የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ማሻሻያ ውዝግብ አስነሳ

0
640

በማሻሻያው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ቅሬታ እንደተሰማው ገለጸ ረቂቅ ሕጉ ከነአጨቃጫቂነቱ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመርቷል

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ ማሻሻያ ላይ እንዳልሳተፍ ተደርጌያለሁ ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ መንግሥትን ወቀሰ። መንግሥት ግን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያው መደረግ ያለበት በገለልተኝነት በተቋቋመው የፍትህና የሕግ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት መሆኑን ጠቅሷል። ኤጀንሲው አስተያያቱን እንዲሰጥ ተደርጓል ያለው አማካሪ ምክር ቤቱ በበኩሉ በማሻሻያ ሂደቱ በአባልነት ተካትቼ መስራት አለብኝ የሚለው አቋሙ ተገቢ አይደለም ብሏል።
መንግሥት በጀመረው የፍትህና ሕግ ማሻሻያ ሥራዎች ቀዳሚ ትኩረት ካገኙት መካካል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001 እና ሌሎችም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ ያወጣቸውን መመሪያዎች ይገኙበታል።
በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 21 ማንኛውም ሰው ለየትኛውም ሕጋዊ አላማ የመደራጀት መብት እንዳለው መመልከቱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ከመደራጀት ጉዳይ ጋር የሚያያዙና የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ስላሉ ሕጋዊ መብቶችን በተሟላ መልኩ ማረጋገጥ እንዲቻልና ከአገሪቱ የፖለቲካ እድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም በሥራ ላይ ያለውን ሕግ ማሻሻል እንዳስፈለገም ተነግሯል።
በዚህም ከመንግስት ገለልተኛ ያለምንም ክፍያ በፍትህ ማሻሻያ ስርዓቱ ውስጥ ለመሳተፍ የተቋቋመው የፍትህና የሕግ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት በሥሩ ባደራጃቸው የሥራ ቡድኖች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራትን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎችን ሲመረምር ቆይቷል።
ምክር ቤቱ ቢሻሻሉ ያላቸውን የሕግ ጉዳዮችም ለሕዝባዊ ውይይት አቅርቦ የመጨረሻ ረቂቅ አዋጅን “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ” በሚል ርዕስ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረከቡ ይታወሳል።
ይሁንና በማሻሻያ ሂደቱ መንግሥት እንዳልሳተፍ አድርጎኛል የሚለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ ቅሬታ እንደተሰማው በተለይ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር መስፍን ታደሰ ኤጀንሲው ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የቁጥጥር ሥራን የሚሰራና በአጥፊዎች ላይም እርምጃ የሚወስድ ሆኖ ሳለ ከማሻሻያ ሂደቱ “እንድንገለል ተደርገናል’’ ይላሉ። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ “የአሁኑን ሕግ ማሻሻያ ጉዳይ እናንተን አይመለከታቹም የማለት ያህል የትኞቹ አንቀጾች እየተሸሻሉ እንዳለ እንኳን አናውቃቸውም ምክንያቱም እኛን አግልለውናል’’ ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹት።
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር የተቋቋመ ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት እንዲያሻስል በተሰጡት ፣ በጸረ ሽብርተኝነት እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጆች ላይ የሥራ ቡድኖችን በማዋቀር በሕግ ሙያ ላይ ለረጅም ዓመት ያለገሉና የዩኒቨርስቲ መምህራንን በማካተት እየሰራ እንደሆነ ይገጻል። የሥራ ቡድኖቹ የሚያቀርቧቸው ሐሳቦችም ለምክር ቤቱ ከቀረቡ በኋላ ለሕዝብ ውይይት ክፍት እየተደረጉ የሚገኙ ሃሳቦች ታክለውበት ረቂቅ አዋጁ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደሚቀርብ ያስረዳል። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ ማሻሻያም በዚህ ሂደት ስለማለፉ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የሥራ ቡድኑ ሰብሳቢና የሕግ ባለሙያው ደበበ ኃ/ገብርኤል ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት መስራታቸውን ያክላሉ።
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ ከሆነ ኤጀንሲው እስከዛሬ በነበረው የሥራ ዘመን ሕጉ ችግር አለበት፤ በዚህ መልኩ ይሻሻል ብሎ ጥናት አቅርቦ አያውቅም። በቅርቡም ቢሆን ጥናት አደረግን ብለው ያቀረቡት በዋናነት የሚያተኩረው የአቅም ግንባታ ላይ መሆኑንና በሕጉ ረገድ እዚህ ጋር ችግር አለበት የሚልም ሆነ ያቀረቡት ማሻሻያ ነገር እንደሌለ ያክለሉ።
እንዲሁም ይሄ ሕግ የሚሻሻለው ሕገ-መንግስቱን መሰረት ባደረገ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ እንደሆነም አክለው ገልፀዋል።
ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት ከመሥራት ባለፈ ለኤጀንሲው ለብቻው የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ በግልጽ መወያየቸውን እና ኤጀንሲው የሰጣቸውን ረቂቅም ተቀብለው እንዳዩት የሚናገሩት አቶ ደበበ ነገር ግን የኤጀንሲውን ሰው የሥራ ቡድናቸው አባል አድርገው እንዳላስገቡ አመልክተዋል።
ለዚህም አቶ ደበበ ምክንያት ያሉት ‹‹እያንዳንዱ ሰው ከመቀመጫው አንፃር ስለሆነ አንድን ነገር የሚያስበው ቀጥሎ የሚመጣውን ነገርና ይሄ በዚህ ቢሄድ ሥራዬን አጣለሁ፣ ህልውናዬን አጣለሁ ስለሚልና የተቋም አድሏዊነት ስለሚኖር ነው›› የሚል ነው።
ነገር ግን እንዲሻሻል በሚፈልጉት ሐሳብ ላይ አስተያየት እንዳይሰጡ የከለከለ አለመኖሩን በመጥቀስ አስተያየቱ እስከጠቀመ ድረስ የሚጣል ነገር አለመኖሩን አክለዋል። ይሁን እንጂ ‹‹ አሁን ያለው አቋሜ ለምን ይነካል ማለት ራስ ወዳድነት ነው፤ ለራስ ክብር ማሰብ ሳይሆን ለለውጡ መታገል ነው የሚያስፈልገው›› ሲሉም ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።
አቶ መስፍን በበኩላቸው ኤጀንሲው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት የትኞቹ ትክክልና መቀጠል አለባቸው; ችግርስ ያለባቸው ድንጋጌዎች እና አላሰራ ያሉ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው የሚለውን በውል ለይተውና ቢሻሻሉ ብለው ያወጧቸውን ነጥቦች ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሰጡም ምን እየተሰራ እንደሆነ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ፀጋዬ ደግሞ ‹‹መንግስት ማስመሰለም፣ የሆነ አካልን ለመጥቀምም ሳይሆን የእውነት ለውጥ ነው የምንፈልገው›› ይላሉ። በመሆኑም አማካሪ ምክር ቤቱ ያለአንዳች ሳንቲምና ሻይ ቡና ከመንግሥት ነፃ ሆኖ ነው መሥራቱ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ።
በፍትህና ሕግ ጉዳዮች ማሻሻያ ሂደት ላይ መንግሥት ሐሳብ የሚያቀርበው ምክር ቤቱ በሚጠራው የውይይት መድረክ ላይ እንደ አንድ ተሳታፊ ግለሰብ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ ሆኖ እንጂ በሂደቱ ላይ በምንም አግባብ ጣልቃ እንደማይገባም ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ገልፀዋል።
በቀጣይ የሕግ ማሻሻያዎች ጥናቶችና ረቂቆች በበይነ ድረ ገጽ ላይ እየተጫኑ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሐሳብ እንዲሰጥ ይደረጋል ያሉት አቃቤ ሕጉ ምክር ቤቱ ግን በገለልተኛነት እየሰራና ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ እንደሚቀጥል አመልተዋል።
የኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተሩ አቶ መስፍን በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት የበጎ ፈቃድ ሥራን ለመስራት ፈቃድ የሚያወጡት ከኤጀንሲው መሆኑን እና ፈቃድ ካወጡ በኃላም የሚከታተሏቸው እነሱ እንደሆነ በመጥቀስ ኤጀንሲው በማሻሻያ ሂደቱ እንዳይሳተፍ መደረጉን ኤጀንሲው እንደሚቃወም ደጋግመው ያነሳሉ።
አዲስ ማለዳ ለአቃቤ ሕግ ከቀረበው ረቂቅ እንደተረዳችው አቶ መስፍን ያነሷቸው የኤጀንሲው ስልጣንና ተግባራት አሁንም እንደተጠበቁ ናቸው። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በመንግሥትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ የሚቋቋም ቦርድም ይኖረዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምዝገባ ወረቀት ሊሰረዝ የሚችለውም በፍርድ ቤት በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here