በአዲስ አበባ ከ20 ሺህ በላይ አባወራዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተባለ

0
686
  • በጎርፉ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሊወድም ይችላል

የክረምት ወር መግባቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች 20 ሺሕ 955 አባወራዎችና 990 ተቋማት ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። አደጋውን መከላከል ካልተቻለ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሊወድም እንደሚችል ተቋሙ አስጠንቅቋል።

የኮሚሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በአሁኑ ሰዓት በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች በጥናት ተለይተው ታውቀዋል። አቃቂ ቃሊቲ፣ ልደታ፣ ቂርቆስና አራዳ ክፍለ ከተሞች በተደጋጋሚ ጎርፍ የሚያጠቃቸውና በከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው። መሥሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ ለመከላከል አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ንጋቱ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በከተማዋ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 131 ቦታዎች በጥናት ተለይተዋል። ከእነዚህ መካከል 67 በወንዝ ተፋሰስ፣ 20 በፍሳሽ ማስወገጃዎች ጥበት ማነስና አለመኖር ወይም በቆሻሻ መደፈን ምክንያት፣ 10 በመልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተጠቅሷል። በሌላ በኩል በጎርፍ ምክንያት 26 አካባቢዎች ለመሬት መንሸራተት የተጋለጡ መሆኑን በቅርቡ ባለሥልጣኑ ያደረገው ጥናት አመልክቷል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንደሚለው፣ በመንገዶች ዳርቻ ያሉ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በፕላስቲክ ውሃ መያዣዎችና በተለያዩ ቁሳቁሶች በመደፈናቸው ውሃው ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ተከትሎ እንዳይሔድ በማድረግ የአደጋ ሥጋት እንዲጨምር አድርጓል።በተጨማሪም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ሎሚ ሜዳ በሚባለው አካባቢ የአስፋልት መንገድ ቱቦዎች በአግባቡ አለመገንባታቸውና የውሃ መፋሰሻ ባለመኖሩ 500 አባወራወራዎች ለአደጋ ሥጋት ተጋላጭ እንዳደረገ ጥናቱ አስታውቋል።

ንጋቱ ለጎርፍ አደጋ መባባስ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ችግሮች ሲገልጹ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፋፍረው ክፍት የተተዉ ጉድጓዶች፣ የውሃ መውረጃ ቦዮች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ወንዞች ላይ ተረፈ ምርቶችንና ቆሻሻዎችን መጣል በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው።

እንደተቋሙ ገለጻ፣ የከተማዋ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የመንገዶች አገነባብ፣ በርካታ ነዋሪዎች በወንዝ ዳር መኖራቸው፣ በከባድ ዝናብ ወንዞች መሙላት፣ የጎርፍ መከላከያ ግንብ አለመኖር፣ ሕገወጥ ግንባታዎች መንሰራፋት፣ በፕላን አለመመራት እና የመሳሰሉት ለአደጋዎቹ ክስተት ምክንያት ናቸው።

በአዲስ አበባ ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ንጋቱ፣ በከተማዋ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል። በዚህም ሳቢያ ባሳለፍነው ሳምንት በአቃቂ ቃሊቲ ኹለት ሰዎች መሞታቸውን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here