በአማራ ክልል ሕገ ወጥ መድኀኒቶችን ሲሸጡ የተገኙ 20 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

0
609

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የሸቀጥ መደብሮች በስፋት እየተሸጡ የሚገኙትን ሕጋዊነታቸው ያልተረጋገጠ የጸረ ተባይ መድኀኒቶችን እና የውበት መጠበቂያ ምርቶች ለመቆጣጠር በተጀመረው ዘመቻ 20 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ዘመቻው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮም በአንድ ሳምንት ውስጥ 80 ሊትር በላይ የተለያዩ ኬሚካሎች እና ኬሚካልና 13 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክልሉ አስታውቋል።

የጸረ ተባይ ኬሚካል አዋጅ ቁጥር 674/2002፣ በየትኛውም አግባብ ያልተመዘገበ ኬሚካል አይተዋወቅም፣ አይሸጥም የሚለውን ሕግ የጣሰ ማንኛውም ሰው ኬሚካሎቹን ሲያዘዋውርና ሲሸጥ ከተገኘ ከሦስት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

የክልሉ የግብርና ቢሮ ሥር የተዋቀረው የዕፅዋት፣ ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው በተለይም የገላ ሳሙና፣ የጸጉር ቅባት፣ ከሰል ማቀጣጠያ፣ የአይጥ መርዝ፣ የበረሮ እና የተለያዩ ነፍሳት ማጥፊያ መድኀኒቶች በስፋት በክልሉ በሕገ ወጥ መንገድ እየተሸጡ ይገኛሉ።

“ጥራቱ የተረጋገጠ፣ ጉዳት የሌለው” የሚለው ማስተዋወቂያም ማረጋገጫ የሌለው እና ሐሰተኛ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ማንኛውም ኬሚካል በባሕሪው መርዝ እንደሆነ እና በየጎዳናዉ የሚስተዋሉትም መድኀኒቶች ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የባለሥጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበባው ይመር ተናግረዋል።

ለሥራ በሚዘዋወሩባቸው አካባቢዎች አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድርጊቱ እንዲቆም እየጠየቋቸው እንደሆነ የገለጹት አበባው፣ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ የመቆጣጠሪያ መንገዶች ቁጥጥር እያደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል። በየወረዳው የሚገኙ አመራሮችም ኀላፊነት ተሰጥቷቸው ክትትል እንዲያደርጉ ቢደረግም ትኩረት መስጠት አለመፈለጋቸውን አስታውቀዋል።

ማንኛውም ዓይነት ኬሚካል ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ወይም ሲመረት ጥራቱ እና ደኅንነቱ በሚገባው አካል ታይቶ መሆን እንዳለበት ሕጉ ቢደነግግም እነዚህ አካለት ያለ ምንም ፈቃድ የኅብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ እርምጃ መወሰዱም ታውቋል።

ሻጮቹ የሚይዙት መድኀኒት ሕጋዊ ቢሆን እንኳን የሚሸጡት አካላት ባለሙያ መሆን እንዳለባቸው ተናግረው፣ ሕገ ወጥ ፀረ ተባይ እና መድኃኒት ሻጮችን ለማስቆም ሕጋዊ መድኀኒት ሻጮችን በማደራጀት እየተሠራ እንደሆነ አበበ ተናግረዋል። ሕጋዊ ሆነው ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችንም እየተቆጣጠሩ በሕግ አግባብ እየቀጡ እንደሆነም ገልጸዋል።

አዋጁ ላይ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ማንኛውም ሰው በኬሚካል ጉዳይ ይመለከተዋል፤ ያሉት አበባው፣ ማኅበረሰቡ በየመንገዱ የሚሸጡ ጸረ ተባይ መድኀኒቶችን ባለመግዛት እና በማጋላጥ ለሕግ ለማቅረብ በሚደርገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። በአማራ ክልል 498 ሕጋዊ የኬሚካል ሻጭ ነጋዴዎች እንዳሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here