ማኅበራዊ ፍትሕ ስለማስፈን – የአዲስ አበባ ነፃ ዩኒፎርምና ደብተር ዘመቻ እንደማሳያ

0
792

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በቅርቡ ተማሪዎችን መመገብ፣ ደብተርና ዩኒፎርም በነፃ መስጠትን እንደ አንድ የማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈኛ መንገድ ማሳያነት የተጠቀሙት ቤተልሐየም ነጋሽ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደሃ ዜጎች መኖሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ እነዚህ ተግባራት እንደመልካም ልምድ መወሰድ ይገባቸዋል ይላሉ። ይሁንና ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈን በፖሊሲ የተደገፈ ተቋማዊ አሠራር መሆን እንዳለበትም ምክረ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

 

የኑሮ ውድነት እየተባባሰ ሲመጣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከጣሪያ በላይ ሲሆን፣ እንደ ዳቦና ዱቄት እንዲሁም ዘይት ያሉ ሸቀጦችን በዛው ዋጋ ማግኘት እንኳን ሲቸግር በተለይ የአገራችንን አብዛኛውን ሕዝብ የሚሸፍነው ዝቅተኛው ማኅበረሰብ የሚከፍለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው። በተለይ አገር ተረካቢ የምንላቸው ሕፃናት ከመቀንጨር እስከ ያልተመጣጠነ የአዕምሮ ዕድገት በድኅነትና የተመጣጠነ ምግብ ካለመመገብ ጋር በሽታ ተጨምሮ የድህነት ዋነኛ ተጠቂ ናቸው።

የተሻለ የሚባል ገቢ ላላቸው ሳይቀር መሠረታዊ ፍጆታን ማሟላት አስቸጋሪ ሲሆን በቀልድ እንደምንለው በተለይ የቤት ኪራይ ንረት፣ የትራንስፖርት ዋጋ ተጨምሮበት ገቢውና ወጪው ሳይመጣጠን አብዛኛው ሰው “በአስማት” የሚኖር እስኪመስል ኑሮ ፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር ምግብ ሳይመገቡ ትምህርት ቤት እየሔዱ ትምህርታቸውን መከታተል ካለመቻል እስከ ራሳቸውን ስተው መውደቅ እስኪፈጠርና ይህንንም መገናኛ ብዙኀን እስኪያወጡት ችላ ተብሎ ነበር። አሁን በመጀመሪያ በግለሰቦችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቀጥሎ በራሱ በመንግሥት ተነሳሽነት የምገባ ፕሮግራም በመካሔድ ላይ ይገኛል። በክልሎች ደረጃ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የምገባ ፕሮግራም ሲካሔድ የነበረ መሆኑ መረጃው ሲኖረኝ የክልል መንግሥታት ይህንን ይተግብሩ አይተግብሩ አላውቅም፤ መተግበር እንዳለበቸው ግን አምናለሁ።

በአገራችን እየታዩ ካሉ ብዙ አሳሳቢና ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ባሻገር በመልካም ሊጠቀስ የሚቻለውና በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ድጋፍ እየተቸረው ያለው ጉዳይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ከሳምንታት በፊት ይፋ ያደረጉት “ስጦታ ለአዲስ አበባዬ” የተሰኘ ለሚቀጥለው የትምህርት ዓመት ለ600 ሺሕ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ነፃ ዩኒፎርምና ደብተር ለመስጠት አቅዶ የተነሳው ዘመቻ አንዱ ነው። የከንቲባው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ እንደገለጸው በዘመቻው ኹለት ሳምንታት ብቻ ከ600 ሺሕ በላይ ደብተር በለጋሾች ሲሰጥ የዩኒፎርም ዲዛይን ዓይነቶችም ቀርበው በሕዝብ አስተያየትና ምርጫ ተደርጎባቸዋል።

በዩኒፎርሙ ላይ ከቀለና ዲዛይም ምርጫ ባሻገር የሴቶች ልዩ ፍላጎቶች (ሙስሊም ሴቶች ረዥምና ሂጃብ፣ ከሰባትና ስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ላሉ ሴቶች ጠቆር ያለ ቀለም ወዘተ) ሊካተቱ እንደሚገባ እንደሚታሰብበት በዚሁ አጋጣሚ እየገለጽኩ፣ መስተዳድሩ በተለያዩ መንገዶች እየተሰጡት ያሉትን አስተያየቶች በሚገባ አጢኖ መውሰድ ያለበትን እንደሚወስድ ተስፋ አደርጋለሁ።

የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን በየደረጃቸው ከፋፍሎ የደንብ ልብስ ለማዘጋጀት ያሰበው መስተዳደሩ የዘገየ ነገር ግን እጅግ መልካም የሚባል እርምጃ መውሰዱ ያስመሰግነዋል። በመንገድ ላይ ተማሪዎች የተቀዳደደ ዩኒፎርም ለብሰው የተቀደደ ጫማ አድርገው ማየት ሁል ጊዜም ልብ የሚነካ ነገር ነው። ጥቂት የሚባለው ቢሆንም የተወሰነው የማኅበረሰብ ክፍል የተሻለ ሲኖር አብዛኛው መሠረታዊ የሚባል ነገር ሳይኖረው፣ በተለይ ሕፃናት የዚህ ሰለባ ሆነው ማየት ልብ የሚሠብር ነው።

ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኩል ይፋ የተደረገው የ2019 ዓለም ዐቀፍ ዙሪያ መለስ የድህነት መለኪያ (Global Multidimensional poverty Index) መሠረት አገራችን ኢትዮጵያ 83.3 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ አሁንም በዙሪያ መለስ ድኅነት ውስጥ ይኖራል።

ዙሪያ መለስ የድኅነት መለኪያ ከተለመደው መለኪያ በተጨማሪ ጥልቀት ያለው፣ ሰዎች ድኅነትን በየቀኑ የሚኖሩበትን መንገድ የሚያሳይ መለኪያ ነው። በዚህ ዓይነቱ ድኅነት የሚኖሩ ሰዎች የመለኪያው አመላካቾች የተባሉትን ሦስት ነገሮች ያጡ ሲሆኑ አመላካቾቹ ጤና፣ ትምህርትና የኑሮ ደረጃ ናቸው።

በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ በመለኪያው አንጻር መሻሻል ብታሳይም 61.8 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የከፋ በሚባል ድኅነት ውስጥ ይኖራል። የድኅነት የመጨረሻ መስመር ከተባለው በቀን 1.9 ዶላር ገቢ በታች የሚገኘው ሕዝቧም ከአጠቃላዩ 26.7 በመቶ ይሆናል። በዚህም አገራችን ከናይጄሪያና ሕንድ ቀጥሎ በዚህ ዓይነት ድኅነት ውስጥ የሚኖሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በመያዝ ትጠቀሳለች። የድኅነቱን መሻሻል ማነቆ የሆነበት ደግሞ የሕዝባችን ቁጥር በፍጥነት እያደገ መምጣት ነው።

ሪፖርቱ ጨምሮ እንዳለው ደግሞ ከ10 ዓመት በታች ዕድሜ ላይ ካሉ የኢትዮጵያ ሕፃናት 90 በመቶው ዙሪያ መለስ ደሃ በሚባል ደረጃ ውስጥ ናቸው።
በሪፖርቱ ይፋ ማድረጊያ ሥነ ስርዓት ወቅት እንደተገለጸው የከፋ ዙሪያ መለስ ድኅነትን ለማስወገድ በማኅበራዊ ዘርፍ በተለይ በሕፃናት ላይ ትኩረት ማድረግ – ከድኅነቱ ለመውጣት ብቸኛ አማራጭ ነው።

የኢትዮጵያን የድኅነት ሁኔታ ለማሻሻል የመንግሥት በጀትና የለጋሽ ድርጅቶች ርብርብ (ይሄ ራሱን የቻለ ውስብስብ ፖለቲካና አሠራር እንዳለው መንገር ለቀባሪው አረዱት ስለሚሆን ይቅር) በቂ እንዳልሆነ እስከዛሬ የመጣንበት መንገድ ያሳያል። በተለይ የተጠቀሰውን ዓይነት ጥናቶች ቁልጭ አድርገው እንደሚያሳዩት ሕፃናት ከዚህ የከፋ ድኅነት ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ አማራጭ የሌለው አጣዳፊ ተግባር ሊሆን ይገባል።

በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚታወቀው መንግሥትም ይሁን ሕዝብ በአገራችን በማኅበራዊ ፍትሕ ላይ መሥራት ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ አይታይም። በተለይ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ትኩረት የሚያሻቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት፣ መፈናቀልና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የሁሉንም ወገን ቀልብ ስቦ ቆይቷል።
አሁን አዲስ አበባ መስተዳደር በትምህርት ዘርፍ እንደጀመረው ማኅበራዊ ፍትሕን የማስፈን ሥራ ግን በሁሉም መስክ ሊካሔድ የሚገባው ነው።

ማኅበራዊ ፍትሕ ቃሉ ሲተረጎም “በማኅበረሰቡ ውስጥ ዕድሎችን፣ ሀብትንና የተመቻቸ ሁኔታን የሚመለከት ፍትሕ” ማለት ነው። ማኅበራዊ ፍትሕ ከሰብኣዊ መብት መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ ሲሆን የማኅበራዊ ፍትሕ ምሰሶዎች ተደራሽነት (ለመሠረታዊ አቅርቦቶችና አገልግሎቶች እኩል ተጠቃሚነት) ማመጣጠን (ለኢኮኖሚያዊ ሀብትና ተጠቃሚነት ፍትሐዊ ያልሆነ ድልድልን ማስቀረት) እና መብቶች (ውጤታማና የተቀላጠፈ የፍሕት፣ የኢንዱስትሪና ፖለቲካ መብቶች) የሚባሉት ናቸው።

ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ የሚቻለውም ማኅበረሰቡ እኩል ተጠቃሚ መሆኑንና በማኅበረ-ኢኮኖሚው የሚፈጠር አድልዎ አለመኖሩን የሚያረጋግጡ ተቋማትና አገልግሎቶችን በማስፈን ነው።

የማኅበራዊ ፍትሕ የማስፈን ጉዳይ የሚከሰተውም በዓለም ዐቀፍ በአገር ዐቀፍ በክልሎችና በአካባቢዎች መካከል ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ሲኖር፣ በሰዎች መካከል አድልዎ የማድረግና የማበላለጥ ሁኔታም ሲፈጠር ነው።

ማኅበራዊ ፍትሕ የሚያሻቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ጉዳችም እንደምሳሌ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የትምህርት ዕድል መመቻቸት፣ የልጆች ብዝበዛና ክብካቤ ማጣት (ችላ መባል)፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ የተዛባ የጤና ሁኔታ፣ እኩልነት መታጣት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ሁኔታ መታጣትና ድኅነት ይጠቀሳሉ።

ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን ወይም አድልዎና ያልተመጣጠነ የሀብት፣ የዕድልና የተጠቃሚነት ሁኔታን ለማስቀረት ይህ አለመሆኑ የሚረጋገጥበትና ሆኖም ሲገኝ የማስተካከያ እርማት የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት የተጠያቂነት ሁኔታ እንዲኖር ሊጠይቁ፣ መንግሥት ይህንን የሚሠሩ ፖሊሲዎችና መዋቅር ብሎም ተቋማት መኖራቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

ከላይ የተጠቀሰውንና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እያከናወኑት ያለውን ተግባር እንደ አንድ ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈኛ መንገድ ብናየው የምገባውና የደንብ ልብሱ ጉዳይ በእሳቸው ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በፖሊሲ ሊመራ የግድ ይላል(የምገባው ተግባር ባለፈው ዓመትም የተከናወነ በመሆኑ ምናልባት የሚመራበት ሰነድ ሊኖረው እንደሚቻል ሲገመት የደንብ ልብስና የደብተሩ ጉዳይ የሚመራበት አሠራር እንዲኖረው ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል)።

በተረፈ መንግሥት ሁሉንም ተግባር ለማከናወን የሚያስችል አቅም ሊኖረው ስለማይችልና ይህን በጎ ተግባር የመሰለ ሌላም በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያለውን ማኅበረሰብ ለማቋቋም እንዲቻልና አገሪቱ ግማሽ የሚሆነውን ወጣት የሥራ ኀይል የሥራ ዕድል ማግኘቱን ለማረጋገጥ፣ የበጎ አድራጎት ሥራን የሚመራ ተቋም አቋቁሞ ከማኅበረሰቡ ገንዘብ የሚሰበስበትን በቋሚነትም በኢንቨስትመንትና ካፒታል ማሳደግ ሥራ ላይ ተሰማርቶ በዘላቂነት እነኝህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደግፍበትን መንገድ የግድ ይላል። ይኸው ተግባርም በተማሪዎች ምገባና ትምህርት መርጃ ስብሰባ ላይ ሳይወሰን በሌሎችም ላይ ውሎ የተሻለ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል አነስተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ ለሌሎች እንዲያዋጣ ለምሳሌ ለወጣቶች ሥራ መፍጠር የሚችሉ የአካባቢ ጥበቃና ከትራፊክ እስቅስቃሴ ጋር የተገናኙ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ከዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ላይ የተወሰነ ክፍያ በመጨመር በቋሚነት የሚቀጠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል። ከዚህ ሌላ የሚቋቋመው ተቋም በንግድ ሥራ የተሰማሩና ከፍተኛ ትርፍ የሚያስመዘግቡ ተቋማት ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያበረታታና የእነሱንም መዋጮ ለተጠቀሱትና ለሌሎች ማኅበራዊ ፍትሕን የማስፈን ተግባራት ሊያውል ይችላል።

በግሌ ባለኝ ግምገማና በኢንጅነር ታከለ ዑማ ለተጀመረው በጎ ተግባር ከተሰጠው ምላሽ እንደተረዳሁት ጠንካራና ተጠያቂነት ያለው፣ ሥራውንም ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ የሚያከናውን ተቋም ቢኖር ማኅበረሰቡ ለመደገፍና ወገኖቹን ለማቋቋም አስተዋጽዖ ከማበርከት ወደ ኋላ አይልም። እንደ መቄዶንያ ያሉ የማኅበረሰቡ ሙሉ ድጋፍ ያቆማቸው ተቋማት ልምድ የሚያሳየንም ይህንኑ ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here