የጤፍ ምርትን በሔክታር 10 ኩንታል ለመጨመር ሥራ ተጀመረ

0
1523

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤፍ አምራች በሆነው ምሥራቅ ጎጃም ዞን ከአራት ሺሕ በላይ አባወራዎች በ1 ሺሕ 227 ሔክታር መሬት ላይ ጤፍን በመስመር እንዲዘሩ በማድረግ በሔክታር ከአራት ኩንታል ወደ 14 ኩንታል ከፍ ለማድረግ ሥራ ተጀመረ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ከ2008 እስከ 2010 አጋማሽ የቆው የኤሊኖ የአየር ንብረት ለውጥ ከኋላ ቀር የምርት ሒደቱ ጋር ተደማምሮ ከፍተኛ ጫና አድርሶ ነበር። በዚህም ምርታቸው ላይ ከፍተኛ መቀነስ አጋጥሟቸው የነበሩት አርሶ አደሮቹ አዲስ እየተተገበረ ያለው የምርት ማዘመን የጤፍ ምርት ላይ ከኹለት እጥፍ በላይ ዕድገት እንዲያመጡ ያስችላል ተብሏል።

እንደ ኤጀንሲው ገለፃም ጤፍን በመስመር በመዝራት የሙከራ ሥራ በተሠራበት በምሥራቅ ጎጃም እናርጂ እናውጋ ወረዳ ከታቀደው የጤፍ ምርት 94 በመቶ መሳካቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በበኩሉ እንዳስታወቀው ጤፍን በዘመናዊ መንገድ በመስመር የመዝራቱ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በአደአ ወረዳ እና በአማራ ክልል ጎጃም ቦሰት ወረዳ ውጤት ማስመዝገብ ከጀመረ ሰንብቷል።

በነጭ ጤፍ ምርቱ ታዋቂ በሆነው በአደአ ወረዳ ውስጥ ካሉት 131 ሺሕ ነዋሪዎች ውስጥ 17 ሺሕ የሚሆኑት ገበሬዎች ናቸው። በቦሰት ወረዳ ውስጥ ካሉት 243 ሺሕ ነዋሪዎችም 101 ሺሕ የሚሆኑት በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ሲሆን በተለይም በጤፍ ምርት ላይ የተመሰረተ ግብርና ገበሬዎች ናቸው። አማካኝ የአንድ ገበሬ የጤፍ እርሻ መጠን በአደአ ወረዳ 1 ነጥብ 4 ሔክታር ሲሆን በቦሰት ወረዳ 1 ነጥብ 3 ሔክታር ነው።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በመኸር ወቅት 21 ከመቶ የሚሆነው የአጠቃላይ ሰብል ማምረቻ መሬት ውስጥ በአነስተኛ አርሶ አደሮች ለጤፍ ማምረቻነት ጥቅም ላይ ሲውል፣ በሰፋፊ የጤፍ እርሻ አምራች ገበሬዎች ለጤፍ ማምረቻነት ጥቅም ላይ የዋለው ግን 0.04 በመቶ ብቻ ነው።

በ2010 አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን ጤፍ በአነስተኛ አርሶ አደሮች መመረቱን ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ 8 ሺሕ 800 ቶን ጤፍ በሰፋፊ የጤፍ እርሻ አምራች ገበሬዎች ተመርቷል። አማካኝ የጤፍ ምርታማነት 14 ነጥብ 5 ኩንታል በሔክታር ሲሆን፣ ይህም በአነስተኛ አርሶ አደሮች እና በሰፋፊ የጤፍ እርሻ አምራች ገበሬዎች መካከል ተመሳሳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር አስታውቋል።

እንደተቋሙ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ እንደሚበቅሉ ሌሎች ሰብሎች ሁሉ ጤፍም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ነው። ከ2008-2010 የተከሰተው ድርቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀላል የማይባል የምርት መቀነስን አስከትሏል። ነገር ግን ጤፍ ከባድ አየር ንብረቶችን እና ረዘም ላለ ጊዜ የሚከሰትን የውሃ እጥረት እንደሚቋቋም በኢንስትቲዩቱ የግብርና ምርምር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አበበ አረዳ (ዶ/ር) ይናገራሉ። ከባድ ዝናብ ባለበት እና ውሃ የሚያቁር መሬት ላይም ጤፍ ያለችግር መብቀል እንደሚችል ኀላፊው ተናግረዋል። ሰብሉ ለኢትዮጵያ አገር በቀል ሰብል እንደመሆኑ መጠን፣ የዕፅዋት ተባዮችን እና በሽታዎችን መቋቋሙ እንደመልካም አጋጣሚ መታየቱን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ መጠኑ እየጨመረ የመጣው ድርቅ በጤፍ ሰብል ላይ ባለፉት ኹለት ዓመታት ከፍተኛ የምርት መቀነስ እንዲመጣ በማድረጉ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ምርቱ ወደ ቀድሞ የማምረት አቅሙ እንዲመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገለጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here