ኢትዮ ቴሌኮም ለሠራተኞቹ የቤት እና የመኪና ግዢ ብድር አመቻቸ

0
548

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ፍሬሕይወት ታምሩ ሐምሌ 1/2011 ለቴሌኮሙ ሠራተኞች በላኩት የውስጥ ማስታወሻ ቴሌኮሙ ከተለያዩ ባንኮች ጋር በሚፈጸም ውል ለሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት እና የተሸከርካሪ ብድር ለማመቻቸት መወሰኑን ተናገሩ።

በአሁኑ ወቅት ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት ቴሌኮሙ “የሠራተኞቹን መሰረታዊ የትራንስፖርትና የቤት ችግር ለማቃለል የሚያስችል የብድር ስምምነት ነው” ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ ዝርዝር አፈጻጻሙ በቀጣይ የሚገለጽ ነው ብለዋል።

ለወራት ሲደረግ በቆየው ድርድር ከተለያዩ የግል ባንኮች ጋር የመጨረሻ ስምምነት ላይ መደረሱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች የተናገሩ ሲሆን ቴሌኮሙ ያለውን ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ በባንኮቹ ሊያስቀምጥ ይችላል ብለዋል።

መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉ የአገልግሎት ክንፍ ለግል ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን በመወሰነው መሰረት በ2012 የበጀት ዓመት ማብቂያ ላይ ኹለት ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚገቡ ይጠበቃል።

በተያዘው ዓመትም ቴሌኮሙ ለሠራተኞቹ ደመወዝ ከመጨመር ባሻገር የተለያዩ ዓለማቀፍ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና የብቃት ማረጋገጫዎን እንዲያገኙ በማድረግ ለሚመጣው ውድድር እና የሰው ኀይል መፍለስ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጽ ቆይቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here