በኢትዮጵያ ትልቁ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ሊገነባ ነው

0
521

ኢትዮጵያ በመያዝ አቅሙ እስከ ዛሬ ከተገነቡት የመጀመሪያ ደረጃውን የሚይዘው የነዳጅ ማጠራቀሚያ (ዴፖ) ለመገንባት ጥናቶች እየተካሔዱ እንደሆነ ታወቀ። ግንባታውን በባለቤትነት የሚመራው እና ጥናቱንም እያስጠናው የሚገኘው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፤ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ፍላጎት ለማርካትና እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜም ረዘም ላለ ጊዜ ከክምችት በማውጣት ለማከፋፈል በማሰብ ግንባታው እንዳስፈለገ ተናግሯል።

በኦሮሚያ ክልል ዱከም አካባቢ እንደሚገነባ የታሰበው ይህ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ቦታው የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት ዱከም ከሚገኘው የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ጣቢያ በቅርበ ርቀት እንዲገኝ በማሰብ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን፤ ይህም የማጓጓዣ ወጪዎችን ለመቀነስም ዓይነተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ታሳቢ ተደርጓል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአንድ የባቡር ጉዞ የሚጓጓዘው የነዳጅ መጠን 72 መኪኖች በአንድ ጊዜ ሊያመላልሱት ከሚችሉት የነዳጅ መጠን ጋር እኩል መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል። ይህ ግንባታም ከኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ሐዲዱን ተከትሎ ከተገነባው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ኹለተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል 30 ሺሕ ሚትሪክ ቶን የሚይዝ የነዳጅ ማጠራቀሚያ መገንባቱ የሚታወስ ነው።

3 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያለው አዲሱ የነዳጅ ማጠራቀሚያ (ዴፖ) በቀጣዩ ዓመት ማለትም 2012 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ግንባታው እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዓለማየሁ ፀጋዬ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ግፋ ቢል ከ1 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ መያዝ የማይችሉ እንደነበሩ የጠቀሱት ኀላፊው አዲስ ለመገንባት የታሰበው ግን ከኹሉም ግዙፉ ማጠራቀሚያ እንደሚሆን እና የነዳጅ መጠባበቂያ ክምችቱንም ወደ ስድስት ወራት ከፍ እንደሚያደርገው ለማወቅ ተችሏል። እንደ ዓለማየሁ ገለፃ በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ሊገነቡ የታሰቡ 12 ማጠራቀሚያዎች ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ስምንት የናፍጣ ማጠራቀሚያዎች፣ ኹለት የቤንዚን ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ኹለት የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እንደሚሆኑ ታውቋል።

ጠቅላላው የግንባታ ወጪው 150 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የተነገረለት አዲሱ የነዳጅ ማጠራቀሚያ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ እንደሚያርፍም ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ማጠራቀሚያም መንግሥት እንደ አገር ውስጥ ማጠራቀሚያ እና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን የነዳጅ ምርቶች ማራገፊያም በማድረግ እንደሚጠቀምባቸው ታውቋል። ኢትዮጵያ እየተገባደደው ባለው ዓመት 2011 የመጀመሪያ ወራት ብቻ 959 ነጥብ 1 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ አስገብታለች። ለዚህም 630 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here