በመዲናዋ ከባድ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋውሩ የነበሩት ግለሰቦች ተከሰሱ

0
746

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት በሦስት መዝገቦች በሺዎች የሚቆጠሩ ጥይቶችን፣ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እና ሽጉጦችን በአዲስ አበባ ሲያዘዋውሩ በነበሩ ግለሰቦች ላይ ረቡዕ፣ ሐምሌ 24/2011 በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ መሰረተ።

በሰኔ 24/2011 ከለሊቱ 10 ሰዓት ላይ ኹለት ከባድ መትረየስ እና አራት ሺሕ የማካሮቭ ሽጉጥ ጥይት ሲያዘዋውሩ በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉ ኹለት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቷል። በእነ ገብረ እግዚአብሄር ወርቁ ላይ ክሱን የመሰረተው ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች የተከለከሉ ወይም ገደብ የተደረገባቸውን እቃዎችን ይዘው ተገኝተዋል በሚል በጉምሩክ አዋጁ መሰረት ክስ መስርቷል። አዲስ አበባ ሃብተ ጊዮርጊስ አካበቢ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ ለችሎቱ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ዐቃቤ ሕግም ይግባኝ በማለት ዋስትናው ታግዶ እንዲቆይለት አመልክቷል።

በተመሳሳይም እነ አወቀ አስረስ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ላይ የተመሰረተው ክስ ከ8 ሺሕ በላይ የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን፣ ኹለት ብሬይል፣ አንድ ማካሮቭ ሽጉጥ ሲያዘዋውሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ በሰኔ 18/2011 በቁጥጥር እንዳዋላቸው ያስረዳል። ተከሳሾቹ በ50 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲወጡ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ መፍቀዱን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በተመሳሳይ ይግባኝ ያለ ሲሆን ተከሳሾቹም በእስር ቆይተዋል።

እነ በድሉ ተስፋዬ የተባሉ ግለሰቦች ላይ በተመሰረተውም ክስ 16 ባለሰደፍ ክላሺንኮቭ፣ 11 ታጣፊ ክላሽ እንዲሁም ኹለት የክላሽ ጥይት በከተማው ውስጥ ሲዘዋውሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ይህም በኮንትሮባንድ ወንጀል እንዳስጠረጠራቸው ክሱ ይናገራል።

የተያዙት መሣሪያዎች የቱርክ፣ የሶሪያ እና የግብፅ ስሪት ሲሆኑ ከመንግሥት አካላት ውጪ በጦር መሣሪያ ንግድ ወይም ያለፈቃድ መሣሪያዎቹን ይዞ መገኘት መከልከሉን ተላልፈዋል በሚል ተጠርጥረዋል። በተፋጠነ የችሎት ሥነ ስርዓት ከተመሰረቱት ክሶች ባሻገር ሌሎች በርካታ መዝገቦች ላይ በዳይሬክቶሬቱ በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለውም በጊዜ ቀጠሮ ላይ ሌሎች መዝገቦች የሚገኙ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካበቢዎች የጦር መሣሪያዎች ዝውውር በሰፊው እየተካሔደ እንዳለ የተለያዩ ፀጥታ አካላት ሲገልፁ ቆይተዋል። ከዚህ ጋር በተያየዘም መንግሥት የተለያዩ የቁጥጥር እርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ እና ልል የሚበለውን የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አንቀፆች የሚያጠናክር አዲስ አዋጅ ማርቀቁም ይታወቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here