የኑሮ ውድነት መልስ የሚሻ የብዙኀን ጥያቄ

0
897

በመንግሥት ግምት ሩብ ያህሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ከድህነት ወለል በታች ነው። ይሁንና ይህ ቁጥር መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደማያሳይ እና ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የድሃ ድሃ ኑሮን የሚገፋ መሆኑን የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ። የመንግሥት ግምት ትክክል ነው ቢባል እንኳን ከድህነት ወለል ከፍ ብለዋል የሚባሉት ብዙኀን ሳይቀሩ ከወለሉ በታች ላለመውደቅ በትግል ውስጥ መሆናቸው እሙን ነው። የዋጋ ግሽበት ማንሠራራት እና የኑሮ ውድነት መጨመር በተለይ የሚፈትነው እነዚህን ከድህነት ወለል በታች ያሉ እና ከድህነት ወለል በታች ላለመውረድ የሚታገሉትን ብዙኀን ነው። ነገር ግን መንግሥት ለችግሩ በቂ እና አስቸኳይ ትኩረት አልሰጠውም።

አዲስ ማለዳ ብዙኀን ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ጥያቄያቸው ያልተመለሱ እንደመሆናቸው የብዙዎቹ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መሠረታዊ መንስዔ እንደሆነ ታምናለች። በነባሩ የሥራ አጥነት ላይ የዋጋ ግሽበት መጨመር እና የኑሮ ውድነትን ማስከተሉ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ያሉባቸውን ችግሮች በማባባስ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳያመሩ ያሰጋል። መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብይት ሒደቱን እና የንግድ ሥራን በቅልጥፍና ለማከናወን የሚያስችሉ የአሠራር ስርዓት ተሐድሶ ለማድረግ ጥረት ማድረጉ የሚደነቅ ነው። ሆኖም ይህ የድህነት እና የኑሮ ውድነት ጫንቃቸው ላይ ላረፈባቸው ብዙኀን አስቸኳይ መፍትሔ ለማግኘት የሚረዳ አይደለም።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በሙሉ የችግሩ መንስዔ የፖሊሲ ችግር እንደሆነ ይጠቁማሉ። ከመንስዔዎቹ ውስጥ በዐቢይነት የተጠቀሰው መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲገጥመው ገንዘብ እያተመ ገበያው ውስጥ የሚከት መሆኑ ነው። ይህ ድርጊት የመንግሥትን ችግር በጊዜያዊነት የሚፈታ ቢሆንም ቅሉ፥ ለብዙኀን ኢትዮጵያውያን ግን የገንዘቡን የመግዛት አቅም በመቀነስ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ስለሚያደርግ የድርጊቱ ሰለባ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

በሌላ በኩል የሰላም እና መረጋጋት እጦት የምርት እና ገበያ ስርዓቱን ውጤታማነት እያደናቀፈ በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቁርጠኛ ነኝ የሚለውን ያክል ለሰላምና መረጋጋትም ቁርጠኝነቱን ማስመስከር ቢችል ኖሮ፥ ይህ የአቅርቦት መቀነስ እንዲከሰት ያደረገ የሰላም እና መረጋጋት እጦት እንዳይከሰት ማድረግ ይችል ነበር ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይሁንና መንግሥት የልኂቃኑን የፖለቲካ ፍላጎት ለማቻቻል እና ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ የሚያሳየውን ሆደ ሰፊነት የብዙኀን ዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ችግሮች ለመቅረፍም ሊያሳየው ይገባል።

ኢሕአዴግ ውስጣዊ ተሐድሶ አካሔዶ መለወጡን ከማወጁ በፊት በሚከተለው ልማታዊ የአገረ-መንግሥት ናሙና “ዴሞክራሲ ከልማት በኋላ እንደሚመጣ” በቀጥታም ባይሆን በገደምዳሜ ሲናገር ነበር። ሆኖም የኢኮኖሚ ዕድገትን ከምጣኔ ሀብት ልማት ጋር በማምታታትም ሲታማ ከርሟል። አሁን “ከለውጡ” ወዲህ ባለው አሠራር ደግሞ የምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ ለጊዜው ቸል ተብሎ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ከተደረገ በኋላ እንደሚደረስበት ተደርጎ ተስሏል።

ይህ አካሔድ በመሠረቱ ከመጀመሪያው ያልተሻለ እና ዜጎች መሪዎቻቸውን እንዲሁም ይበጀናል የሚሉትን ስርዓት የሚዘረጉላቸውን ወኪሎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጡንም ይሁን የኢኮኖሚ ጥያቄያቸውን መልስ መሳ ለመሳ ማግኘት – ኹለቱንም ባንዴ – የሚፈልጉ መሆኑን ያልተረዳ ነው። የኢኮኖሚ ጥያቄ ከፖለቲካ ጥያቄ፣ ወይም የፖለቲካ ጥያቄ ከኢኮኖሚ ጥያቄ ተለይተው መታየታቸው የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

መንግሥት የኑሮ ውድነትን በአስቸኳይ ለመቅረፍ ማድረግ ከሚጠበቅበት እርምጃዎች አንዱ የገበያ ትስስሩ ውስጥ ያለውን ሙሰኝነት እና ጥቅመኝነት መቅረፍ ነው። የገበያ ስርዓቱ በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ያለ እና የዋጋ ተመኑ ምክክር የሚደረግበት በመሆኑ ብዙኀን ድሀዎች አማርጠው የመሸመት ዕድሉ አልተሰጣቸውም። መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ትስስር (‘ኦሊጋርኪ’) በመቅረፍ ፋንታ አለ በጅምላን እና የሸማቾች ማኅበር የመሳሰሉ የጅምላ አከፋፋዮችን እና ቸርቻሪዎችን ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ የሕዝብ ሀብት ከማባከን ውጪ ይኼ ነው የሚባል ለውጥ እንዳላመጣ ያለፉት ዓመታት ምስክር ናቸው። ስለሆነም፣ መንግሥት ተወዳዳሪ ነጋዴ ሆኖ ለመምጣት ከመሞከር ይልቅ የድሆችን ችግር ለመቅረፍ ፍትሐዊ የክትትል አሠራር በመዘርጋት ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እንዲሠራ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ሌላው እና የመንግሥትን በጀት ለመሙላት ገንዘብ ማተምን ከመቀነስ በተጨማሪ ሊታሰብበት የሚገባው የአገር ውስጥ ምርትን ማበረታታት ነው። በተለይም ከ80 በመቶ በላይ አምራች ዜጎች አርሶ አደር እና አርብቶ አደር በሆኑበት አገር ውስጥ የምግብ ፍጆታዎችን በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፥ ለምጣኔ ሀብት ቀውሱ አስተዋፅዖ ያደረገውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማባባስ የዋጋ ግሽበቱን ያንረዋል። መንግሥት በችርቻሮ ንግድ ውስጥ ገብቶ ገበያ ለማበረታታት ከሚሞክር፣ የምግብ ፍጆታ አምራቾችን ልዩ ማበረታቻ በመስጠት በውድድር ላይ የተመሠረተ የአቅርቦት መጨመር እንዲኖር ማድረግ ይጠበቅበታል።
በመጨረሻም የኑሮ ውድነት ጥያቄ የብዙኀን ጥያቄ መሆኑን ዕውቅና በመስጠት መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያበጅለት አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታቀርባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here