ቃና ቴሌቪዥን ተቀጣ

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስተዳደራዊ ችሎት ቃና ቴሌሌቪዥን አሳሳች የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ አስተላልፏል በሚል ከዓመታዊ ገቢው ላይ አምስት በመቶውን እንዲከፍል ሐምሌ 12/2011 ቅጣት ጣለበት።

የብሮድካስት ባለስልጣን ‹‹ሌሎች የጥርስ ሳሙናዎች በቂ አይደሉም፤ ለዚህም ነው ምርጫዬ ዳቦር ኸርባል የሆነው›› በሚል አረፍተ ነገር እናት እና ልጅ የሚነጋገሩበት ማስታወቂያ በጥናት ያልተረጋገጠ እና ለሌሎቹ ተወዳዳሪዎችም ፍትሃዊ ያልሆነ ነው በማለት አቤቱታ ማስገባቱን ተከትሎ ግንቦት 12/2011 በባለስልጣኑ አቃቤ ህጎች ክስ ተመስርቶበት ነበር። ባለስለጣኑ በማስታወቂያው ላይ ሙያዊ ጥናት በማካሄድ እና ማስታወቂያውን በማስረጃነት በማቅረብ አስረድቷል።

ከቃና ቴሌቪዥን ባሻገር የዳቦር ኸርባል የጥርስ ሳሙና አስመጪ ድርጅት ባለቤት አብዱራዛቅ ታከለ ፍትሃዊ ያልሆነ ማስታወቂያ አሰርተዋል በሚል በተመሳሳይ ከአመታዊ ገቢያቸው ላይ የአምስት በመቶ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ማስታወቂያውን ያዘጋጀው ቢ ሚዲያ እና የማስታወቂያ ድርጅትም በተመሳሳይ ከዓመታዊ ገቢው ላይ የአምስት በመቶ ቅጣት እንደተጣለበት የባለስልጣኑ የውሳኔ መዝገብ ያስረዳል።

የቃና ቴሌቪዥን የህዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኀይሉ ተክለ ሃይማኖት ለባለስልጣኑ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማለታቸውን እና ውሳኔው ላይም ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here