ሞዴስ እንደቅንጦት ዕቃ መታየቱ ይቁም!

0
1210

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ጀሚላ ከድር (ሥሟ የተቀየረ) ወራቤ ከተማ ተወልዳ በ12 ዓመቷ ለትምህርት በነበራት ጉጉት ከቤተሰቦችዋ ጠፍታ ወደ አዲስ አበባ መጣች። ጀሚላ ስትወለድ ማየት ትችል የነበረ ቢሆንም በ9 ዓመቷ ባጋጠማት ድንገተኛ ሕመም ምክንያት የዓይን ብርሃንዋን በድንገት አጣች። በዚህም ምክንያት ትምህርቷን ከኹለተኛ ክፍል ለማቋረጥ ተገዳ ነበር። የዛሬ ችግሯን የምትሻገረው በትምህርት መሆኑን አምና ነው ወደ አዲስ አበባ ያቀናችው። ግና ሕይወት እንዳሰበችው አልጋ በአልጋ አልሆነላት፤ ቢሆንም ትግሏን አላቋረጠችም።

ጀሚላ ትምህርት ቀጥላ አሁን የ7ኛ ክፍል ተማሪና የ21 ዓመት ወጣት ናት። ከትምህርት መልስም እንደ ማስቲካ፣ ሶፍትና መሰል ቀለል ያሉ ነገሮችን በመሸጥና ከኢትዮጵያ ማየት የተሳናቸው ማኅበር በየወሩ በምታገኘው 150 ብር የቤት ኪራይዋንና የወር ቀለብዋን ለመሸፈን ትጥራለች። “ምሳ ሰዓት የክፍል ጓደኞቼ ምሳ ሲበሉ ገለል ብዬ ዛፍ ጥላ ሥር አሳልፋለው” የምትለው ጀሚላ፥ ለረሃብ እጅ ሳትሰጥ ትምህርቷን ቀጥላለች። ነገር ግን ለረሃብ ያልተሸነፈችው ጀሚላ፥ ከተፈጥሮ ጋር መገዳደር ከብዷት የወር አበባዋ በመጣ ቁጥር ከትምህርት ገበታዋ ለመቅረት ትገደዳለች። “የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ የመግዛት አቅም ስለሌለኝ በቤት ውስጥ ያገኘሁትን ጨርቅ የምጠቀም ቢሆንም ፈሳሽን ለረጅም ጊዜ ይዞ መቆየት ስለማይችል የወር አበባዬ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሴን አበላሽቶብኝ ጓደኞቼ ሲነግሩኝ በተደጋጋሚ ተሳቅቂያለሁ። በመሆኑም መሰል አጋጣሚዎች እንዳይፈጠሩ በየወሩ የወር አበባዬ በመጣ ቁጥር ከምወደው ትምህርቴ ለመቅረት እገደዳለው” በማለት ትገልጻለች። ይህን መሰል ታሪክ ያላቸውና የወር አበባቸው በመጣ ቁጥር ከትምህርት ቤት የሚቀሩ እህቶች ቁጥር ቀላል አይደለም።

በኢትዮጵያ በግልጽ የመወያየት ባሕላችን ገና ያልዳበረ በመሆኑ በቤት ውሰጥ ከሚገኙ ነገሮች ሞዴስን አዘጋጅቶ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለመጠየቅ ብዙ እህቶች ያፍራሉ። የሃፍረቱ መነሻ ደግሞ የወር አበባን እንደ ነውር የሚቆጥረው ጎጂ ልማዳችን ነው። ሌላው ተግዳሮት ደግሞ 80 ከመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚኖርበት የገጠሩ ክፍል ውሃ እንደልብ ማግኘት አለመቻል ቶሎ ቶሎ መቀየርና ማጠብ የሚያስፈልገውን ከአንሶላ፣ ከጋቢ፣ ከነጠላና መሰል ለስላሳ ጨርቆች ሞዴስን አዘጋጅቶ በመጠቀም ትምህርት ቤት ውሎ መመለስ አዳጋች መሆኑ ነው። የውሃ አቅርቦት እንደልብ በሚገኝባቸው ቦታዎቸ እንኳን አጥበን በተደጋጋሚ ልንጠቅምባቸው የምንችላቸውን ሞዴሶች በቅርበት ከሚገኙ ቁሳቁሶች አዘጋጅተን ለመጠቀም ሥልጠና ቢሰጥ ጊዜያዊ መፍትሔ ይሆናል።

ዘለቂታዊ መፍትሔ የሚሆነው ግን ሞዴስ ላይ የተጣለውን ግብር በመቀነስ ሁሉም ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ነው። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሞዴሶች ላይ እንደ ቅንጦት ዕቃ ከ67 እስከ 123 በመቶ ግብር ሰለሚጣልባቸው እንጂ ከምርት ወጪው ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ከጀግኒት የሴቶች ንቅናቄ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ትኩረት ሰጥቶ እየተሻሻለ ባለው የታክስ ሕግ ላይ ሞዴስን እንደቅንጦት ዕቃ የሚያየውን ሕግ በማሻሻል ሁሉም ሴቶች ገዝተው ሊጠቀሙ እንዲችሉ እንዲያደርግ እንደሴትም ሆነ ጉዳዩ ይመለከተኛል እንደምትል አንዲት ዜጋ ጥሪዬን አቀርባለው።

ኪያ አሊ
በkiyaali18@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here