የፖለቲካ ስርዓታችንን እንዴት ይቀየር?

0
641

የፖለቲካ ስርዓታችን ከባሕላችን የተቀዳ ነው የሚሉት መላኩ አዳል፥ የፖለቲካ ባሕላችንን ለማስተካከል ደግሞ ጥቂት ባለእውቀቶች በጋራ ርዕዮታችን ላይ ለመሥራት ፈቃደኝነታቸው ማሳየት አለባቸው ይላሉ። ይህም ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ፣ አካታችና አቃፊ መንግሥት እንዲኖር ወሳኝ ሚና ይጫወታል በሚል የመከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

 

ከምወዳቸው ነገሮች ውስጥ ዋናዎቹ ማሰላሰል፣ ማንበብና ከመሰሎቼ ጋር መወያየት ናቸው። እናም ከጓደኞቼ ጋር ስንወያይ የአገራችን ችግር የእውቀት ማነስና የጋራ ርዕዮት አለመኖር ነው አልኩ። አንዱ ምርጥ ጓደኛ ሐሳቤን በመደገፍ “እናት የሚወዱት ልጃቸው ሚስት ለማግባት መስለብ ነበረበትና ይህን ሲያደርግ ሰውየው ይሞትበታል። እናም ፍርድ ቤት ቀርቦ ተውንጅሎ ሞት ይፈረድበታል። እናትም የይግባኝ ማመልከቻቸውን ለሚመለከተው አካል ያቀርባሉ። የማመልከቻው ይዘት ስህተቱ የልጄ ሳይሆን የማኅበረሰቡ ባሕል ነው። መንግሥትም ይህን ለመቀየር ምንም አልሠራም። ስለዚሀ በማኅበረሰብ ስህተትና መንግሥትም ግዳጁን ባለመወጣቱ ምክንያት በመጣ ችግር የምወደው ልጄ በሞት ሊቀጣ አይገባም” የሚል ነበር። ለእናንተ ይህ ጥያቄ ቢቀርብና ውሳኔው የእናንተ ቢሆን ውሳኔያችሁ ምን ይሆናል? የዳኛውም ወሳኔ “ልጅዎትን ይዘው ይሒዱ” የሚል ነበር።

ሌላው ያነሳነው ጥያቄ፣ የአገራችን ችግሮች መንስኤ ምንድን ነው የሚል ነው። እንደነሱ ችግሩ ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ባለማድረጉ ነው። እኔም ይህ ሐሳብ ስህተትነት አለበት የሚል ሐሳብ በምሳሌ አስደግፌ አቀረብኩ። በመጀመሪያ ሕዝብ ስርዓት እስካልተዘረጋለት ድረስ ተጠያቂነት የለበትም። በየትኛው ሕግና ስርዓት ሊጠየቅና ሊዳኝ? አንድ መምህር የወደቁ ተማሪዎችን አሳልፍ ያለበለዚያ ትባረራለህ ቢባል ምን ያድርግ አልኩ? ይባረር እንጂ ማሳለፍ የለበትም አሉ። የመምህራን ማኅበረሰብን ወጥ ማድረግ ስለማይቻል፣ በዚህ መንገድ ራስን ከመጉዳት የዘለለ ለውጥ አያመጣም አልኩ። ችግሩ ከስርዓቱ እንጂ ከግለስቦች ላይሆን ይችላልና።

ይታያችኋል በቦይ የሚፈሰው ጎርፍ? ቦዩ ጥሩ የተሠራ ከሆነ ውሃው የሚፈሰው፣ መንገድ ሳያበላሽ በታለመለት መንገድ ነው። ውሃው አይበተንም፣ ኅብረቱ እጅግ ደስ ይላል። የኅብረቱ መገለጫ ደግሞ በውሃ ቅንጣቶች መካከል የሚፈጠረው አያያዥ ኀይል (ሃይድሮጅን ቦንድ) ነው። ይህም ማለት፣ የቦዩ ጥሩ መሆኑ ኅብረቱን አጠንክሮታል ነው። መዳረሻውም የመቀበል አቅም ያለው ገንዳ መሆን አለበት። ያለዚያ በኋላም መበተኑ አይቀርም። የአገርም ጉዳይ ይኽው ነው። ያለአድሎ የተቀየሰ ስርዓት በሕዝብና በመንግሥት፣ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ሥጋትን በመቀነስና ዋስትናን በመጨመር የአገር አንድነትንና ህልውና ብሎም ዕድገት ያፋጥናል። ነገር ግን ታማኝነት የሌለው መንግሥት፣ የሚታመን ስርዓት ሊገነባ ስለማይችል፣ በሕዝብና በመንግሥት፣ እንዲሁም በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነትንም ስለሚበጣጠስ ሕዝብን ወጥ በሆነ መንገድ መምራት አይችልም። በሕዝብ ዘንድ ሥጋት ጨምሮ፣ ዋስትና ይቀንሳልና። ይህም ለሰላም መጥፋት፣ ለአንድነትና ለአገር ህልውና ተግዳሮት ይሆናል። የአገራችን ችግርም ይኸው ነው። የመንግሥት አለመታመንና የሕዝብን ግንኙነትም በብሔር ፖለቲካ መበጣጠሱና መተማመን መጥፋቱ።

እና ምን ለማለት ነው፣ ዋናው ችግራችን ዘረኝነትን የመንግሥት መዋቅራችንና የአስተዳደር ስርዓታችን ማድረጋችን ነው። ይህም የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የክልል መንግሥታትና የፌዴራል መንግሥትን ግንኙነት ያለአድሎ የማስተካከል፣ ስርዓት በያዘ መልኩ ያልተከናወነው የአገራዊ መግባባት፣ የተጠያቂነት እና የእርቅ ጉዳይ አለመከናወን እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ትቶ ለዘሩ ብቻ የሚሠራ ተረኛና ዘረኛ እንዲሆን አድርጎታል። የምናየው የባለሥልጣናትና የጦር መኮንኖች ግድያም በመንግሥት ደረጃ ያለው ዘረኝነት መገለጫ ነው። በየክልሎቹ እየፈነዳ እያጠፋን ያለው፣ ላለፉት 50 ዓመታት የቀበርነው የጥላቻ፣ የበቀልና የዘረኝነት ፖለቲካ ነው። ወንጀለኞቹ ይሔን የርዕዮት ቦንብ ሰው አንጎል ላይ የቀበሩ ዘረኛ የፖለቲካ ልኺቃን እንጂ ሕዝቡ አይደለም። በደካማ አስተሳሰብ እንዲበላሽ ያደረጉትን ዜጋ ብቻ ተጠያቂ ማድረግ በቂ አይደለም። የችግሩ ጠንሳሽ መሪዎችና ታዋቂ ሰዎችስ መቼ ነው የሚጠየቁት? የችግሩን ዋና መንስኤ ማስተካከል እንጂ፣ እሳቱ ከተነሳ በኋላ የማጥፋት ሥራ ውጤትን አጉልቶ ማሳየት አንጂ መፍትሔ አይሆንም።

ጥያቄያችን መሆን ያለበት፣ አገራችንን ስምምነት መሰረት ባደረገ አዲስ ፖለቲካ ላይ እንዴት ትቁም ነው። የባህል አንድነት በስርዓት ከተመራ ለአገር አንድነትና ህልውና ብሎም ዕድገት መሰረት የሚሆነው የጋራ እሴቶቻችንን ማጠንከር የሚችል በመሆኑ ነው። የባሕል አንድነት እንዲኖረን የጋራ ስምምነትንና ጥሩ እሴቶችን በማያሳጣን መንገድ መሥራት ይኖርብናል። አንዱ የባህል አንድነት መገለጫ ሕገ መንግሥታዊ የሕግ ከለላን፣ መድብለ ፓርቲን፣ ምርጫንና የፕሬስ ነጻነትን የሚያጠቃልለውን የዲሞክራሲን ባሕል ማዳበር ነው።

የብሔር ፖለቲካ ልዩነትን መሰረት ያደረገ የማንነት ፖለቲካ ነው። በቁጥር ብዙም ሆንን ትንሽ፣ የዚህ ፖለቲካ ዓላማ ልዩነትን መሰረት አድርገህ የሌሎችን አንድነት በማዳከም ለራስህ ቡድን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መፍጠር ነው። የዘውግ ፖለቲካና ፌዴሬሽን የብዝኀነት መጠበቂያ መንገድ ተብሎ ቢሰበክም፣ ብዙዎችን ከመሬት ባለቤትነት በማፈናቀል፣ የፖለቲካ መብቶቻቸው በመከልከል የባሕል አንድነትና የብዝኀነት ማዳከሚያ መንገድ ሆኗል። የብሔር ፖለቲካ የሐሳብ መሰረት ልዩነትና የራስን ቡድን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚ ማድረግ ስለሆነ ሐሳብን መሰረት ባደረግ በርዕዮት መሰረት ለሚያድገው ዲሞክራሲ እንቅፋት ነው። በዚህ መንገድ ብሔራዊ ማንነትን መፍጠር ስለማይቻል፣ የአገር አንድነትንና ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል፤ በዘውግ መደራጀት ያመጣብንን ችግር በተግባር አይተናል።

የአገርን ሕዝብ ብዛት 34 በመቶ ስለሆንን ገዥዎች መሆን ያለብን እኛ ነን ማለት፣ ለአገር አንድነትና ህልውና ብሎም ለዴሞከራሲ እድገት እንቅፋት መሆን ነው። ይህ ጥያቄ የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትሕ ሳይሆን የበላይነት ጥያቄ ነው። ስለዚህ ትክክል አይደለም ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። የዘውጌ ፖለቲካ ማኅበራዊ ሀብት የሆኑትን መተማመንን፣ ማኅበራዊ ግንኙነትን፣ የጋራ እሴቶችን (ርዕዮት፣ ታሪክ፣ ጀግኖች ወዘተ) በመሸርሸር ለአገር አንድነት፣ ህልውናና ዕድገት ተግዳሮት እየሆነ ነው። ጥያቄው ሐሳብ/አመለካከት ሁሉ ተመሳሳይ ይሁን አይድለም። ጥያቄው ሁሉንም በእኩል ተጽዕኖ የሚያመጣ ከሆነ፣ አብዛኛውን ያማከለ የብዙኀኑ የጋራ ርዕዮት ይሁን ነው። በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ካልያዝን፣ የአገር አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። ለምሳሌ የአገራችን የፖለቲካ ችግር የጋራ ርዕዮት ካለመኖር ይመነጫል።

አሁን ደግሞ የቀረችውን የሕዝቦች የግንኙነት ድር ለመበጣጠስ፣ ከፌደሬሽን አልፈን ወደ ኮንፌደሬሽን የአስተዳደር ማደግ አለብን የሚል አስተያየት እየሰማን ነው። ይህ ሐሳብ እጅግ አደገኛና የአገርንም ህልውና ችግር ሊጥል የሚችል ነውና አሁኑኑ ሊቆም ይገባል። የቀረችው ዜጎችን ያያያዘው ድርና ማግ ተቆራርጦ ሳያልቅ።

ስለዚህ ዜጎችን ተጠያቂ ከማድረጋችን በፊት ስርዓትን ማስተካከልና ለዜጋው የሚቻለው ሥልጠና ያስፈልጋል። ያልዘሩትን መሰብሰብ አይቻልምና። ያለዚያ ግን ተጠያቂነትን ማስፈን አይቻልም። ይህንንም ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ባለእውቀት ጥቂቶች በቂ ናቸው። እናም ችግራችን ተማርን የተባልነው የያዝነው ርዕዮት የጋራ አለመሆኑ ነው። ለችግሩ ተጠያቂዎቹ ጥቂቶችና ሥልጣን የተቆናጠጡ እሩቅ የማያዩ የቅርብ አዳሪዎች ናቸው። የዚህ ሁሉ የአገራችን ትርምስምስ ምክንያቱም ይኸው የጋራ ርዕዮት መጥፋት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ችግር ለመፍታት ምን ምን ፖሊሲዎችና ሕጎች እያሻሻለና እያወጣ፣ ተቋማትን እየገነባ ነው? የአስተሳሰቡ አካታችነትስ ምን ያህል ነው? በጠቅላላው ያለጠንካራ፣ አካታችና አቃፊ መንግሥት ጠንካራ አገር አይገነባም እላለሁ።

በተጨማሪም መፍትሔው፣ የገዥ ተረኝነትን፤ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ በእኔ ቡድን አምሳል የሚል እምነትን፤ የተንሻፈፈ ትርክትን፤ ያለፉት 60/150 ዓመታት ለእኛ ሙሉ ለሙሉ ሽንፈት ነበር ብሎ ማመንን፤ ሊወራረድ የሚገባ ታሪካዊ ጠባሳ አለ ብሎ ማሰብን፤ የጋራ እሴቶቻችንን፣ ታሪካችንንና ጀግኖቻችንን ማጣጣልን ማቆምና በጋራ ርዕዮት፣ ለጋራ ርዕይ መሥራት፣ የሁሉም የሆነ መንግሥት እንዲኖረን ማድረግ ብቻ ነው። ለዚህም ወጥ የትምህርት ስርዓትና ጠንካራ የልማት ሥራዎች ያስፈልጋሉ። የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ መሆን ያለበት የአካባቢው ቋንቋና አማርኛ በየትኛውም ቦታ ጎን ለጎን የሚኖርበትን መንገድ መፈለግ አለብን። የሕዝብ አንድነትና ግንኙነት የሚጠነክረው የጋራ መግባባት ሲኖር ነውና። ይህ ደግሞ ያለ ጋራ ቋንቋ አይሆንም። በየትምህርት ቤቶችም የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ በተጓዳኝ ይሰጡ። የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀት ብሔራዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የብሔር ድርጅቶች ከፖለቲካ ተሳትፎ ታግደው ማህበራዊና ባህል ላይ እንዲሠሩ መደረግ ይኖርበታል። ይህም ብሔራዊ ማንነትና የዘውግ ማንነት ተጣጥመው እንዲሄዱና የአገርን አንድነትና ህልውና እንዲሁም ዕድገት ያስጠብቃል። ይህም ማለት የብሄር ፖለቲካ ከማኅበራዊ ማንነት የሚነጠልበት መንገድ መፈለግና ከአስተዳደራዊና ከትምህርት ስርዓት ውጭ ባለው ሁሉ እንዲሳተፉ ማድረግ ይኖርብናል።
መላኩ አዳል የባዮ ሜዲካል ሳይንስ የዶክትሬት ተማሪ ናቸው ። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here