የሴት ባለሥልጣናት ትችት ሴትነታቸው ላይ ማነጣጠሩ ይቁም!

0
461

በሐምሌ መጨረሻ የፍትሕ አካላት በሚያዘጋጁት የፍትሕ ወር ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መአዛ አሸናፊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን የመፈፀም እና የማስፈፀም ሒደትን በተመለከተ አስተያየት ሰጥተው ነበር። ፕሬዘዳንቷ የሰጡት አስተያየት በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ የተለያዩ ድንጋጌዎችን የጣሰ ንግግር ነው በሚል ሲተች ቆይቷል።

የንግግሩ ይዘት ላይ መነጋገር እንዲሁም ሕጋዊነቱ ላይ ሐሳቦችን በማንሳት የተደረጉ ገንቢ ውይይቶች በቀጣይ ከሕግ ተርጓሚው የሚሰጡ አስተያየቶች በሕግ የበላይነት እና በፍርድ ቤቶች ገለልተኝነት ላይ ስላላቸው ጫና ያብራሩ ነበሩ። ነገር ግን በፕሬዝዳንቷ ማንነት ላይ ተመስርተው በማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ ሲንሸራሩ የነበሩ ሐሳቦች እንደ ማኅበረሰብ ሴት የሥራ ኀላፊዎችን በሥራ ውጤታቸው መለካት ላይ ገና ብዙ እንደሚቀር እና ሴትነታቸው ከስኬቶቻቸው እንዲሁም ከስህተቶቻቸው ቀድሞ መነጋገሪያ እንደሆኑ አስረድቷል።

የፕሬዘዳንቷን የሰውነት ቅርፅ፣ የቆዳ ቀለም ከወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር የተነሷቸውን ምስሎች መሰረት በማድረግ ተለያዩ ክብረ ነክ አስተያየቶች በሰፊው ሲዘዋወሩ ተመልክተናል። የእነዚህ የሥራ ኀላፊዎች የግል ሕይወት እንዲሁም ቤተሰብ ያላቸው መሆኑን በመዘንጋት እና እነዚህ አስተያየቶች በሥነ ልቦናቸው ላይ ሊያሳድሩ ስለሚችሉት ከፍተኛ ጫና ባለማገናዛብ የተሰጡት አስተያየቶች መዘዛቸው ብዙ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

እነዚህ ድርጊቶች ምናልባትም ስህተት ተፈፅሞ ቢሆን እንኳን ስህተቱን በጥላቻ በመሸፈን ለነገ አሻሽሎ ለመሔድ የማይረዳ ፋይዳ ቢስ ጥቃት ነው ብለን እናምናለን።
ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ኀላፊነት ላይ ያሉ ሴቶችን ነገም በእኔ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ይፈፀም ይሆን ወይ በሚል ሥጋት ውስጥ ከቶ የሚያሸማቅቅ እንዲሁም ከዚህ በኋላም ወደ ኀላፊነት ሴቶች እንዳይመጡ ወደ ኋላ የሚገፋ ድርጊት ነው። አንድ ሴት የሥራ ኀላፊ ከሚኖርባት የተለያዩ ጫናዎች ባሻገር እንዲህ ያሉ በሴትነት ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶች የሥራ ውጤታማነት ላይም ጉዳት ማምጣታቸው አይቀሬ ነው።

እነዚህ ድርጊቶች በማይታወቁ የማኅበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች ላይ ብቻ የሚሰጡ ሳይሆኑ በታዋቂ ሰዎች ገፆች እንዲሁም ለወትሮው ራሳቸውን የሰብኣዊ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ተሟጋች አድርገው በሚቆጥሩ ሰዎች ጭምር ሲካሔድ የነበረ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሒምም ተናገሩት በተባለው ንግግር ሴትነታቸው ላይ የተመሰረቱ አፀፋዎች በሚታወቁ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ሐሳብ በሚመሩ ሰዎች ጭምር ሲሰራጭ መቆየቱ ይበልጥ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

በእነዚህ የመንግሥት ሴት የሥራ ኀላፊዎች ንግግር ተጣሰ የተባለው ሕገ መንግስት ከመሰረታዊ መርሆዎቹ ጀምሮ ከተለያዩ አካላት ሲደርስባቸው ስለነበረው ጥቃት ምን ይላል የሚለውን ማየት አስተማሪ ይሆናል ብለን እናምናለን።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 10 (1) “ሰብኣዊ መብቶች እና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱ እና የማይገፈፉ ናቸው” ሲል ያስቀምጣል።
ይህ የሕገ መንግሥት መርህ አንድ ሰው የመንግሥት ኀላፊ በመሆኑ የሚያጣቸው ወይም የሚያገኛቸው ሳይሆኑ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ በተፈጥሮ የሚያገኛቸው መብቶች ናቸው። ታዲያ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24 “ማንኛውም ሰው ሰብአዊ ክብሩ እና መልካም ሥሙ የመከበር መብት አለው” የሚለውን ድንጋጌ በመጣስ ሴት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ስብአዊ ክብርን መጣስ ለሕገ መንግሥቱ የመቆም እና የመቆርቆር ድርጊት የሚሆንበት መሰረት የለም።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 (4)ም “ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎች እና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው” የሚለው በመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ዜጋ መከበር እና መተግበር ያለበት ሕግ ነው። የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለማቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪዎች የተቀመጡ የሴቶች መብቶችን መጣስም በሕግ የሚያስቀጣ ተግባር ነው።

አዲስ ማለዳ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችን የመፈፀም እና ማስፈፀም ዋነኛ ኀላፊነት በተለይም የመንግሥት ተግባር ቢሆንም እያንዳንዱ ዜጋ በሚያደርጋቸው እንቅስቀሴዎች ሊያከብረው ይገባል ብላ ታምናለች። ሕገ መንግሥቱ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ታሪካዊ የጭቆና ቅርስ ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለየ የሚጠብቅ ሰነድ ነው።

በእነዚህ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች ላይ የሚሰነዘሩ የቃላት ጥቃቶች በታዳጊ ሴት ልጆች ላይ ያላቸውን ጫናዎችም ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ እርከኖች ላይ የሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ከሥር ለሚያድጉ ልጆች አርዓያ ይሆናል ተብሎ ቢታመንም በሴትነታቸው እና በተለያዩ ማንነቶቻቸው ላይ የሚፈፀሙ የቃላት ጥቃቶች ግን ይህንን ተስፋ ወደ ኋላ መመለሳቸው አይቀርም።

በሴትነት ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የሰው ልጅ ማንነቶች ላይ የሚመሰረቱ ትችቶች ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው ነገር ግን ጉዳታቸው የከፋ ነው። ይልቁንም ወዳልተፈለገ ግጭት እና ውጥረት የሚያመሩ እንጂ በሥራ ውጤት እና ቅልጥፍና ላይ መሻሻል የማይጨምሩ ናቸው።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቷ ላይም ሆነ በፌዴሬሸን ምክር ቤት አፈጉ ባ ኤዋ ላይ የተሰነዘሩትን ጥቃቶች ለአብነት አነሳን እንጂ በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ላይ የሚሰነዘሩ የቃላት ጥቃቶች የሉም ማለት አይደለም። በተለይም የአካለዊ ቅርፆች እና በትዳር ሁኔታ ላይ በመመስረት የሚደረጉ ማጥላላቶችን መታዘብም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

በመአዛ አሸናፊ እና በሌሎች ሴት የሕግ ባለሞያዎች የተቋቋመው የሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበርን ጨምሮ በሴቶች መብቶች እና እኩልነቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማትም እንዲህ ዓይነት ተግባራትን በማውገዝ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው።

አዲስ ማለዳ ማንኛውም የመንግሥት የሥራ ኀላፊ ለሕዝብ ትችት እና አስተያየት ክፍት መሆን አለበት ብላ ታምናለች። ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እንዲሁም የተጠያቂነት መርሆች ማንኛውም የሥራ ኀላፊ ተግባራትን ለትችት የተጋለጠ የሚያደርገው ቢሆንም እነዚህን መብቶችን በመጠምዘዝ ሴቶችን የማጥቃት መሣሪያ መሆን ግን የለባቸውም።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here