚህም እንቅስቃሴያቸው ኢትዮጵያ በግብርናው፣ በቴክኖሎጂው፣ በትራንስፖርቱ በግንባር ቀደምትነት ተመራጭ አገር ናት። ስለዚህ በአግባቡ እስከ ተጠቀምንበት ድረስ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ይሰጣል። አረቦችና በእስራኤል፤ በአረቦችና ኢራን እና በሱኒና ሽዓት መካከል ያለው የተቀናቃኝነት ፍጥጫ የምንጠቀምበትን ተጨማሪ ዕድል ሊፈጥር ይችላል። ይሁንና አደገኛነቱ በተቀናቃኝ አገራቱ መካከል ይደረግ የነበረው የኢኮኖሚ ተቀናቃኝነት ወደ ወታደራዊ ተቀናቃኝነት መለወጡ ነው። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በደኅንነቱ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል።

የአፍረካ ቀንድ እንብርት ኢትዮጵያ ናት። ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት በእኩልነትና ወንድማማች መንፈስ ከጎረቤቶችዋ ጋር አብሮ ማደግ ነው። ነፃነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሰላምና ልማት አብሮ መሥራት ያስፈልጋል።

ሽግግሩ አሁን በሚሔድበት አካሔድ ወደሚፈለገው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ይወስዳል ብለው ያስባሉ?
ስለ ሽግግሩ ስናነሳ መሠረታዊ ስህተት ሆኖ የሚታየው ሁል ጊዜ በልኂቃን መካከል ያለውን እሰጣ ገባ ብቻ ነው የምናየው። አጠቃላይ ፖለቲካውን እንደ ማዕከላዊ ስበት ሆኖ የሚይዘው ሕዝቡ ነው። በሕዝቡ ዘንድ ያለው ጥንካሬ አገሪቷን ይጠብቃታል። በሕዝቡ ያለው ድክመት፣ ድኅነትና ኋላ ቀርነት አገሪቱን ያፈርሳል። ይሔንን ካላየን ፖለቲካ ነጋዴዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎች ብቻ በማየት ይህቺ አገር ትቀጥላለች አትቀጥልም የሚለው ስህተት ይመስለኛል።

እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ እንዴት ቆየች የሚለውን ማንሳት ይኖርብናል። መንግሥት ባልነበረበት ሁኔታ በ1966፤ 1983 እንዲሁም 1997 ቀውስ የሕዝቡን ጨዋነት አይተናል። በተለይ በ1983 ወደ አዲስ አበባ ስንገባ የራበው፣ የተሸነፈና ሞራሉ የወደቀ ወታደር ወደ ሕዝቡ አላነጣጠረም። ያም የሚያመለክተው የኅብረተሰቡ እሴት መኖሩን ነው። በወቅቱ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ኢሕአዴግ ባይኖርም ሕዝቡ ግን ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነበር።

ከ2008 እስከ አሁን ብዙ ችግር ተፈጥሯል። እንደ ሌላ አገር ቢሆን ኖሮ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን መተላለቅም ይኖር ነበር። አገራችን እንደዚህ እንዳትሆን ያደረጓት ሦስት ነገሮች ናቸው።

አንደኛ የነፃነት አገር መሆናችንና ሥነ መንግሥትን የምንማረው ሳይሆን ባሕላችን ስለሆነ ነው። ኹለተኛው ሃይማኖት ነው። ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀጥሎ ክርስትናም ሆነ እስልምና ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቱና እንደ ዐሥርቱ ትዕዛዛትና የቁርዓን ብሂሎችን ባሕላችን በማድረጋችን እና ሦስተኛው እንደ ሁሉም የሰው ልጆች ሰላም፣ ልማትና መብት እንዲጠበቅልን መፈለጋችን ናቸው።

እነዚህ ሦስቱ ነገሮች እያሉ ኢትዮጵያ አትፈርስም! እየተንጫጩ ያሉት የፖለቲካ ልኂቃን የሕዝባችን ማዕከላዊ ስበት ጎትቶ ልካቸውን ያስገባቸዋል። ተስፋ ያላት አገር ናት የምለው ለዚህ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here