በኢንቨስትመንት ላይ የሚሠራ አዲስ የዲያስፖራ ባንክ ሊቋቋም ነው

0
313

ኑሯቸውን በአገረ በእንግሊዝ ለንደን ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጪ ምንዛሬ የሚከፈል ካፒታል ያለው አዲስ የኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም ዝግጅት መጀመራቸውን አስታወቁ።

ዐሥር አባላት ያሉት አደራጅ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ውስጥ ወኪል በማዘጋጀት የገበያውን ሁኔታ በማስጠናት ላይ እንደሆነ እና የዝግጅት ሥራዎችን መጀመሩን ከአደራጆቹ መሐል የሆኑት መክብብ ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በእንግሊዝ የአክሲዮን ገበያ እና በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ የፋይናንስ ባሞያዎች የአደራጅ ኮሚቴው አባላት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በ50 ሚሊዮን ዩሮ የተፈቀደ ካፒታል እና በ15 ሚሊዮን ዩሮ የተከፈለ ካፒታል ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የዲያስፖራ ባንክ ሦስት ሺሕ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይመሰረቱታል ተብሎ ይጠበቃል። ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በባንክ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ እየጠበቁ መሆናቸውን የተናገሩት መክብብ በአንድ ዓመት ውስጥ ባንኩ ተቋቁሞ ይጠናቀቃል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ባንኩ በተለመደው የንግድ ባንክ ሥራ ውስጥ ለመሰማራት እቅድ እንደሌለው እና የኢንቨስትመንት ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮችን በውጪ ካሉ ጋር የሚያገናኝ ኮሮስፖንዳንት ባንክ ለመሆን ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። “በጥናቱ ውጤት መሰረት እና ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የባንክ ሥራ አዋጅ በሚወጣበት ወቅት የንግድ ባንክ ሥራን መሥራት ግዴታ ሆኖ ከተገኘ እና የገበያውም ፍለጎች አስገዳጅ ከሆነ ከግምት ውስጥ የምንከተው ይሆናል” ሲሉ መክብብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“የቤት ብድሮችን፣ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እና አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚደግፉ ሥራዎችን መሥራት ላይ የምናተኩር ሲሆን የረጅም ጊዜ ዕቅዳችንም የአገር ውስጥ ባንኮችን መጠቅለል ነው” ሲሉ መክብብ ተናግረዋል።

የሕግ ማዕቀፉ ታትሞ ከወጣ በኋላም ለብሔራዊ ባንክ ማመልከቻቸውን እንደሚያስገቡ ተናግረው ስትራቴጂያዊ እና የንግድ አዋጪነት ጥናቶች በእንግሊዝ አገር እና በኢትዮጵያ እየተጠኑ እንደሆነም ተናግረዋል። የባንኩ ሥያሜ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በቅርቡ እንደሚወሰኑም አስታውቀዋል፡፡
ከኹለት ዓመት በፊት የገበያውን አካሔድ በመመልከት የኢንቨስትመንት ባንክ የመመስረት ሐሳብ እንደነበራቸው እና በዚህ መሰረትም የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ 17 የንግድ ባንኮች በሃገሪቱ የሚገኙ ሲሆን ሶስት እስላማዊ ባንኮች አክሲዮን መሸጥ ጀመራቸው እና ሌሎች ባንኮችም በዝግጅት ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪም አምስት አነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ለማደግ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ብሄራዊ ባንክ ማስታወቁ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here