የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ5 መቶ ሚሊዮን ዶላር ቀነሰ

በኢትዮጵያ እየተገባደደ ባለው ዓመት በዐሥር ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ የተቻለ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱ ታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በበጀት ዓመቱ ከመስከረም 2011 ጀምሮ ባሉት ዐሥር ወራት ውስጥ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ታላላቅ ኩባንያዎች ለመሥራት ፍላጎት በማሳየታቸው እና መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰው ኩባንያዎች በአገር ውስጥ የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ጠቁሟል። ይሁን እንጂ በባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማሽቆልቆሉንም አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

በዐሥር ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለማድረግ ፍላጎታቸውን ካሳዮ 24 የአውሮፓና እና እስያ አገራት በቀጣዩ ዓመት በእርግጠኝነት ወደ ሥራ እንደሚገቡ የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መኮንን ኀይሉ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። አያይዘውም ግንባር ቀደም ከሆኑት ዓለም ዐቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከልም የጀርመኑ ግዙፍ የአውቶሞቢል አምራች ኩባንያ ቮልስ ዋገን እና በተለያዩ የመሰረት ልማት ዝርጋታ ዘርፎች የተሰማራው ሲመንስ ኩባንያም እንደሚገባ ማረጋገጫ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከአውሮፓዊ ኩባንያዎችም በተጨማሪ የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገራትም ፍላጎታቸው መታየቱን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መረጃ አመላክቷል።
በኤልክትሮኒክስ አምራችነቱ የሚታወቀው የጃፓኑ ግዙፍ ኩባንያ “ኤንኢሲ” በቀጣዩ አመት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎችን እያገባደደ እንደሆነ አዲስ ማለዳ መረጃዎች ያመላክታሉ። ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፍላጎት ካሳዩ የውጭ አገር ኩባንያዎችው ውስጥ ኹሉም ሊባሉ በሚያስችል ደረጃ በአምራች ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ታውቋል። በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጅት ላይ የሚገኙት ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና የልማት ድርጅት በ2010 እና 2011 በጀት ዓመት ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ከተመዘገቡት የውጭ ቀጥተኛ አንቨስትመንት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው የተመዘገበው በኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ ይፋ ማድረጉን ገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ በአፍሪካ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ በመሰለፍ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ለማወቅ ተችሏል። ከቀዳሚ አገሮችም አንጻር ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮንጎ እና ሞሮኮ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይይዛሉ።

በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው ምሥራቃዊው የአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በፍጥነት ዕድገት እያሳየ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መመዝገቡንም አስታውቋል። ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የቀጠናውን 40 በመቶ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ትሸፍናለች ቢልም ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ18 በመቶ ቀንሷል ሲል ይፋ አድርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here