አምስት የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ሊያድጉ ነው

0
809

በመላው ኢትዮጵያ ካሉ 38 አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ውስጥ አንጋፋዎቹ አዲስ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደደቢትና ኦሞ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ይሸጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ከቅርብ ዓመታት እነዚህ አንጋፋ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሸለ እየሆነ ቢመጣም ያላቸውን ትልቅ አቅም ግን በትልልቅና የተሸለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ማፍሰስ ባለመቻለቻው የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ ለመፍቀድ መታሰቡን ባንኩ አስታውቋል።

ባንኩ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ወደ ባንክ ለማሳደግ የሚያስችለውን ጥናት እና የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑን ገለፆ ሥራውን አጠናቆ መስፈርቱን ለሚያሟሉት ተቋማት ፍቃድ መስጠት የሚጀምርበትን ቀነ ገደብ ግን አላስቀመጠም።

የሚዘጋጀው የሕግ ማዕቀፍም መስፈቱን እና ሒደቶችን የሚወስኑ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ትልቁ የባንኩ ሥጋት ግን የአነስተኛ የብድር እና ተቋማቱ ወደ ባንክ ሲሸጋገሩ በእነሱ ቦታ የአገልግሎት ክፍተት (mission drift) እንዳይፈጠር እንዴት እናድርግ የሚለው መሆኑን አስታውቋል።

የባንኩ የማይክሮ ፋይናንስ ሱፐርቫይዘሪ ባልደረባ ፍሬዘር አያሌው እንዳሉት ተቋማቱ ወደ ባንክ ሲያድጉ የክልል መንግሥታት በተቋማቱ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በባንኮች ውስጥ የማይቀጥል ሲሆን መንግሥት ለተቋማቱ የሚደርጋቸው የቢሮ፣ የብድርና ሌሎች ድጋፍ አቅርቦቶችም ይቀራሉ።

በባንኩ ሕግ መሰረት ማንኛውም ባንክ አክስዮን ማኅበር ሆኖ መቋቋም ያለበት ሲሆን ማንም ሰው ከ5 በመቶ በላይ የአክስዮን ባለቤት ሊሆን አይችልም።
አነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማቱ 5 ሚሊዮን የብድር ደንበኞች ያሏቸው ሲሆን የቁጠባ ደንበኞቻቸው ግን ከተበዳሪዎቻቸው ጋር የማይመጣጠኑ ናቸው ተበሏል። ተቋማቱ ያበደሩት ጠቅላላ ገንዘብ በ32 በመቶ እያደገ 51.7 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን ካፒታላቸው ግን 15.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ሆኖ ተቀማጭ 38.4 ቢሊየን ብር እና ጠቅላላ ሀብታቸው ደግሞ 76.6 ቢሊዮን ደርሷል። የባንኩ መረጃ እንደሚሳየው ንግድ ባንክን ጨምሮ ያሉት 17 ባንኮች ያላቸው የቁጠባ ሒሳብ ደንበኛ ግን 50 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የብድር ደንበኞቻቸው ግን 215 ሺሕ ብቻ ናቸው።

አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የሚቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገለግሉ ሲሆን ባንኩ እንደክፍተት ከለያቸው ነገሮች መካከልም የቡድን ትውውቅን እንደ ብድር ማስያዣ መጠቀም አንዱ ነው።

በሌላ በኩል የባንኮች ጠቅላላ ሀብት 1 ነጥብ 1 ትሪልዮን ብር የደረሰ ሲሆን ካፒታላቸውም 90 ቢሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስቃውቋል። በአሁኑ ሰዓትም 5 አዳዲስ ባንኮች የወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የጠየቁ ሲሆን በባንክ ዘርፉ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔም መጠነኛ ዕድገት አሳይቶ 3.66 በመቶ መድረሱን ባንኩ አስታውቋል።

አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡት ብድር ዕድገት ከፍተኛ ሲሆን የመመለስ መጠኑ ግን እያነሰ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑንም ባንኩ አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here