የዐቢይ አካሔድ በወላይታ፡- “በመጀመሪያ ‘በዱርሳ’ ከዚያም ‘በእርሳስ’ ነው”

0
409

የወላይታ ሕዝብን የክልልነት ጥያቄ ለማፈን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሔዱበት አካሔድና የኋላ ኋላ የወሰዱት እርምጃዎች፥ ክልሎችን በኀይል ለመቆጣጠር፣ መዋቅራቸውን ለመበጣጠስና ህልውናቸውን ሽባ ለማድረግ ነው የተጠቀሙበት ሲሉ ግዛቸው አበበ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

 

ከአማርኛ ጭፈራዎች አንዱ እስክስታ እንደሚባለው የወላይታ ባሕላዊ ጭፈራ ዱርሳ ይባላል። በአንዳንድ የአማርኛ ዘፈኖች ቃል በቃል ‘እስክስ’ ወይም ‘እስክስታ’ ሲባል እንደሚሰማው በወላይታ ዘፈኖች ውስጥም ‘ዱርሳ’ የሚለው ቃል ሊሰማ ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው የደቡብ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን በኮማንድ ፖስት ሥር አስገብተውታል። የደቡብ ክልል በየትኛውም እርከን ላይ በተለይም የክልልነት ጥያቄዎች በሚነሳባቸው ወረዳዎችና ዞኖች የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ከፌደራል በተላከ ጸጥታ ኀይል እጅ ውስጥ ወድቀዋል ማለት ይቻላል። የእነዚህ አካባቢዎች ሕዝቦች በሰላም ጥያቄ በማቅረብ ላይ የነበሩትም ጭምር በኀይል ታፍነዋል። ከኢሕአዴግ ልምድ በመነሳት የእነዚህ ሕዝቦች ዕጣ በአንድ ግለሰብ ማለትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተወሰነ ነው ማለት ይቻላል። የሰላም ሚኒስቴር፣ የክልል አስተዳደርና ምክር ቤት፣ የዞን አስተዳደርና ምክር ቤት ወዘተ…. ከአንድ አካል ከምትመጣ ቀጭን ትዕዛዝ ውልፍት እንዳይሉ ተደርገው ተጨፍልቀዋል።

ነገሮች በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐምሌ 22 በችግኝ ተከላው ዘመቻ ሰበብ ወደ ወላይታና ጋሞ ያመሩት። በእነዚህ ዞኖች አንዲትም ችግር ሳትከሰትና ምንም ዓይነት ኀይልን የመጠቀም አዝማሚያ ሳይታይ ነው በአስቸኳይ ጊዜው አዋጁ አማካኝነት የጭፍለቃ እርምጃ የተወሰደባቸው። የእነዚህ አካባቢዎች አስተዳዳሪዎችና ባለሥልጣናት የሕዝብን ጥያቄ ስላልጨፈለቁና ሕዝብ አርፎ እንዲቀመጥ ጫና ባለማሳደራቸው እገዳ ተጥሎባቸዋል ወይም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የዞን፣ የወረዳና የክልል ባለሥልጣናት ሐዋሳ ላይ ተሰብሰበው እየመከሩ ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጓሮ ለጓሮ ዙረት ብቻ ሳይሆን የዞኖቹን መጸኢ ዕድል በሚመለከት ውይይት ተደረገ መባሉ በዚህ ክልል ያለው የአስተዳደር መዋቅር የይስሙላ ይሆን ዘንድ መደረጉንና የዚያ ክልል ሕዝቦች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለማስተናገድ የሚጫወቱት ሚና ከአሻንጉሊትነት የዘለለ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

በወላይታ ተደረገ በተባለው ስብሰባ ላይ ሊታፈን የሚፈለገውን የክልልነት ጥያቄን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አብሮነትን እየሰበኩ፣ አስቡበት ምከሩበት ሲሉ ተደምጠዋል። እነዚህ የደቡብ ክልል ሕዝቦች ኦሮሞው፣ አማራው ትግሬው ወዘተ… የየራሱን ክልል ስላገኘ ምን ጥቅም አገኘ? በምንስ ተጎዳ? ብለው አስበውና አንሰላስለው ለረዥም ጊዜ ሲጠይቁት የኖሩትን ጥያቄ በድጋሜ እያነሱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልብ ሊሉት አልፈቀዱም ወይም ያላወቁ መስለው እያደናቆሩ ሊያልፉት ይፈልጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሞ የራሱን ክልል በማግኘቱ የተጎዳው ነገር ካለና ከዚህ ዓይነት አከላለል ኦሮሞውን ነጸ ለማድረግ ትግል ጀምረው ከሆነ በግልጽ ይናገሩና የክልል ጥያቄ የሚባል ነገር ይገታ። ካልሆነ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር አጉል ብልጠት ከመሆን የዘለለ አይሆንምና ማንንም አያሳምንም፣ አያታልልምም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሆኑ የክልልነት ጥያቄዎችን የሚያጣጥሉና ለኢትዮጵያ ሕልውና አደገኛ እንደሆነ አስመስለው ከሚናገሩት ሌሎች ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና አክቲቪስቶች ብዙዎቹ የራሳቸውን ዘር ተኮር ክልል ያገኙ፣ የክልላቸውን ጥቅም ለማስፋት በሰፊው የሚሠሩና የሚያቅራሩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች መሰል የድፍጠጣ ዓላማዎችን የሚያራምዱ ግለሰቦች ሊክዱት የማይገባው ሃቅ ኢትዮጵያን የሚበትነውና አንድነትን የሚያዳክመው (1ኛ) አገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይኖራት መደረጓ (2ኛ) በብሔራዊ ቋንቋ ሥም አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዳይናገር መጠነ ሰፊ ዘመቻዎች መካሔዳቸውና (3ኛ) የክልሉን የሥራ ቋንቋ አትናገርም እየተባለ ክልልን የማጥራት ዘመቻ መካሔዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ኢሕአዴጋውያን በሚገባ እንደሚያውቁት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይኖራት የተደረገውና ቋንቋ አታውቅም እያሉ ክልልን የማጥራት (መጤ የተባለ ሕዝብን የማባረር) ዘመቻ በሰፊው የተካሔደው በሕወሐት መሪነትና በዋናነት በኦሕዴድ አቀንቃኝነት ሲሆን፣ ከ1984 ጀምሮ መጠነ ሰፊ ክልልን የማጥራት ዘመቻ የተካሔደውና ሕዝብ ከወለደበትና ከከበደበት አካባቢ በብዛት የተባረረው ከትግራይና ከኦሮሚያ ነው። የክልሎቹን ቋንቋዎች የሚችሉ ሰዎች የዘር ሐረጋቸው እየተቆጠረ ከመንግሥት ሥራዎች እየተፈናቀሉ ከቦታ ቦታ የተሳደዱት ከኦሮሚያና ከትግራይ መሆኑም ከምንም የተሰወረ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣናቸው የጫጉላ ሰሞን ሐዋሳ ተገኝተው ነበረ። በዚያን ጊዜ የሲዳምን ሕዝብ ወክለው በስብሰባው የተካፈሉ ሰዎች ጾታና ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃና ሐይማኖት ሳይለይ በአንድ ድምጽ የክልልነት ጥያቄያቸው በአስቸኳይ እንዲመለስ ሲጠይቁም ለወላይታዎች የሰጡትን መልስ ከተመሳሳይ ስብከት ጋር ነበረ ያቀረቡላቸው። ሲዳማዎች ጉዳዩን ቀድመው ያሰቡበትና የወሰኑበት ስለነበረ ጥያቄያቸውን በየደረጃው እያቀረቡ መልስ ሲጠብቁ ቆይተዋል። መጨረሻ ላይም የደም መፋሰስ፣ የሕዝቦች መፈናቀል፣ የንብረት መውደም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ጭፍለቃ በመላ ደቡብ ክልል ሰፍኖ እየታየ ነው። የተበሳጩ ወጣቶች ስሜታዊ እርምጃ እና ባለው ኀይል ያሻውን እንደሚደርግ የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትም የክልሉን ‘አማራጭ መፍትሔ’ ጥፋት አድርገውታል።

በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች ኹለት ዓይነት ሆነው ይታያሉ። በደቡብ ክልል ውስጥ የሚነሱ የክልልነት፣ የዞንነትና የወረዳነት ጥያቄዎችን በሙሉ ቀስ በቀስ ኢትዮጵያን የማፍረስ እንቅስቃሴዎች ናቸው ብለው የደመደሙ ምሁራንና ፖለቲከኞች የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ሲደግፉ ይደመጣሉ። በሌላ በኩል ግን የፌዴራሉ መንግሥት ደቡብ ክልልን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ክልሎች የመቆጣጠር ዓላማ እንዳለውና ሰበብ ባገኘ ቁጥር ይህንኑ ዓላማውን ለማሳካት እርምጃ እየወሰደ ነው ይላሉ። ገንዘብ በመመደብ እሳቱን የሚለኩሱ የራሱን ተላላኪዎች በማሰማራት ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ ነው በማለትም ይወነጅሉታል። ይህን መሰሉ ሒደት ክልሎችን በኀይል በመቆጣጠር፣ ክልላዊ መዋቅሮችን ወደ ማሽመድመድና የክልሎች ህልውና ያከተመ ያህል ሽባ የሚደርግ ስርዓት ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።

የኢሕአዴግ ስብሰባዎች ለጋዜጠኞች ክፍት ይሆናሉ፣ ‘አስረን ማስረጃ አናፈላልግም’፣ ሰው ተቃዋሚ ስለሆነ ብቻ አሸባሪ ተብሎ ሌላ ታርጋ ተለጥፎለት አይታሰርም፣ ወዘተ…ወዘተ…. እየተባለ የተገቡት ቃሎች በዓመታቸው እንደተሻሩት ሁሉ ሌሎች ዐበይት ጉዳዮችም ችግር አይገጥማቸውም ብሎ እርግጠኛ መሆን እንዴት ይቻላል?
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን የመጀመሪያ ቀናት በሐዋሳ በተደረገው ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲዳማን ሕዝብ አወድሰዋል ተሰብሳቢዎች አጨብጭበዋል አፏጭተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲዳማን መሬት ለምነት አድንቀዋል ተሰብሳቢዎች አጨብጭበዋል አፏጭተዋል። የሲዳምን ሕዝብ መርቀዋል፤ ተሰብሳቢዎችም አጨብጭበዋል፤ አፏጭተዋል። በ11/11/2011 ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው ሲዳማ ቀይ አሻራቻን በማሳረፍ ያጨበጨቡላቸውንና ያፏጩላቸውን ሁሉ አንገት አስደፍተዋል። በሐምሌ 22/2011 በወላይታ ስብሰባ ላይ ያጨበጨቡና ያፏጩ ሰዎችም ቀጣዩ ጉዳይ ዱርሳ መጨፈር ሳይሆን በወታደራዊ እርሳስ መጨፍጨፍ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አለባቸው። ልስላሴዎች ሁሉ ምቾት ላይሰጡ ይችላሉ፣ እባብ ሰለክላኬም ቆዳው ለስላሳ ነውና።
ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here