የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ በውርስ እንዲተላለፍ የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

0
711

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ኤጀንሲ እና በአንድ ነዋሪ መካከል በተነሳው የፍትሐ ብሔር ክርክር መነሾ ለሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የቀረበው ጉዳይ ላይ የግለሰቡን ክርክር በመደገፍ ጉበኤው የውሳኔ ሐሰብ ሰጠ። የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ዕድሜአቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ወራሾች አይተላለፍም በሚለው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያ ላይ የሕገ መንግሥታዊ ትረጉም የሰጠው ጉባኤው መመሪየው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 እና ከሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ ነው በሚል የውሳኔ ሐሳቡ ይጸድቅ ዘንድ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩንም አስታውቋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ባካሔደው ስብሰባ ውሳኔውን ያሳወቀው ጉባኤው በ2008 ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው “የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ የወጣ መመሪያ ቁጥር 1/2008” አንቀፅ 44 (ሐ እና ሠ) ሕገ መንግሥቱን እንደሚጣረስ ባደረገው ማጣራት መሰረት ማረጋገጡንም ገልጿል።

“የጉዳዩን ክብደት በመረዳትም ከከተማው አስተዳደር ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ኀላፊና ባለሞያ አስቀርቦ በጉዳዩ እና በድንጋጌዎቹ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ተቀብሏል” ሲል ከጉበኤው ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል። “የቤት ዕድለኛ በሞተ ጊዜ ዕድሜያቸው 18 ዓመት የሞላቸው የሟች ልጆችበሟች ሥም የወጣውን እጣ አይወርሱም በሚል የደነገገው የመመሪያው አንቀጽ በወራሾች መካከል ልዩነት በመፍጠር ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በውርስ መልክ የሚያገኙትን የቤት ባለቤትነት መብት የሚሸራርፍ ነው” ሲል ጉባኤው አብራርቷል።

ሕገ መንግሥቱ ስለዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚደነግግበት ምዕራፉ ሦስት አንቀጽ 40 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ ይከበርለታል ሲል ያስቀምጣል። ቀጥሎም ይህ መብት የሕዝብን መብት ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የሚያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም ሌሎች ዜጎችን መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችንም ጭምር እንደሚያካትት ያስቀምጣል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመ እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ከተረጎመ በኋላ ሞያዊ አስተያየቱን እና የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ ሲሆን ምክር ቤቱም ጉባኤው ባቀረባቸው ሐሳቦች ላይ በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል።

ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው በሚለው መርህ ላይም ተመስርቶ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ ከሆነ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የሚጸኑ እንደሆነ ተደንግጓል።

ዐሥራ አንድ አባላት ያሉት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሰብሳቢነት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዘዳንት፣ ስድስት የሕግ ባለሞያዎች እና ሦስት የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አባላት ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here