የጉደር ፋጦ ግድብ በ950 ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው

0
547

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን 950 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የጉደር ፋጦ ወንዝ ላይ ግድብ ስራ ፕሮጀክትን ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመስኖ ልማት ኮሚሽን ጋር ተፈራርሞ ሥራ ሊጀምር መሆኑን ነው የገለጸው።

ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቆ ኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ልዩ ስሙ መልኬ ዴራ ቀበሌ ውስጥ በፋጦ ወንዝ ላይ የሚገነባው የጉደር ፋጦ ግድብ በሶስት ዓመታት ግዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፣ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ እንዲሁም፣ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፆ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ግድቡ፣ 283 ሜትር ርዝመት እና 40 ሜትር ቁመት የሚኖረው ሲሆን፣ 57.7 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሀ ማጠራቀም ይችላል። በወንዙ የቀኝ ጎን በኩል 4 ሺህ 972 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋልም ተብሏል፡፡

የውኃ መሰረተ-ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፉ ሊድ የዲዛይን መሀንዲስ የሆኑት አዲሱ ወሌ፣ ከዚህ ቀደም ከኮርፖሬሽኑ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ባልደረቦች ጋር በመሆን ሰኔ 9/2011 በፕሮጀክት ሳይቱ ላይ በመገኘት ገለፃ አድርገዋል፡፡ በወቅቱም እንደተናገሩት በግድብ ግንባታ ከፍተኛ የሆነ ልምድ ያለው ቡድን እንደሚሰማራ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም የጉደር ፋጦ ግድብ ከተቻለ ከተያዘለት የግዜ ገደብ አስቀድመን ካልተቻለም በተቀመጠለት ግዜ እናጠናቅቃለን›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን አማካሪነት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ በስተምእራብ በኩል 150 ኪሎ ሜትር ላይ የሚጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ በአካባቢው ለሚኖሩ ከ2 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፆ ይኖረዋልም ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢፌዲሪ መንግሥት ለሚቀጥለው በጀት ዓመት በግንባታ ላይ ለሚገኙ እና አዳዲስ ግድብና መስኖ ፕሮጀክቶች የ13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ይታወቃል። ሆኖም ለቀጣዩ በጀት ዓመት 2012 የተመደበው በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት በቀረበበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በመገንባት ላይ ለሚገኙ አምስት ግድብ፣ መስኖና ተፋሰስ ፕሮጀክቶች 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በተጨማሪም በተማሩ ወጣቶች ለሚሠሩ መስኖ ልማት እና ለመስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ተብሎ በድምሩ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘም ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here